የአሜሪካ ምርጫ 2020፡ ባይደን እንደሚያሸንፉ ተነበዩ

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ክፉኛ በተመታችው አሜሪካ እስካሁን ባለው ከ99 ሚሊዮን አሜሪካውያን በላይ ቀድመው መምረጣቸው ተገልጿል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ማርክ ሚዶውስ በኮሮና ተያዙ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ማርክ ሚዶውስ የኮቪድ-19 ምርመራ አድርገው ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ባለስልጣናት ለአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ገለጹ፡፡

    የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ዝግጅቶች ላይ ብዙ ጊዜ የሚታዩት ሚዶውስ እንዴት ቫይረሱ እንደያዛቸው ግልጽ አልሆነም፡፡

    ኃላፊው በትራምፕ አስተዳደር ውስጥ ከሚሠሩ እና በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች መካከል አንደሱ ሲሆኑ በአሜሪካ 230,ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል፡፡

    አሜሪካ አርብ ከ127 ሺህ በላይ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ያስመዘገበች ሲሆን ይህም ለሦስተኛ ተከታታይ ቀናት ዕለታዊ ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቁልፍ ርዕስ የነበረ ሲሆን ሰዎች ድምጻቸውን በፖስታ እና ቀደም ብለው በአካል እንዲሰጡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

    ከቀናት በፊት ሚዶውስ ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አሜሪካ "ወረርሽኙን ለመቆጣጠር አትችልም" ያሉ ሲሆን ኮቪድ-19 ማሸነፍ የሚቻለው በክትባት እና ህክምና ብቻ እንደሆነ አስታውቀዋል።

  2. የአሜሪካ ምርጫ፡ ቆጠራው በቀጠለበት ምርጫ ባይደን እንደሚያሸንፉ ተንብየዋል

    የማክሰኞውን የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ ዶናልድ ትራምን ለማሸነፍ ከጫፍ የደረሱት ጆ ባይደን እንደሚያሸንፉ በመተማመን በድጋሚ ተናግረዋል ፡፡

    የዴሞክራቲክ ፓርቲው ዕጩ ኋይት ሐውስ ለመግባት ከሚያስፈልጉት 270 የኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምፆች 253ት ያህሉ አግኝተዋል፡፡

    በተጨማሪም ባይደን ወሳኝ ግዛቶች በሆኑት በጆርጂያ፣ ኔቫዳ፣ ፔንሲልቬንያ እና አሪዞና እየመሩ ነው፡፡

    የባይደን ድል ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከአራት ዓመት በኋላ በመጪው ጥር ስልጣናቸውን እንዲለቁ ያደርጋቸዋል፡፡

    ባይደን ምን አሉ?

    ባይደን አርብ ምሽት ዊልሚንግተን ደላዌር ለነበሩ ደጋፊዎቻቸው ሲናገሩ "ይህንን ውድድር እናሸንፋለን" ብለዋል፡፡ መድረኩ ላይ የባይደን ምክትል በመሆን የሚወዳደሩት የካሊፎርኒያ ሴናተር ካማላ ሃሪስ ተገኝተዋል፡፡

    ከ 300 በላይ የኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጾችን ለማሸነፍ በትክክለኛው መንገድ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል። በታሪክ ውስጥ ከማንኛውም የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ በላይ በምርጫ ከ74 ሚሊዮን በላይ በሆኑ ሰዎች ተመርጠዋል፡፡

    አሜሪካውያን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝንን፣ የተዳከመውን ኢኮኖሚ፣ የአየር ንብረት ለውጥን እና ዘረኝነትን እንዲዋጉ ስልጣን እንደተሰጣቸው ባይደን ተናግረዋል፡፡

    የሪፐብሊካኑን ዶናልድ ትራምፕን ያልጠቀሱት ባይደን "እኛ ተፎካካሪዎች ልንሆን እንችላለን ግን ጠላቶች አይደለንም እኛ አሜሪካውያን ነን" ብለዋል፡፡

    ባይደን የማሸነፊያ ንግግራቸውን እንደሚያቀርቡ የታቀደ ቢሆንም በምርጫው ውጤት ላይ የመገናኛ ብዙሃን አሸናፊ መሆናቸውን አለመጥቀሳቸውን ተከትሎ አጠቃላይ መረጃ ለመስጠት መርጠዋል።

  3. ባይደን በፔንሲልቬኒያ መምራት ጀመሩ

    ጆ ባይደን በፔንሲልቬኒያ መምራት ጀመሩ።

    ትራምፕ በሰፊ ልዩነት ሲመሩ በቆዩበት ፔንሲልቬኒያ ጆ ባይደን መሪነቱን ተቀብለዋል።

    ፔንሲልቬኒያ 20 ኤሌክቶራል ድምጽ ያላት ሲሆን በዚህ ግዛት ጆ ባይደን ድል የሚቀናቸው ከሆነ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን ማሸነፋቸው ይረጋገጣል።

