የአሜሪካ ምርጫ፡ ባይደን አሸንፈዋል፤ ቀጥሎ ምን ይሆናል?

ዲሞክራቱ ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት በመሆን ተመርጠዋል።

132 ክፍሎች እና 35 መጸዳጃ ቤት ወዳለው ዋይት ሃውስ የሚያደርጉት ጉዞም ተረጋግጧል።

በቀጣይ ምን ይሆናል? ትራምፕ ስልጣናቸውን አሳልፈው መቼ ይሰጣሉ?

ባይደን መንበረ ስልጣናቸውን የሚቀበሉት መቼ ነው?

በአሜሪካ ሕገ-መንግሥት መሠረት አዲሱ የፈረንጅ ዓመት በገባ በ20ኛ ቀኑ አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝነዳንት ስልጣኑን ይረከባል።

ይህም በዋሽንግተን ዲሲ በሚካሄድ ስነ-ስርዓት ይከናወናል። ፕሬዝደንቱ እና ምክትል ፕሬዝደንቷ ቃለ መሃል ይፈጽማሉ።

የምርጫ ውጤቱን ይፋ ከተደረገ በኋላ ተመራጩ ፕሬዝደንት ስልጣን እስከሚረከቡት ጊዜ ድረስ የሽግግር ቡድን ያቋቁማሉ።

ይህም ፕሬዝደንቱ ስልጣናቸውን በይፋ ከተረከቡ በኋላ ስራቸውን በፍጥነት እንዲጀምሩ ነገሮችን ቀላል ያደርጋል።

ከሰሞኑ በመገናኛ ብዙሃን የምንሰማቸው ቃላት

ባይደን ምርጫውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ በመገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ከምንሰማቸው ቃላት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

'ተመራጩ ፕሬዝዳት' (President-elect): ይህ ማለት እጩዉ ፕሬዝደንታዊ ምርጫውን አሸንፈዋል። ስልጣን ግን አልተረከቡም ማለት ነው። ጄነዋሪ 20 ላይ 'በዓለ ሲመት' ተብሎ በሚጠራው ስነ-ስርዓት ላይ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ፕሬዝደንት ተብለው ይጠራሉ።

ካቢኔ: ባይደን በቅርቡ የካቢኔ አባላቶቻቸውን ያሳውቃሉ። ይህም ከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣናት እና ኤጀንሲ መሪዎችን ያካተተ ይሆናል።

ሴልቲክ፡ ተመራጩ ፕሬዝደንት በአሜሪካው ሴክሬት ሰርቪስ (የደህንነት ጥበቃ የሚሰጠው አካል) ጥበቃ ይደረግላቸዋል። ጥበቃ ለሚያደረገው ቡድን ደግሞ ስያሜ ይሰጣል። ስያሜውን የሚሰጠው ተመራጩ ፕሬዝደንት ነው። ባይደን ለሴክሬት ሰርቪስ ቡድኑ "ሴልቲክ" የሚል ስያሜ ሰጥተዋል። ካማላ ሃሪስ በበኩኣለቸው 'ፓዮኒር' የሚል ስያሜን መርጠዋል።

ትራምፕ በቀጣይ ምን እንዲያደርጉ ይጠበቃሉ?

በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ተሸናፊው አሸናፊው ጋር ደውሎ እንኳን ደስ ያለህ/ያለሽ ማለቱ የተለመደ ነው። ትራምፕ ይህን ማደረግ ግዴታቸው አይደለም።

ይሁን እንጂ ትራምፕ የተመራጩ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ቡድን ወደ ስልጣን ለመምጣት በሚያደርገው ዝግጅት የሎጂስቲክ አቅርቦት እንዲደረግላቸው የመፍቀድ ግዴታ አለባቸው።