ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጆ ባይደን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ
ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ።
ባይደን የአሜሪካን 2020 ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ማሸነፋቸው የተረጋገጠው ፕሬዝደንታዊ ምርጫውን ለማሸነፍ 270 ኤሌክቶራል ድምጽ ማግኘታቸውን ተከትሎ ነው።
ጆ ባይደን ማናቸው?
ጆ ባይን የቀድሞ የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው አገልግለዋል።
ደጋፊዎቻቸው ባይደን የውጪ ጉዳይ ፖሊስ አዋቂ ናቸው ይሏቸዋል። በእርጋታቸው የሚታወቁት ፖለቲከኛ በግል ሕይወታቸው አሳዛኝ ክስተቶችን አሳልፈዋል።
ባይደን የፖለቲካ ሕይወታቸው የጀመረው ከ47 ዓመታት በፊት ነበር። የአሜሪካ ፕሬዝደንት ለመሆኑን ጥረት ማድረግ የጀመሩት ደግሞ ከ33 ዓመታት በፊት እአአ 1987 ላይ።
ባይደን በጥቁር አሜሪካውያን ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት አላቸው።
አሳዛኝ ክስተቶች
ባይደን ባለቤታቸውን እና ሴት ልጃቸውን በመኪና አደጋ በሞት ተነጥቀዋል።
ባይደን የመጀመሪያ የሴኔት ድላቸውን ተከትሎ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ባለቤታቸው የመኪና አደጋ አጋጥሟቸው ነበር።
ባለቤታቸው እና ሴት ልጃቸው ሕይወታቸው ሲልፍ ሃንተር እና ቤኡ የተባሉት ሁለት ወንድ ልጆቻቸው ላይ ጉዳት ደርሷል።
ቤኡ እአአ 2015 ላይ በአእምሮ ኢጢ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።
ስልጣን፣ ሙስና እና ውሸት?
በሕይወት ያለው ቀሪው ልጃቸው ሃንተር ጠበቃ ሆነ። ገንዘብ ህይወቱን ከቁጥጥር ውጪ አደረገበት።
ከዚያም ሃንተር ከባለቤቱ ጋር ተፋታ። በፍቺው ወረቀት ላይ የሃንተር የቀድሞ ባለቤት ሃንተር አልኮል እና አደንዛዥ እጽ እንደሚጠቀም እንዲሁም የምሽት መዝናኛ ክበቦችን እንደሚያዝወተር ገልጻለች።
ሃንተር በተደረገለት ምርመራ ኮኬይን በሰውነቱ ውስጥ በመገኘቱ ከአሜሪካ ጦር ባሃር ኃይል ተጠባባቂነት ተሰርዟል።
ከዛም ሃንተር ባለፈው ዓመት አንድ ሳምንት ብቻ ካወቃት ሴት ጋር ትዳር መስርቷል። ይህም የመገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።
የዩክሬኑ ጉዳይ
ሃንተር በዩክሬን ብዙ ገንዘብ የሚያስከፍል ስራ አግኝቶ ነበር።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ሃንተር በዩክሬን ሙስና ፈጽሟል በሚል በሃንተር ላይ ምርመራ እንዲደረግ የዩክሬን መንግሥት ላይ ጫና አሳደሩ ተባለ።
ፕሬዝደንት ትራምፕ የዩክሬኑ አቻቸው ዜሌኔስኪ ጋር ስልክ ደውለው የጆ ባይደን ልጅ ሙስና ለመፈጸሙ እንዲያጣሩ ቀጭን ትዕዛዝ ሰጥተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።
ጆ ባይደን በቁልፍ ጉዳዮዎች ላይ ያለቸው የፖሊስ አቋም
የአየር ንብረት ጉዳይ
ጆ ባይደን ነጩ ቤተ መንግሥት እንደገቡ ወዲያውኑ ወደ ፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት መልሰው ለመግባት ይሻሉ።
አሜሪካ በ2050 ዜሮ የካርበን ልቀት ላይ እንድትደርስ ይሰራሉ። 2 ትሪሊዮን ዶላር በአረንጓዴ ታዳሽ ኃይል ያወጣሉ። የነዳጅና ጋዝ ፍለጋ እንዲቆም ያደርጋሉ።
በምጣኔ ሀብት ጉዳይ
ባይደን ሀብታም ኩባንያዎች ላይ ግብር በመጫን ሕዝቡን የሚጠቅሙ ልማቶች ላይ አተኩራለሁ ይላሉ። ነገር ግን ግብር የምጭነው ገቢያቸው በዓመት 400 ሚሊዮን ዶላር በሚያገኙ ግዙፍ ኩባንያዎች ላይ ብቻ ነው ብለዋል።
በቀን ዜጎች የሚያገኙት ትንሹ የምንዳ ምጣኔ በሰዓት 15 ዶላር እንዲሆን አደርጋለሁ ብለዋል። አሁን ያለው ትንሹ በሰዓት የሚከፈለው 7.25 ዶላር ነው።
ጤና
ባይደን የኦባማ የጤና ሽፋን መድኅንን አስጠብቃለሁ ይላሉ።
በዕድሜ የገፉ ሰዎች የሚያገኙትን የጤና ትሩፋቶችን አስፋፋለሁ፤ ለዚህ ትሩፋት የሚያበቃውን ዕድሜም ከ65 ወደ 60 አወርደዋለሁ ብለዋል።
ሁሉም አሜሪካዊያን የኅብረተሰብ ጤና መድኅን የመመዝገብ ምርጫ እንዲኖራቸው አደርጋለሁ ሲሉ ቃል ገብተዋል።
የውጭ ፖሊሲ ጉዳይ
ጆ ባይደን ትራምፕ ያበላሹትን የውጭ ግንኙነት አስተካክላለሁ፤ አሜሪካ ያስቀየመቻቸውን ወዳጆቿን ልብ እጠግናለሁ ብለዋል። ከኢራንና ከቻይና ጋር የሚከተሉት ፖሊሲም ትራምፕ ጋር የሚቀረን ነው።
የጦር መሣሪያን በተመለከተ
ጆ ባይደን በጦር መሣሪያ ረገድ ቁጥጥር ማጥበቅ ይፈልጋሉ።
ለምሳሌ የገዢዎችን የኋላ ታሪክ ማጥናትና መመዝገብ፣ አንድ ዜጋ በወር መግዛት የሚችለው የመሣሪያ ብዛት አንድ ብቻ እንዲሆን ማድረግ፣ ቸልተኛ የመሣሪያ አምራቾችና ሻጮችን ተጠያቂ ማድረግ፣ ለዜጎች መሸጥ የሚችሉ የጦር መሣሪያ ዓይነትም በሕግ እንዲወሰን ማድረግ ይፈልጋሉ።