    ባይደን እስካሁን የተረጋገጠ 253 ኤሌክቶራል ድምጽ አላቸው።

    ፕሬዝዳንት ሆኖ ለመመረጥ 270 ድምጽ ያስፈልጋል።

    • ትራምፕ በትዊተር ላይ ያላቸውን 'ልዩ መስተንግዶ' ሊያጡ ይችላሉ ተባለ

      ጆ ባይደን የዘንድሮውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚያሸንፉ ከሆነ ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ይሰጣቸው የነበረው ልዩ መስተንግዶ ይቋረጣል።

      ብሉምበርግ እንደዘገበው ምንም እንኳን ፕሬዝዳንቱ የትዊተር ህጎችን በተደጋጋሚ ቢጥሱም ምንም አይነት እርምጃ የማይወሰድባቸው እስከ ጥር ወር ድረስ ነው።

      ለሁለተኛ ጊዜ የማያሸንፉ ከሆነ ደግሞ ይህንን ልዩ መስተንግዶ ይገፈፋሉ።

      ትራምፕ በትዊተር የሚሰጣቸው ይህ ልዩ መስተንግዶ 'ወርልድ ሊደርስ ፖሊሲ'የሚባል ሲሆን የአገራት ፕሬዝዳንቶች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮችና ሌሎች ወሳኝ ሰዎች የሚሰጣቸው ነው።

      ትዊተር እነዚህ ሰዎች የፈለገ ነገር ቢያደርጉ ትልቅ የዜና ምንጮች ናቸው ብሎ ነው የሚያምነው።

      ለዚህም ነው ዶናልድ ትራምፕ በርካታ የትዊተር ሕጎችና ፖሊሲዎችን ሲጥሱ መልዕክታቸውን ሙሉ በሙሉ ከማጥፋት ይልቅ ከእሳቸው መልእክት ስር ማስጠንቀቂያ የሚያስቀምጠው።

      ነገር ግን ማስጠንቀቂያዎቹን አልፌ ማንበብ እፈልጋለሁ የሚል ሰው አሁንም መልዕክቶቹን ማየት ይችላል።

      ማንኛውም የትዊተር ተጠቃሚ የዚህ መስተንግዶ አካል አይደለም። እንደ ዶናልድ ትራምፕ ላሉ የዓለም መሪዎች ብቻ የተዘጋጀ አሰራር ነው።

      ምንም እንኳን ፕሬዝዳንቱ በርካታ አወዛጋቢና ያልተረጋገጡ መረጃዎችን በተደጋጋሚ በትዊተር ገጻቸው ቢያሰፍሩም ትዊተር ግን ሰውዬው 88 ሚሊዮን ተከታዮች ያሏቸው መሆኑና የአገር መሪ በመሆናቸው ምክንያት መልዕክታቸውን ሙሉ በሙሉ መደበቅ ተገቢ አይደለም ይላል

      ።ስለዚህ ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው የሚሸነፉ ከሆነ አንድ የአሜሪካ ዜጋ ብቻ ነው የሚሆኑት። በዚህም ቀድሞ ያገኙት የነበረው ልዩ መስተንግዶ ይቋረጥባቸዋል ማለት ነው።

    • ሰበር, ባይደን በጆርጂያ መሪነቱን ከትራምፕ ተቀበሉ

      ጆ ባይደን 16 ኤሌክቶራል ድምጽ ባላት ጆርጂያ መምራት ጀመሩ።

      ትራምፕ በጆርጂያ ሲመሩ ቢቆዩም፤ 99% በመቶ ድምጽ መቆጠሩን ተከትሎ መሪነቱን ለጆ ባይደን አሳልፈው ሰጥተዋል።

      ባይደን 253 የተረጋገጠ ኤሌክቶራል ድምጽ ያላቸው ሲሆን በጆርጂያ አሸናፊ መሆናቸው ከተረጋገጠ 269 ድምጽ ይኖራቸዋል ማለት ነው።

      ፕሬዝደንት ሆኖ ለመመረጥ 270 ኤሌክቶራል ድምጽ ያስፈልጋል።

      ይህ ውጤት የተመዘገበው 12፡55 ላይ ነው።

    • በኔቫዳ ባይደን እየመሩ ነው

      ዲሞክራቱ ጆ ባይደን 6 ኤሌክቶራል ድምጽ ባላት ኔቫዳ በ11ሺህ 438 ድምጽ እየመሩ ይገኛሉ።

      ይሁን እንጂ ትራምፕ በኔቫዳ የነበራቸውን ልዩነት እያጠበቡ ይገኛሉ።

      ባይደን 604ሺህ 251 (49.4%)

