የአሜሪካ ምርጫ፡ የትራምፕ ክስ እና የባይደን የሰላም ጥሪ

ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዴሞክራቶች ምርጫውን ለማጭበርበር እየሞከሩ ነው ብለው ከሰዋል።

ተፎካካሪያቸው ጆ ባይደን ደግሞ ቆጠራው እየተካሄደ ስለሆነ ሰከን ማለት ያዋጣል ይላሉ።

ባይደን በኔቫዳ እና አሪዞና በጠባብ ውጤት እየመሩ ነው። በፔንስልቬንያ እና ጆርጅያ ደግሞ እየተከተሉ ነው።

ባይደን እስካሁን የ73 ሚሊዮን መራጮችን ድምጽ አግኝተዋል። ይህም በአሜሪካ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ታሪክ ትልቁ ነው።

ትራምፕ 70 ሚሊዮን የሚጠጋ ድምጽ መሰብሰብ ችለዋል።

ትራምፕ ምን አሉ?“

ሕጋዊ ድምጾች ከተቆጠሩ አሸንፋለሁ” ብለዋል። ነገር ግን ዴሞክራቶች ምርጫውን ለማጭበርበር እየሞከሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ትራምፕ ይህንን ክስ የሚሰነዝሩት ያለ ማስረጃ ነው። በቁልፍ የውድድር ግዛቶች በሰፊ ልዩነት እየመሩ እንደነበረና ከዛም “ሳይጠበቅ ቁጥሩ እንዳሽቆለቆለ” ይናገራሉ።

የትራምፕ ተቺዎች እንደሚሉት፤ ቁጥሩ የቀነሰው ከባይደን ደጋፊዎች አብዛኞቹ ድምጻቸውን በፖስታ ስለላኩ ነው።

ለወትሮው ትራምፕን የማይተቹ ሪፐብሊካኖች፤ የፕሬዘዳንቱን ንግግር ኮንነዋል።

ሚት ሮምኒ “ድምጹ ይቆጠራል። ሕግ ከተጣሰ ይጣራል። በዴሞክራሲያችን፣ በሕገ መንግሥታችን እና በሕዝባችን እምነት እናሳድር” ብለዋል።

የሜሪላንድ አገረ ገዢ ሌሪ ሆገን የፕሬዘዳንቱ ንግግር ዴሞክራሲን ያጣጣለ ነው ብለዋል።

ባይደን ምን አሉ?

ባይደን እንደሚያሸንፉ አምነው አገሪቱ እንድትረጋጋ ጥሪ አቅርበዋል።

“ዴሞክራሲ አንዳንዴ ትዕግስት ይጠይቃል። ትዕግስተኛነት ለ240 ዓመታት ጠቅሞናል። ዓለም የሚቀናበት ሥርዓት አለን” ሲሉም ተደምጠዋል።

ቆጠራው ሲጠናቀቅ ውጤቱ እንደሚታወቅ እና እስከዛ ግን ሕዝቡ መስከን እንደሚገባው ተናግረዋል።

ዋና ዋና በሚባሉ ከተሞች የሁለቱም ተወዳዳሪዎች ደጋፊዎች የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል።

በሌላ በኩል ድምጽ እየተቆጠረ ያለው ያለ ታዛቢ ነው የሚልና ሌላም ውንጀላ የሚሰነዝሩት ትራምፕ፤ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ደፍርድ ቤት እንደሚወስዱት ተናግረዋል።

ውድድሩ ምን ላይ ደርሷል?

የዊስኮንሰን፣ ፔንስልቬንያ፣ ኔቫዳ፣ አሪዞና፣ ጆርጅያ፣ ሚሺገን እና ኖርዝ ካሮላይና ውጤት ገና አልታወቀም።

ሆኖም ባይደን ሚሺገን እንዳሸነፉና ዊስኮንሰንን የማሸነፍ ሰፊ እድል እንዳላቸው ተነግሯል።

ባይደን እስካሁን 253 የኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጽ አግኝተዋል።

ትራምፕ ደግሞ 214።

ለማሸነፍ 270 ድምጽ ያስፈልጋል።

ባይደን በፔንስልቬንያ ወይም በተቀሩት ሁለት ግዛቶች ካሸነፉ ሊመረጡ ይችላሉ።ትራምፕ ደግሞ ፔንስልቬንያን እንዲሁም ተጨማሪ ሦስት ግዛቶች ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።

የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ክስ ለመመስረት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያሰባሰቡ ነው።

ድምጽ ቆጣሪዎች ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ታገሱ ብለዋል።

ፕሬዘዳንቱ ምን ብለው ከሰሱ?

ምርጫው ግልጽነት የለውም ያሉት ትራምፕ፤ የዊስኮንሰን ድምጽ በድጋሚ ይቆጠር ብለዋል።

በዚህ ግዛት ትፈምፕ ባይደንን በ20,000 ድምጽ እየመሩ ነበር።

ትራምፕ የሚሺገን እና ጆርጅያ ቆጠራ ላይም ቅሬታ አቅርበዋል።

ጆርጅያ ውስጥ 53 ዘግይተው የደረሱ ድምጾች ተቆጥረዋል ብለው ቢከሱም፤ ፍርድ ቤት ማስረጃ አላገኘሁም ብሏል።

ትራምፕ በፔንሰልቬንያ ያቀረቡት ክስ ተቀባይነት አግኝቶ፤ የሪፐብሊካን ታዛቢዎች ቆጠራውን በቅርበት እንዲከታተሉ እንዲፈቀድ ተወስኗል።

ዴሞክራቶች ይህንን ውሳኔ ጥሰው ሪፐብሊካን ታዛቢዎችን ከቆጠራው እንደተከላከሉ ተገልጿል።

የኔቫዳ የሪፐብሊካን ፓርቲ ክንፍ፤ ቢያንስ 3,062 ድምጾች ተጭበርብረዋል ሲል ለፍትሕ ሚንስቴር ቅሬታ አሰምቷል።

ግዛቱን የለቀቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ድምጽ እንደሰጡ ተነግሯል።

የትራምፕ አጋርና የቀድሞ የነቫዳ ዓቃቤ ሕግ አዳም ላክሴት “የሞቱ ሰዎች ድምጽም ተቆጥሯል” ብለዋል።

የባይደን የሕግ አማካሪዎች በበኩላቸው፤ ክሶቹ “መሠረተ ቢስ ናቸው” ብለዋል።