አዘርባጃን ከአርሜኒያ ጋር በምታደርገው ጦርነት ቁልፍ ከተማን ተቆጣጠርኩ አለች

ጎረቤት አገራቱ አርሜኒያና አዘርባጃን የሚያደርጉት ጦርነት ተፋፍሞ ቀጥሏል።

አዘርባጃን እንደምትለው ተገንጣይ የናግሮኖ ካራባህ ክልል ቁልፍ ከተማ የሆነችውን ሱሺን ተቆጣጥራለች።

ይህ ከወራት በፊት የሚታሰብ አልነበረም።

የአዘርባጃኑ ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊየቭ ድሉን በቴሌቪዥን ትናንት እሑድ ማብሰራቸውን ተከትሎ ሕዝቡ ደስታ ፈንቅሎት አደባባይ ወጥቷል።

አዘርባጃን በእጇ ያስገባቻት ከተማ ሹሻ ተብላ ነው የምትጠራው። አርመኖች ደግሞ ሹሺ ነው የሚሏት።

አዘርባጃኖች በድል ከፍተኛ ደስታ ውስጥ ባሉበት በአሁኑ ወቅት አርሜኒያ "ሹሺ ከተማ ሙሉ በሙሉ አልተወሰደችብኝም ጦርነቱ ቀጥሏል" ስትል አስተባብላለች።

እንደሚባለው አዘርባጃን ሹሺ ከተማን በእጇ ካስገባች ቀጣይ ጦርነቶች ቀላል ይሆኑላታል ይላሉ የጦር አዋቂዎች። ምክንያቱም ሹሺ ባላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ነው ይህን የሚሉት።

አዘርባጃንና አርሜኒያን ለዚህ የከፋ ጦርነት ያበቃቸው ክልል ናጎርኖ ካራባህ የሚባለው ነው።

ይህ ክልል በዓለም አቀፍ ደረጃ የአዘርባጃን እንደሆነ ይታወቃል። ሆኖም በክልሉ ነዋሪዎች የአርመን ብሔር ተወላጆች በመሆናቸው በአዘርባጃን ሥር መሆንን አይሹም። ራስ ገዝ አስተዳደርን ይሻሉ። ውግንናቸውም ከአርሜኒያ ጋር ነው።

ናጎርኖ ካራባህ ሙሉ በሙሉ የሚደገፉትም በአርሜኒያ መንግሥት ነው።

በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1994 በተጠናቀቀው ደም አፋሳሽ የሁለቱ አገሮች ጦርነት 30ሺ ሕዝብ አልቋል። በመቶ ሺዎች ተፈናቅለዋል። ሆኖም ጦርነቱ ያን ጊዜ ያለ ሁነኛ የሰላም ስምምነት በመጠናቀቁ ዘመናትን ቆጥሮ በድጋሚ አገርሽቷል።

አዘርባጃን ተቆጣጠርኳት የምትላት ሹሻ ከተማ የምትገኘው በአወዛጋቢው ክልል ናጎርኖ ካራባህ ዋና ከተማ ስቴፓናከርት መግቢያ ላይ ነው።

የአዘርባጃን ፕሬዝዳንት "በምድር ላይ የትኛውም ኃይል ድሉን ሊነጥቀን አይችልም" ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ሹሻ ከተማን ከመቆጣጠራቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ለቢቢሲዋ ኦርላ ጉሪን እንደነገሯት አርሜኒያ ጊዜው እየነጎደባት ነው። እጅ መስጠቷም የማይቀር ነው።

እስካሁን በጦርነቱ ምን ያህል ዜጎች እንደተገደሉ አይታወቅም።

ሆኖም 1500 ወታደሮች መሞታቸው ይገመታል። የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን ግን ከ5ሺ ሰዎች በላይ በአዘርባጃንና በአርሜኒያ ጦርነት አልቀዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የሹሻ ከተማ በአዘርባጃን ወታደሮች ቁጥጥር ሥር መውደቋ እንደተሰማ የአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ አደባባዮቿ ደስታ ባሰከራቸው ዜጎች ለመሞላት ጊዜ አልወሰደባትም።

ሮይተርስ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ለማድረስ የቱርኩን ኤርዶጋንን የቀደመ የለም። "አዛሪ ወንድሞቼ! እንኳን ደስ አላችሁ። ድሉን አጣጥሙት" ብለዋል።

ቱርክና አዘርባጃን የቋንቋና የባሕል እንዲሁም የሃይማኖት ዝምድናቸው የጎላ ነው። ቱርክ በጦርነቱ አዘርባጃንን ወግና በይፋ እገዛ ትሰጣለች። ሩሲያም በተመሳሳይ በጦርነቱ ውስጥ አርሜኒያን ደግፋ ከገባች ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ይወጣሉ በሚል ፍርሃት ነግሶ ቆይቷል።

ከአዘርባጃንም ሆነ ከአርሜኒያ ጋር ስምምነትና ወዳጅነት ያላት ሩሲያ እስከአሁን በጦርነቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ አላደረገችም።

አርሜኒያና አዘርባጃንን ለመሸምገል በርካታ ሙከራዎች በሩሲያ፥ በአሜሪካና በአውሮጳ አገራት ቢደረጉም አንዳቸውም አልተሳኩም።