      ትራምፕ 592ሺህ 813 (48.5%)

      ልዩነታቸው 11ሺህ 438 ሲሆን 147ሺህ 951 ድምጽ ገና አልተቆጠረም።

    • የትራምፕ ልጆች ሪፐብሊካኖችን ‘አባታችንን አልደገፋችሁም’ ብለው ተቹ

      የፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁለት ልጆች ሪፐብሊካኖች አባታቸው ምርጫውን ለማሸነፍ የሚያደርጉትን ትግል እንዳልደገፉ ተናገሩ።

      የትራምፕ ትልቁ ልጅ ዶን ጁንየር [ትንሹ]፤ ፓርቲው “ደካማ ነው” ሲል፤ ኤሪክ ደግሞ “እንደ በግ መንጋ ከሆናችሁ መራጮች መቼም አይረሱትም” ብሏል።

      የትራምፕ ልጆች ፓርቲውን ማብጠልጠል የጀመሩት አባታቸው ከፓርቲው ጋር አለመጣጣም መጀመራቸውን ተከትሎ ነው።

    • ኖርዝ ካሮላይና

      ኖርዝ ካሮላይና 15 ኤሌክቶራል ድምጽ አላት።

      በዚህ ግዛት ትራምፕ በ76ሺህ 734 ድምጽ እየመሩ ይገኛሉ። ልዩነቱ ግን እየጠበበ ይገኛል።

      እስካሁን 95 በመቶ ድምጽ የተቆጠረ ሲሆን፤ ትራምፕ 50% ድምጽ ሲያገኙ ጆ ባይደን በበኩላቸው 48.6% ድምጽ በመቶ አስመዝግበዋል።

      የልተቆጠረው ድምጽ 283ሺህ 552 ነው።

    • ጆ ባይደን 'ጥበቃ እንዲጠናከርላቸው' ታዘዘ

      ጆ ባይደን በሚቀጥሉት ሰዓታት ምርጫውን በይፋ ያሸንፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

      ደህንነት ኃይሉ ለጆ ባይደንና ለቡድናቸው ተጨማሪ ጥበቃ እንደሚቀጥር ሰምቻለሁ ሲል ነው ጋዜጣው የዘገበው።

      ባይደን ምናልባት ከሰዓታት በኋላ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

      የደህንነት ክፍሉ በቃል አቀባይ ካትሪን ሚሎሃን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀው 'እኛ ለከፍተኛ አመራሮች ስለሚደረጉ ጥበቃዎች አስተያየት አንሰጥም' ብለዋል።

      የባይደን ረዳቶችም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

      ባይደን እና አጋሮቻቸው ዴልዌር ያለ አንድ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እንደሚገኙ ተነግሯል።

    • በሌላኛዋ ቁልፍ ግዛት ጆርጂያ

      16 ኤሌክቶራል ድምጽ ባላት ጆርጂያ ሁሉቱ እጩዎች እጅግ በጣም ተቀራራቢ ውጤት ላይ ይገኛሉ።

      ባይደን በዚህ ግዛት የነበራቸውን ልዩነት በከፍተኛ ሁኔታ ማጥበብ ችለዋል።

      ልዩነታቸው የ665 ድምጽ ብቻ ሆኗል።

      ያልተቆጠረው ድምጽ 1% ብቻ ነው።

      የዚህን ግዛት የመጨረሻ ውጤት በቅርቡ የምንሰማው ይሆናል።

      ይህ ውጤት የተመዘገበው ጥቅምት 27 4ሰዓት ከ50 ደቂቃ ላይ ነው

    • በቁልፍ ግዛቶች በእጩዎቹ መካከል ያለው ልዩነት

      ፔንሲልቬኒያ ውጤታቸውን ይፋ ካላደረጉ ግዛቶች ትልቁ ኤሌክቶራል ድምጽ ያላት ግዛት ናት።

      20 ኤሌክቶራል ድምጽ!

      ባይደን በዚህ ግዛት አሸነፉ ማለት ወደ ዋይት ሃውስ የሚያደርጉት ጉዞ የተረጋገጠ ይሆናል ማለት ነው።

      ለመሆኑ በዚህ ግዛት የድምጽ ቆጠራው ከምን ደርሷል? ልዩነታቸውስ?

