ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሕንድ፡ ራሳቸውን ለማጥፋት የሚመጡ ሰዎችን 'አላስሞት' እያለ ያስቸገረው ዋናተኛ
ሺቫ ይባላል፡፡ ወጣት ነው፡፡ በሰሜን ሕንድ ሀይድራባድ ከተማ ይኖራል፡፡ እዚያ አንድ ሐይቅ አለ፡፡ ሑሴን ሳጋር ሐይቅ የሚባል፡፡
ብዙ ሰዎች እየገቡ ሰምጠው ይሞቱበታል፡፡ ራሳቸውን ማጥፋት የሚፈልጉ ሰዎች እዚያ ይሄዳሉ፡፡ ራስን ለማጥፋት በጣም የተስማማ ሐይቅ ነው ይሉታል የአካባቢው ሰዎች፡፡ አንደኛ ጥልቅ ነው፤ ሁለተኛ ቆሻሻ ነው፤ ሦስተኛ እባብና በርካታ ገዳይ እንሰሳት ይኖሩበታል፡፡
ራስን ለማጥፋት እንደ ሑሴን ሳጋር ያለ ሐይቅ ከየት ተገኝቶ?
ሺቫ ግን አስቸገረ፡፡ ሰዎች በሰላም ሰምጠው እንዳይሞቱ እንቅፋት ሆነባቸው፡፡
ከሞት ጋር ለምን ይተናነቃል?
ለዓመታት ሺቫ ፖሊስን ሲያግዝ ነው የኖረው፡፡
ገና 10 ዓመቱ ላይ ሳለ ምን ሆነ መሰላችሁ?
የሆኑ ፖሊሶች መጡና ከዚህ ሐይቅ የሞተ ሰው ሬሳ ለሚያወጣ ሰው ገንዘብ እንሸልማለን አሉ፡፡ ሺቫ እዚያ ሰፈር ነበር፡፡ ለፖሊሶቹ "ሰውየውን እኔ አወጠዋለሁ" አላቸው፡፡
ፖሊሶቹ ደንግጠው እርስ በእርስ ተያዩ፡፡
ፖሊስ በዚያ አካባቢ በቂ በጀት ስለሌለው የራሱ ጠላቂ ዋናተኛ እንኳን አልነበረውም፡፡
የፖሊስ መኮንኖቹ መዋኘት እንኳ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ነበር ዋናተኛ ያስፈለጋቸው፡፡ ሺቫን ግን አላመኑትም፡፡
ይህ የ10 ዓመት ታዳጊ እንዴት ነው ከዚህ ሐይቅ ሬሳ ተሸክሞ የሚወጣው?
"ሬሳ አወጣለሁ ብሎ ሬሳ እንዳይሆን ብቻ" እያሉ ሲከራከሩ ሺቫ ዘሎ ባሕር ውስጥ ገብቷል፡፡
በደቂቃ ውስጥ ሬሳውን ይዞት ወጣ፡፡ 40 ሩጲ ተከፈለው፡፡ በዶላር 0.42 ሳንቲም ቢሆን ነው፡፡
ይህ ከሆነ 20 ዓመት አለፈው፡፡ አሁን ሺቫ 30 ዓመት ደፍኗል፡፡ ሥራውን ግን አልቀየረም፡፡ ሬሳ ያወጣል፡፡
ለምን አላስሞት ይላል?
አሁንም ድረስ ሬሳ ጥልቅ ሐይቅ ውስጥ ገብቶ ያወጣል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ግን ሥራው፡፡ ሰዎች ራሳቸውን ሊያጠፉ ሲሉም ያደናቅፋል፡፡
ሺቫ የሚኖረው ከሑሰይን ሳጋር ሐይቅ በቅርብ ርቀት ነው፡፡ ይህ ሐይቅ ሰው ሰራሽ ነው፡፡
ይህ ሐይቅ የሂንዱ አማልክትን ለማጥመቅ እና ጋኔሻ ለሚባለው መንፈሳዊ ክብረ በዓል አገልግሎት ላይ ይውላል፡፡
ይህ ሐይቅ ታዲያ ለማምለኪያነት ብቻ አይደለም የሚውለው፡፡ ሰዎች ራሳቸውንም ለማጥፋት የሚመርጡት ሁነኛ ሐይቅ ነው፡፡
ላለፉት 20 ዓመታት እንዳደረገው ሁሉ ሺቫ አሁንም የሟቾችን ሬሳ ከሐይቁ ያወጣል፡፡ ፖሊስ ዛሬም ድረስ በሱ ተማምኖ ነው ያለው፡፡
በዚህ ሐይቅ ብቻ ሳይሆን በአቅራቢያ ከሚገኙ ሌሎች ሐይቆች በርከት ያሉ ሬሳዎችን ያወጣል፡፡
ሺቫ ሬሳን ብቻ ማውጣት አይደለም ሥራው ብያችኋለው፡፡ እንዲያውም ይበልጥ የሚታወቀው የታቀደን ሞት በማክሸፍ ነው እንጂ ሬሳ በመጎተት አይደለም፡፡
"ኧረ በጣም ብዙ ሰው ነው ያዳንኩት፤ መቁጠር ሁሉ አቁሜያለሁ፤ ለመጨረሻ ጊዜ ትዝ የሚለኝ 114ኛውን ሰው ማዳኔ ነው" ብሏል ለቢቢሲ፡፡
