ጃክ ማ 34 ቢሊዮን ዶላር ያጡበት ሳምንት

ያሳልፍነው ሳምንት ጃክ ማ በቻይና ታሪክ ሃብታሙ ሰው ሊያደርጋቸው ይችል ነበር። ነገር ግን ይህ አልሆነም።

የጃክ ማ ድርጅት የሆነው አንት ፋይናንሻል የአክሲዮን ገበያውን ይቀላቀላል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ይህ ድርጅት በሻንግሃይና በሆንግ ሆንግ የአክሲዮን ገበያዎች ላይ ውሎ 34 ቢሊዮን ዶላር በሚገመት ዋጋ ይሸጣል የሚል ዕቅድ ነበር።

ነገር ግን አክሲዮኑ ገበያ ላይ ሊውል ደቂቃዎች ሲቀሩት የቻይና ፋይናንስ ቁጥጥር ሰዎች አግደውታል።

ከዚህ አክሲዮን ገበያ የጃክ ማ ድርሻ 17 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሆነ ይነገራል። ይህ ደግሞ የሰውየውን ሃብት ወደ 80 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ያደርገው ነበር።

ተንታኞች የቻይና መንግሥት ይህን ያደረገው የጃክ ማ ሃብት ካሰቡት በላይ ስለሆነና ይህም የሰውየውን ኃያልነት ከፍ ስለሚያደርገው ነው ይላሉ።

ማ የቻይና መንግሥት ባለሥልጣናትን ነቅፎ ባለፈው ወር ሻንግሃይ ውስጥ በተካሄደ አንድ የቴክኖሎጂ ኮንፍረንስ ላይ አስተየት ሰጥተው ነበር።

ሃንግዡ ውስጥ በድህነት ያደጉት የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለመግባት ሁለት ጊዜ ተፈትነው ወድቀዋል። ብዙ ሥራ ለመቀጠር ሞክረው አልተሳካላቸውም። ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲን ለመቀላቀል 10 ጊዜ አመልክተዋል። አልፎም ኬአፍሲ ለተሰኘው የትኩስ ምግብ አቅራቢ ድርጅት ሠራተኛ ለመሆን አመልክተው ወድቀዋል።

ሰውዬው ብዙ ጥረዋል። ወጥተዋል ወርደዋል።

ማ፤ አሊባባ የተሰኘውን ድርጅት ያቋቋሙት በአውሮፓውያኑ 1999 ነው፤ ከጓደኞቻቸው ጋር ሆነ በተደበሩት 60 ሺህ ዶላር።

አሁን ከዓለማችን ልጥጥ ሃብታሞች አንዱ የሆኑት ማ ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር እሰጥ አገባ ሲገጥሙ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።

ነገር ግን የፋይናንስ ዘርፍ ተንታኞች፤ ማ የቻይና ባለሥልጣናትን ስለተናገሩ ብቻ አይደለም አንት ፋይናንሻል የተባለውን ድርጅት ይፋ ከማድረግ ያገዷቸው ይላሉ።

የጃክ ማ አዲስ ድርጅት ተበዳሪዎችን ከባንኮች ጋር ማገናኘት ነው ሥራው። የቻይና ባለሥልጣናት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሰል ድርጅቶች መበራከታቸው ስጋት ውስጥ ሳይከታቸው አይቀርም።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በርካታ ባንኮች ለችርቻሮ ነጋዴዎች በርካታ ገንዘብ እያበደሩ ነው ብሎ ዘግቧል።

ይህ ደግሞ በጊዜ ብዛት የቻይና ምጣኔ ሃብት ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ተሰግቷል።

የጃክ ማ ድርጅት አሁን ይከልከል እንጂ የቻይና ፋይናንስ ሕግን በማይጣረስ መልኩ በአዲስ ይዘት ሊመጣ ይችላል እየተባለ ነው።

ጃክ ማ ድርጅታቸው እንዳይከፈት ሲታገድ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮችን ቢያጡም እጁ ይሰጣሉ ተብሎ አይጠበቀም።