ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሐይማኖት መቀየር ምክንያት ጥቃት ወይም እስርን የሚፈሩት የሕንድ ክርስቲያኖች
በጥቅምት ወር አንድ እሁድ ፓስተር ሶሙ አቫራዲ በደቡባዊ ሕንድ ካርናታካ ግዛት ውስጥ በምትገኘው በሁባሊ ከተማ ወደሚገኝ ቤተ ክርስቲያናቸው ሲገቡ ደነገጡ።
"በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ በርካታ ሰዎች ተሰባስበው የሂንዱ ሐይማኖታዊ መዝሙሮችን እየዘመሩ፣ መፈክሮችንም እያሰሙ እየጮሁ ነበር" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፓስተሩም ተደናግጠው ለፖሊስ ደወሉ። ፖሊሶች በቦታው ሲደርሱም እነዚህ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ግለሰቦች የሂንዱ አማኝ የሆነ ግለሰብን ክርስትናን እንዲቀበል በማስገደድ ግፍ ፈጽመውበታል ብለው ፓስተሩን ከሰሷቸው።
ፓስተሩ በቁጥጥር ዋሉ፤ "በተወሰኑ የእምነት ተከታዮች ዘንድ ቁጣ በማነሳሳት" በሚል ክስም ለ12 ቀናት ያህል ታስረው የተፈቱትም በዋስ ነበር።
ይህ የተናጠል ክስተት አይደለም፤ በሕንድ ኢቫንጀሊካል ፌሎውሺፕ ቤተ ክርስቲያን ሪፖርት መስረት እተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያን ዓመት ከጥር እስከ ኅዳር ባለው ወቅት በካርናታካ ግዛት በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸሙ 39 ዛቻዎችና ጥቃቶች ተመዝግበዋል።
ከእነዚህም መካከል በፅንፈኛው የቀኝ ክንፍ አክራሪው ሂንዱ ስር የተደራጁ ቡድኖች በክርስቲያን ፓስተሮች ላይ የሚሰነዝሩት ጥቃቶችን ጨምሮ ሐይማኖታዊ አገልግሎቶችን እንዳያካሂዱ የከለከሉባቸው አጋጣሚዎች በርካታ ናቸው። በሕንድ ውስጥ ሕዝቡ በዋነኝነት የሂንዱ እምነት ተከታይ ሲሆኑ ክርስቲያኖች በጣም አናሳ ናቸው።
የክርስቲያን ተወካዮች እንደሚናገሩት የካርናታካን ግዛት ጨምሮ በብሔራዊ ደረጃ ገዢ የሆነው የባሃራቲያ ጃናታ ፓርቲ (ቢጄፒ) በግዛቲቷ ውስጥ የሐይማኖት ለውጥን የሚቃወም "ጠንካራ" ሕግ እያረቀቀ እንደሆነ በተደጋጋሚ አሳውቋል ይላሉ።
ረቂቅ ሕጉን ያዩት ተቺዎች ጭካኔ የተሞላበት ብለው የገለጹት ሲሆን፤ በዚህ ረቂቅ መሰረት ግለሰቦችን "በኃይል"፣ "በተጭበረበረ" ዘዴ ወይም በጋብቻ ሐይማኖትን በማስቀየር ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ የአስር ዓመት እስር እንዲሁም ከመንግሥት ጥቅማ ጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ይደረጋል።
በረቂቅ ሕጉ መሠረት ሐይማኖት ለመለወጥ የመረጡ ግለሰቦች ውሳኔያቸውን ቀድመው ከሁለት ወራት በፊት ለአካባቢው ባለሥልጣናት ማሳወቅ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ ባለሥልጣናቱም ከመፍቀዳቸው በፊት ውሳኔውን በጥልቀት ይመረምራሉ።
የክርስትና እምነት አመራሮች ይህ ረቂቅ ሕግ የሂንዱ አክራሪዎች ኅብረተሰቡን በበለጠ ኢላማ እንዲያደርጉ ያበረታታል የሚል ስጋት አላቸው።
በጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ ባሃራቲያ ጃናታ ፓርቲ (ቢጄፒ) ገዢነት እየተመራች ባለችው ሕንድ የተንሰራፋው የጽንፈኝነት ስሜት፣ አናሳ ማኅበረሰቦች ኢላማ እንዲሆኑና ያንዣበባቸውም ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ ፍርሃታቸው እንደተባባሰ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
"ረቂቅ ሕጉ ከፀደቀ የበለጠ ስደት እና ፈተናዎች እንደሚገጥመን መጠበቅ አለብን" በማለት የባንጋሎር ሊቀ ጳጳስ ፒተር ማቻዶ ለቢቢሲ ሂንዲ ተናግረዋል።
ይህ ረቂቅ ሕግ መሰረት ያደረገው ባለፈው ዓመት በሰሜናዊ የኡታር ፕራዴሽ ግዛት ተግባራዊ በሆነው ሌላ ሕግ ነው።
ይህ ሕግም የጸደቀው በቢጄፒ ፓርቲ አማካኝነት ነው። ሕጉ በአክራሪ ሂንዱዎች "የፍቅር ጂሃድ" ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሙስሊም ወንዶች ሂንዱ ሴቶችን በጋብቻ ውስጥ እምነታቸውን እንዲቀይሩ ያደርጓቸዋል የሚለውንም ለማመልከት የሚጠቀሙበት ነው።
ፖሊስ ከ100 የሚበልጡ ሐይማኖት በግዳጅ በመለወጥ የተጠረጠሩ ጉዳዮችን መዝግቧል ሲል አንድ ድረ-ገፅ ዘግቧል።
በሕንድ ውስጥ 65 ሺህ አብያተ ክርስቲያናትን የሚያስተዳድረው የሕንድ ኢቫንጀሊካል ፌሎውሺፕ ዋና ጸሐፊ ቄስ ቪጃዬሽ ላል በካርናታካ ያለው ሁኔታ "የፍቅር ጂሃድ" ተብሎ የሚጠራው ሕግ ከመውጣቱ በፊት በኡታር ፕራዴሽ ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
"ኅብረተሰቡን በከፍተኛ ሁኔታ ትገፋፋለህ እንደምንም ወርደው በሃሳብ እንዲስማሙ ታደርጋለህ። በሐይማኖት መቀየር ላይ የሐሰት ውንጀላ ትሰነዝራለህ በመጨረሻም ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጻረር ሕግ ታረቃለህ" ይላሉ።
ሐይማኖት መቀየር በሕንድ አከራካሪ ርዕስ ነው። የቀኝ ክንፍ አክራሪ ሂንዱዎች ክርስቲያን ሚስዮናውያን ገንዘብ ወይም ሌሎች ድጎማዎችን አቅም ለሌላቸው የሂንዱ እምነት ተከታዮች እንደ ጉቦ በመስጠት እምነታቸውን በግዳጅ ለውጠዋል በማለት ሲከሷቸው ይሰማሉ። ክርስቲያኖች ግን ይህንን ወቀሳ አይቀበሉትም።
ነገር ግን ዳሊትስ ወይም በሕንድ የኑሮ ደረጃ አመዳደብ መሰረት 'አይነኬ' የሚባሉት የማኅበረሰብ አባላት ካለው የሂንዱ የመደብ ተዋረድ ለማምለጥ ወደ ክርስትና እምነት ሲቀይሩ ይታያሉ። ምንም እንኳን ይህንን ማኅበረሰብ መብቱን እንዲያስጠብቅ ሕጎች ቢኖሩም መገለል ብቻ ሳይሆን ጥቃትም ሲደርስባቸው ይታያል።
በአሁኑ ወቅት ያለው የሐይማኖት ውጥረት አብዛኛውን ጊዜ ወደ ብጥብጥ ሲቀየርም ይታያል። በአውሮፓውያኑ 1999 በኦሪሳ ምሥራቃዊ ግዛት በክርስቲያን ተቋሞች ላይ በርካታ ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን በተጨማሪም አንድ አውስትራሊያዊ ሚስዮናዊ እና ሁለት ወጣት ልጆቹ በመኪና ውስጥ ተኝተው እያለ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል።
በካርናታካ ግዛት ያሉ ክርስቲያን ፓስተሮች እና ቀሳውስት የወደፊቱ እንደሚያስፈራቸው ይናገራሉ። መጀመሪያ ላይ ጥቃቶቹ በግዛቱ በተወሰኑ ሰፈሮች ተገድበው የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ካሉት 31 ወረዳዎች በ21ዱ ቢያንስ አንድ ጥቃት ተፈጽሟል በሚል ሪፖርት አድርገዋል።
