ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የሕንድ የቤት እመቤቶች ለምን ራሳቸውን ያጠፋሉ?
የሕንድ መንግሥት ብሔራዊ የወንጀል መዛግብት ቢሮ (ኤንሲአርቢ) በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ባለፈው ዓመት ብቻ 22 ሺህ 372 የቤት እመቤቶች ራሳቸውን አጥፍተዋል።
ይህ ማለት በየቀኑ በአማካይ 61 ሴቶች ወይም በየ25 ደቂቃው አንዲት ሴት ራሷን ታጠፋለች።
በአውሮፓውያኑ 2020 በሕንድ ውስጥ ራስን በማጥፋት ከተመዘገቡት 153 ሺህ 52 ውስጥ 14.6 ያህሉ የቤት እመቤቶች ሲሆኑ ራሳቸውን ካጠፉት ሴቶች አጠቃላይ አሀዝ ከ50 በመቶ በላይ ይሸፍናሉ።
ያለፈው ዓመት ከሌሎቹ ጊዜያት የተለየ አልነበረም። ብሔራዊ የወንጀል መዛግብት ቢሮ ከአውሮፓውያኑ 1997 ጀምሮ የራስ ማጥፋትን በሥራ ዘርፍ ከፋፍሎ ባጠናቀረው መረጃ መሰረት በአማካይ በየዓመቱ ከ20 ሺህ በላይ የቤት እመቤቶች ራሳቸውን ያጠፋሉ።
በአውሮፓውያኑ 2009 አሀዙ ወደ 25 ሺህ 92 ከፍ ብሏል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እመቤቶች ራስ የማጥፋት ምክንያቶች ጋር በተያያዘ የሚወጡ ሪፖርቶች ችግሩን "በቤተሰብ ችግሮች" ወይም "ከትዳር ጉዳዮች" ጋር በተያያዘ ብለው ይጠቅሳሉ።
ለመሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ራሳቸውን እንዲያጠፉ የሚያደርጋቸው ምክንያት ምን ይሆን?
የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎች ዋነኛው ምክንያት በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት ነው ይላሉ። መረጃዎችን በምናይበት ወቅት 30 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች በትዳር አጋሮቻቸው ጥቃት እንደተፈጸመባቸው በቅርቡ በሕንድ መንግሥት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በርካቶች በጨቋኝ ትዳርና በማያፈናፍን ሁኔታ ውስጥ ተገደው እንደሚኖሩም ገልጸዋል።
"ሴቶች በእውነት ጠንካራ ናቸው፤ ነገር ግን የመቻል ገደብ አለው" በማለት በሰሜናዊ የቫራናሲ ከተማ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ኡሻ ቨርማ ስሪቫስታቫ ይናገራሉ።
"አብዛኞቹ ለጋብቻ ሕጋዊ እድሜ 18 ዓመት ሲሞላቸው ይዳራሉ። ሚስት ብቻ ሳትሆን ምራት ትሆናለች ቀኑን ሙሉ ያለ እረፍት ለባለቤቷና ለቤተሰቦቹ ምግብ በማብሰል፣ በማፅዳት እንዲሁም ሌሎች ሥራዎችን ስትከውን ታሳልፋለች። ሁሉም ዓይነት ገደቦች በእሷ ላይ ተቀምጠዋል። ያላት የግል ነፃነት በጣም የጠበበ ነው። የራሷን ገንዘብ የማግኘት ዕድሉም የመነመነ ነው" ይላሉ።
አክለውም "ትምህርቷ እና ህልሟ ምንም ለውጥ አያመጣም። ምኞቷም ቀስ በቀስ መጥፋት ይጀምራል፤ እናም በተስፋ መቁረጥ እና በብስጭት ይተካል። ህይወቷም ስቃይ ይሆንባታል" በማለት ያስረዳሉ።
