ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ50 ሚሊዮን አለፈ
በመላው ዓለም በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ከ50 ሚሊዮን አለፈ።
በበርካታ አገራት በኮቪድ-19 የሚያዙ ከፍተኛ ቁጥር መመዝገቡን ተከለትሎ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ከ50 ሚሊዮን አልፏል።
እንደጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ ከ1.25 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል።
በብዙ አገራት በቂ ምርመራ ባለመደረጉ እንጂ ይህን አሃዝ ከፍ ያለ ነው ተብሎ ይገመታል።
ሮይተር በበኩሉ ቫይረሱ ሁለተኛ ዙር ማገርሸቱ ከተመዘገበው ቁጥር ውስጥ ሩብ ለሚሆነው ድርሻ አለው ሲል ዘግቧል፡፡
ቀደም ሲል የቫይረሱ ስርጭት ማዕከል የነበረችው አውሮፓ 12.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙባት 305,700 ደግሞ ህይወታቸው አልፎፋባት በድጋሚ የቫይረሱ ስርጭቱ ማዕከል ሆናለች፡፡
በአሜሪካ 10 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡ ለተከታታይ ሦስት ቀናት በቀን ከ125,000 በላይ ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የችግሩን መጠን ከማሳነስ ባለፈ የአፍና የአፍንጫ ጭምብል ማድረግ እና አካላዊ ርቀት ማስጠበቅን ባይቀበሉም ተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሙሉ ሃይላቸው እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።
ባይደን በጥቂት ቀናት ከፍተኛ የሳይንስ ሊቃውንትን ያካተተ የኮሮናቫይረስ ግብረ ኃይል ለማቋቋም ቃል ገብተዋል። ተጨማሪ ምርመራዎችን ለማድረግ እና ሁሉም አሜሪካዊያን ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ሲሆኑ የአፍና የአፍንጫ ጭንብል እንዲያደርጉ ለመጠየቅ አቅደዋል።
ባይደን ወረርሽኙ በአገሪቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ኃላፊነታቸውን ሊረከቡ ይችላሉ ሲሉ የቀድሞው የአሜሪካ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር ኮሚሽነር ዶ/ር ስኮት ጎትሊብ ገልጸዋል።
እንደ ዶ/ር ጎትሊብ ከሆነ የቫይረሱ ስርጭት ጥር መጨረሻ ድረስ መቀነስ ይጀምራል። "ብቸኛው ጥያቄ በዚህ ጊዜ ውስጥ ስንት ሰዎች ይሞታሉ እና ምን ያህል ሰዎች ይያዛሉ የሚለው ነው" ብለዋል፡፡
በአውሮፓ ፈረንሳይ እሁድ 38,619 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዝግባለች። ቅዳሜ ከፍተኛ ሆኖ ከተመዘገበው የ86,852 ቁጥር ግን በጣም ያነሰ ነው፡፡ ሆኖም የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ መረጃ የመሰብሰብ ችግሮች እንደነበሩበት በመግለጽ ሰኞ እርማት እንደሚያደረግ ገልጿል ፡፡
ህንድ እና ብራዚልም እንዲሁ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል ፡፡