"በዚች ግዛት ለ40 ዓመታት ያህል ኖሬያለሁ። ነገር ግን እነዚህ የሐይማኖት ቅየራ ክሶች በአሁኑ ወቅት ለምን እንደሚመጡ በትክክል አላውቅም። የሂንዱ እምነት ተከታይ የሆኑ ብዙ ጓደኞች አሉን" በማለት በቤላጋቪ ወረዳ የፓስተር ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ቄስ ቶማስ ያስረዳሉ።
ቄስ ቶማስ እንደሚናገሩት ባለፈው ወር የሂንዱ ቀኝ ክንፍ ቡድኖች ጥቃትን ለማስወገድ የፀሎት ፕሮግራሞችን እንዳያካሂዱ የአካባቢው ፖሊሶች መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለማኅበሩ አሳውቀዋል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ፖሊስ ለቢቢሲ ሂንዲ እንደተናገሩት በግዛቲቷ የሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎች ቄሶች እንዲጠነቀቁ ቢመክሩም በጉዳዩ ላይ "መንግሥታዊ ፖሊሲ" የለም ብለዋል።
በቤላጋቪ በሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን ቄስ የሆኑት አባ ፍራንሲስ ዲሶዛ ባለፈው ሳምንት አንድ ሰይፍ የያዘ ሰው ጥቃት ሊያደርስባቸው መሞከሩን ተናግረዋል። ጉዳዩ እየተጣራ ሲሆን የፖሊስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ለአባ ፍራንሲስ አረጋግጠውላቸዋል።
"ነገር ግን ያ የነበረው ፍርሃት አሁንም በውስጤ አለ" ይላሉ አባ ፍራንሲስ።
የሕንድ ሕገ መንግሥት ለሁሉም ዜጎች የፈለጉትን ሐይማኖት የመከተል መብት እንደሚያከብር በማመልከት የፀረ ሐይማኖት ቅየራ ሕግ አስፈላጊነት ላይ የማኅበረሰቡ ተወካዮች ጥያቄ እያነሱ ይገኛሉ።
ሕንድ ሐይማኖታዊ ለውጥን የሚገድብ ምንም ዓይነት ብሔራዊ ሕግ የላትም። ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት ረቂቅ ሕጎችን በፓርላማ ለማቅረብ የተደረገው ሙከራ ባይሳካም ነገር ግን የተለያዩ ግዛቶች ሐይማኖት መቀየርን ለመቆጣጠር የራሳቸውን ሕግን ባለፉት ዓመታት አውጥተዋል።
በፓስተር ሶሙ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን የመሩት የቢጄፒ ሕግ አውጪ አርቪንድ ቤላድ ለምን ክርስቲያኖች ብቻ ስለ አዲሱ ረቂቅ ይጨነቃሉ ብለው ይጠይቃሉ።
"አስገራሚው ጉዳይ ሙስሊሞች፣ ሲክ ወይም ጄይን ያሉ ሌሎች አናሳ ማኅበረሰቦች ስለ አዲሱ ሕግ አይጨነቁም" ሲሉ አክለዋል።
የግዛቲቷ አስተዳዳሪ ባስቫራጅ ቦምማይ በበኩላቸው ሰዎችን ወደ ሌላ ሐይማኖት ለመቀየር የሚሞክሩና የሚያማልሉ ብቻ ሕጉን መፍራት አለባቸው ይላሉ።
ሊቀ ጳጳስ ማቻዲ በዚህ አይስማሙ ጥቃቶቹም ሆነ በሕጉ ዙሪያ ያሉ ውይይቶች በግልጽ ክርስቲያኖች ላይ ያነጣጠሩ ለመሆናቸው ማሳያ ነው ይላሉ።
"መንግሥት እያደረገብን ያለው ጉዳይ መልካም ነገር አይደለም" ይላሉ።
የማኅበራዊ ተንታኙና በጡረታ የተገለሉት ሜጀር ጄኔራል ኤስጂ ቮምባትኬሬ በበኩላቸው ሰዎች በሕግ መመራት እንጂ ሥርዓት አልበኝነት አይገባም ይላሉ።
"በአንተ ላይ ቅሬታ ካለኝ መጥቼ ልደበድብህ አልችልም። ምንም አድርግ፣ የትኛውንም ነገር ፈጽመህ ሊሆን ይችላል፣ ጥቃት ልፈጽምብህ ግን አልችልም። በአሁኑ ወቅት ግን እየታየ ያለው ይህ ያልተለመደ ጉዳይ ተፈጻሚ እየሆነ ነው" ይላሉ።