ዶክተር ቬርማ ስሪቫስታቫ በእድሜ የገፉ ሴቶች ራስን የማጥፋት ምክንያቶች የተለያዩ መሆናቸውን ይናገራሉ።
"ብዙዎቹ ልጆቹ አድገው ከቤት ከወጡ በኋላ ቤታቸው ባዶ የመሆን ሁኔታ ለበርካቶች አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። እንዲሁም በርካታዎቹ በማረጥ ወይም በቅድመ-ማረጥ ምልክቶች ይሰቃያሉ። እነዚህም ድብርት እና ማልቀስ የመሳሰሉት ናቸው።"
ነገር ግን ዶክተሯ ራስን ማጥፋት በቀላሉ መከላከል እንደሚቻል ይናገራሉ።
"ህይወቷን ልታጠፋ ያለች አንዲት ሴት ለአንድ ሰከንድ ያህል ብናስቆማት እንደገና የማሰብ ዕድሏ ከፍ ይላል። ራሷንም ላታጠፋ የምትችልበት እድሉ ከፍተኛ ነው" ይላሉ።
ይህ የሆነበት ምክንያት የሥነ አእምሮ ባለሙያው ሱሚትራ ፓትሃር እንደሚያብራሩት በርካታ ሕንዳውያን ራሳቸውን የሚያጠፉት በግልፍተኝነት ወይም በስሜታዊነት ነው።
"አንድ ግለሰብ ቤቱ መጥቶ ሚስቱን ይደበድባል በምላሹም ራሷን ታጠፋለች" ይላሉ።
ገለልተኛ ጥናት እንደሚያሳየው ራሳቸውን ከሚያጠፉት ሕንዳውያን ሴቶች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በቤት ውስጥ ጥቃት ይሰቃያሉ፤ ነገር ግን የቤት ውስጥ ጥቃት በብሔራዊ የወንጀል መዛግብት ቢሮ መረጃ ውስጥ እንደ ምክንያት አልተካተተም።
"በርካታ በቤት ውስጥ ጥቃት የሚሰቃዩ ሴቶች የአዕምሮ ጤናቸው በአንፃሩ የተጠበቀ ሆነው የሚቆዩት በሚደረግላቸው መደበኛ ያልሆነ ድጋፍ ብቻ ነው" በማለት በባንጋሎር ላይ የተመሰረተ የአእምሮ ጤና መተግበሪያ ዋይሳ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ቻይታሊ ሲንሃ ይናገራሉ።
ቀደም ሲል በሙምባይ የመንግሥት የአዕምሮ ህክምና ሆስፒታል ውስጥ ለሦስት ዓመታት የሰሩት ቻይታሊ ሲንሃ ራሳቸውን ሊያጠፉ ሞክረው የተረፉ ሴቶችን በሚያማክሩበት ወቅት የተረዱት ጉዳይ ቢኖር፣ በርካታ ሴቶች በባቡሮች ሲጓዙ ወይም ከጎረቤቶቻቸው ጋር አትክልት ሊገዙ በሚወጡበት ወቅት በርካታ መደበኛ ያልሆኑ ድጋፍ ሰጪ ቡድኖችን መመስረታቸውን ነው።
"ሀሳባቸውን የሚገልጹበት ሌላ መንገድ አልነበራቸውም እና አንዳንድ ጊዜ የጤነኝነት ሁኔታቸውን የሚወሰነው ወጥተው ከጎረቤት ወይም ድጋፍ ሰጪ ከሚሏቸው ሰዎች ወይም አንድ ሰው ጋር ብቻ በሚያደርጉት ውይይት ላይ ነው" ሲሉ ወረርሽኙ እና የእንቅስቃሴ ገደብ ሁኔታቸውን እንዴት እንዳባበሰው ይናገራሉ።
"ወንዶች ወደ ሥራ ሲሄዱ የቤት እመቤቶች በቤታቸው ውስጥ ደኅንነት ይሰማቸው ነበር፤ ነገር ግን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ይህም ሁኔታ ጠፋ። በቤት ውስጥ ለጥቃት የተጋለጡት ደግሞ መውጪያ መግቢያ አጥተው ከጥቃት አድራሾቻቸው ጋር ይቆያሉ ማለት ነው። ወረርሽኙ እንቅስቃሴያቸውን የበለጠ ገድቦ ደስታን ወይም መፅናኛ የሚያገኙበትን ሁኔታም አሳጥቷቸዋል። ስለዚህ ቁጣ፣ መጎዳትና ሐዘን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ራስን ማጥፋት የመጨረሻ አማራጫቸው ይሆናል" ይላሉ።
ሕንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የራስን ማጥፋት የሚመዘግባት አገር ናት።
ሕንዳውያን ወንዶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሩቡን ያህል ቁጥር ሲይዙ ሕንዳውያን ሴቶች ደግሞ 36 በመቶውን ይይዛሉ። እነዚህም ከ15 እስከ 39 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
ነገር ግን የአእምሮ ሕመሞች እና ራስን ማጥፋትን መከላከል ላይ ጥናት ያደረጉት ዶክተር ፓትሃሬ የሕንድ ይፋዊ አሀዞች የችግሩን ትክክለኛ ሁኔታ የማያሳይና በጣም ዝቅተኛ ነው ይላሉ።
"የሚሊዮኖች ሞት ጥናት [ከአውሮፓውያኑ ከ1998-2014 ባለው ጊዜ ውስጥ 2.4 ሚሊዮን ቤቶችንና ወደ 14 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ያካተተው] ወይም የላንሴት ጥናት በሕንድ ውስጥ ራስን ማጥፋት በዝቅተኛ ሁኔታ ሪፖርት እንደሚደረግ ይፋ ያወጣ ሲሆን ይህም ከ30 አስከ 100 በመቶ ባለው ነው" ይላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ራስን ማጥፋት በሕንድ ውስጥ በግልፅ የሚወራ አይደለም። ከራስ ማጥፋት ጋር ተያይዞ መገለል ስለሚከተል እና ነውር ስለሆነ፣ በርካታ ቤተሰቦች ይህንን ለመደበቅ ይሞክራሉ። በሕንድ ገጠራማ አካባቢ የአስከሬን ምርመራ ግዴታ አይደለም።
በርካታ ሃብታሞች ደግሞ ራሳቸውን ያጠፉ ቤተሰቦች ካሏቸው ድንገተኛ ሞት ተብሎ እንዲሰፍር ከፖሊስ ጋር ይመሳጠራሉ። የፖሊስ መረጃ ደግሞ ጥያቄ ውስጥ አይገባም።
ሕንድ ብሔራዊ ራስን ማጥፋት የመከላከል ስትራቴጂ እየነደፈች ባለችበት በዚህ ወቅት ዶክተር ፓትሃሬ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ተግባር የመረጃ ጥራት መስተካከል ነው ብለዋል።
"በሕንድ ውስጥ ራስ የማጥፋት ሙከራዎችን ቁጥር በምንመለከትበት ወቅት በጣም ዝቅተኛ ናቸው። የሙከራዎችን አሀዝ በምናይበት ወቅት በየትኛውም የዓለም ክፍል ከራስ ማጥፋት ቁጥር በአጠቃላይ ከአራት እስከ 20 እጥፍ በላይ ናቸው። ይህም ማለት ሕንድ ባለፈው ዓመት 150 ሺህ ራስን የማጥፋት ክስተቶችን ከመዘገበች የሙከራዎች ቁጥር ከ600 ሺህ እስከ 6 ሚሊዮን ይደርሳል" ሲሉ ተናግረዋል።
ዶክተር ፓትሃሬ "ሕዝቡ በአደጋ ላይ እንዳለ ተረድተን በዓለም አቀፍ ደረጃም መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል አስበን ራስ ማጥፋትን ለመከላከል ጣልቃ መግባት ቢኖርብንም በመረጃ አያያዝ ምክንያት ተቸግረናል" ብለዋል።
"የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአውሮፓውያኑ 2030 በዓለም አቀፍ ደረጃ ራስን ማጥፋት በአንድ ሦስተኛ ለመቀነስ አቅዷል። ነገር ግን የሕንድን ያለፈውን ዓመት ከአምና በስቲያ ጋር ስናነፃፅረው በ10 በመቶ ጨምሯል። የመቀነሱም ሁኔታ ህልም ይመስላል" በማለት ዶክተር ፓትሃሬ አስረድተዋል።