አሁን የሟቾች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ነፍስ አዳኝ እጥረት ገጥሞታል፡፡ ከሰሞኑ ሚስቱን ዋና የሚያለማምዳትም ለዚሁ ነው፡፡
እሷ ቢያንስ ሴት ሟቾችን ብታድን፤ ከሞቱም ደግሞ ሬሳቸውን ጎትታ ብታወጣ ቀላል አይደለም፡፡
ኢንስፔክተር ቢ ዳናላክሽሚ የአካባቢው መርማሪ ፖሊስ ናቸው፡፡ እሳቸው ስለ ሺቫ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡
"ሺቫ፣ እኔ ብቻ የማውቀው ከመቶ ሰው በላይ ሰው ራሱን ለማጥፋት ሲል ሕይወቱን አድኗል" ይላሉ፡፡
ራስን ማጥፋት በሕንድ አገር ወንጀል ነው፡፡ ስለዚህ ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩትን ካዳናቸው በኋላ እንዲለቃቸውና እንዲሸሹ ይፈልጋሉ፡፡ በኋላ ግን ፈልገው ያገኙታል፡፡
ይህን ሁሉ ነፍስ የሚያድነው ሺቫ ነፍስ ካወቀበት ዘመን ጀምሮ ወላጆቹን አያውቅም፡፡ ጎዳና ነው ያደገው፡፡
የሆነ ጊዜ ግን አንዲት አሮጊት አስጠጉት፡፡ የሳቸው ልጅ ነው ለመጀመርያ ጊዜ ዋና ያስተማረው፡፡ የሆነ ጊዜ ታዲያ የሆኑ ጓደኞቹ ጋር እየዋኙ ሳለ ይሄ ዋና ያስተማረው "ወንድሜ" የሚለው ልጅ ይሰምጣል። እሱን ለማዳን ጠልቆ የገባው ሌላ ልጅ ግን በዚያው ሞተ፡፡
"አሁን ያ ይጸጽተኛል፤ ሰዎችን የምታደገው ያን ጓደኛችንን ባለማዳኔ ለማካካስ ነው" ይላል፡፡
ሺቫ መሞት ፈልገው ከሞት ድንገት የታደጋቸው ሰዎች በሚሰጡት የኪስ ገንዘብ ነው የሚተዳደረው፡፡
የተመኙትን ሞትን ካስመለጣቸው በኋላ በጣም ይጠሉታል፡፡ ትንሽ ከኖሩ በኋላ ግን ባለውለታቸው ያደርጉታል፡፡
ሺቫ አሁን ትንሽዬ ዝናን እያገኘ መጥቷል፡፡ "የአገሬውን ሰው አላስሞት ያለው ወጣት" በሚል ጋዜጦች ላይ ስሙ ከወጣ በኋላ ቴሉጉ በሚባል የሕንድ ፊልም ላይ እንዲተውን ተደርጓል፡፡
ኮቪድ ደንበኛ አብዝቶለታል
ሰሞኑን አንድ ሰውዬ ኮቪድ ያዘኝ ብሎ ደንግጦ ራሱን ለማጥፋት ወደ ሐይቁ መጣ፡፡ ከጓደኛው ጋር ነው የመጣው፡፡
ሆኖም ጓደኛው ይህ ኮቪድ ያዘኝ የሚለው ሰው ራሱን ሊያጠፋ እንደመጣ አላወቀም፡፡ ጥልቁ ሐይቅ ውስጥ ሲገባ ጓደኛውም አብሮት ዘሎ ገባ፡፡ ሺቫ ሦስተኛ ሆኖ ተከተላቸው፡፡ ማዳን የቻለው ግን ለመሞት አቅዶ የነበረውን ጓደኛ ብቻ ነበር፡፡ ባለ ኮቪዱ ሰውዬ ግን እንዳለመው ይቺን ምድር ተሰናበተ፡፡
"ሬሳውን አውጥቼ ሰጠኋቸው፡፡ ነገር ግን ቤተሰቦቹም ኮቪድ ይይዘናል ብለው ሬሳውን ለመውሰድ አልፈለጉም" ይላል ሺቫ፡፡
"ሬሳውን የሚረከበኝ ሳጣ ምን ላድርግ? አቃጠልኩት"
ይህ ሰዎች በስፋት እየሞቱበት ያለው ሐይቅ በጣም ቆሻሻና የተበከለ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ሺቫ በርካታ የቆዳ ሕመሞች እንዲሁም ታይፎይድ ይዞታል፡፡ ሆኖም ወዴት ይሂድ፡፡
ለምን ሥራ አትቀይርም ሲባል፣ "እኔ ሰዎችን ከሞት ከማትረፍ በላይ እርካታ የሚሰጥ ሥራ አለ ብዬ አላምንም፤ ከዚህ ኃይቅ ወደየትም ንቅንቅ አልልም" ይላል፡፡