      በፔንሲልቬኒያ እስካሁን 95 በመቶ ድምጽ ተቆጥሯል።

      በዚህ መሠረት ትራምፕ 3, 286,171 (49.5%) አግኝተዋል።

      ባይደን ደግሞ 3,267,942 (49.2%) አግኝተዋል።

      በሁለቱ እጩዎች መካከል ያለው ልዩነት 18ሺህ 229 ድምጽ ብቻ ነው።

      ያልተቆጠረው ድምጽ ደግሞ 344ሺህ 953 ነው።

    • የቀድሞው የትራምፕ አማካሪ ከትዊተር ታገዱ

      ትዊተር የተሰኘው ማሕበራዊ ድር አምባ የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ መልዕክቶች ላይ ማስጠንቀቂያ እያወጀ ነው።

      ይህ የሆነው ፕሬዝደንቱ ምርጫውን የተመለከቱ ያልተረጋገጡ ሃሳቦች መለጠፋቸውን ተከትሎ ነው።

      ዛሬ ደግሞ ትዊተር የቀድሞው የትራምፕ አማካሪ የሆኑት ስቲቭ ባነን ከድሩ እንዲታገዱ አድርጓል።

      አማካሪው በፌስቡክ፣ ዩቲዩብና ትዊተር ገፆቻቸው በለቀቁት መልዕክት አሜሪካዊው ከፍተኛ የጤና ባለሙያ ዶክተር አንተኒ ፋውቺና የኤፍቢአይ ኃላፊ ክሪስቶፈር ራይ "ጭንቅላታቸው ሊቀላ ይገባል" ሲሉ ተደምጠዋል።

      ፌስቡክና ዩቲዩብ ተንቀሳቃሽ ምስሉን ከገፆቻቸው አስወግደውታል።

      የትዊተር ቃል አቀባይ እንዳሉት አማካሪው የለጠፉት መልዕክት የድሩን ዓላማ የሚጥስ ነው። "በተለይ ደግሞ ግጭትን ማበረታት የሚለውን ክፍል ይነካል" ብለዋል።

      ዶ/ር ፋውቺና ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያቱ በተዳጋሚ በአደባባይ ተጋጭዋተዋል።

      ከምርጫው በፊት ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩት ትራምፕ ድጋሚ ከተመረጡ ባለ ሙያውን እንደሚያባርሯቸው ፍንጭ ሰጥተው ነበር።

      አሜሪካ በኮሮናቫይረስ በተያዙና በሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዓለም አንደኛ ናት።

    • የአሜሪካ ሴኔት ምርጫ ትንቅንቅ እስከ ጥር ሊቀጥል ይችላል

      በጆርጅያ ሁለተኛ ዙር ውድድር ሊደረግ ስለሚችል የአሜሪካ ሴኔት ምርጫ ትንቅንቅ እስከ ጥር እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።

      የትኛውም እጩ 50 በመቶ ድምጽ አላገኘም። ሕጉ ደግሞ 50% ድምጽ ያስፈልጋል ይላል።

      ሁለተኛው ዙር ውድድር ጥር 5 ሊካሄድ ይችላል።አሁን ላይ ሪፐብሊካኖች 53 ለ 47 በሆነ መቀመጫ የሴኔቱን የበላይነት ይዘዋል።

      ዴሞክራቶች አራት ድምጽ በማግኘት የበላይ ለመሆን ተስፋ ጥለዋል።

      በሪፐብሊካኖች ደጋፊነት በምትታወቀው ጆርጅያ ዴሞክራቶች ሁለቱንም ድምጽ ካገኙ ሴኔቱ እኩል 50-50 ይሆናል።

    • የትራምፕ ክስ እና የባይደን የሰላም ጥሪ

      ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዴሞክራቶች ምርጫውን ለማጭበርበር እየሞከሩ ነው ብለው ከሰዋል።

      ተፎካካሪያቸው ጆ ባይደን ደግሞ ቆጠራው እየተካሄደ ስለሆነ ሰከን ማለት ያዋጣል ይላሉ።

      ባይደን በኔቫዳ እና አሪዞና በጠባብ ውጤት እየመሩ ነው።

      ባይደን እስካሁን የ73 ሚሊዮን መራጮችን ድምጽ አግኝተዋል። ይህም በአሜሪካ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ታሪክ ትልቁ ነው።

      ትራምፕ 70 ሚሊዮን የሚጠጋ ድምጽ መሰብሰብ ችለዋል።

      ለመሆኑ ትራምና ባይደን ስለ ድምጽ ቆጠራው ምን አሉ? የትራምፕ ክስ እና የባይደን የሰላም ጥሪ

    • ባይደን መሪነታቸውን አጠናከሩ

      ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ያላቸውን ልዩነት አሰፉ።

      ጆ ባይደን 10 ኤሌክቶራል ድምጽ ባላት ዊስኮንሲን ማሸነፋቸው መረጋገጡን ተከትሎ ከትራምፕ ጋር ያላቸውን ልዩነት በ39 ኤሌክቶራል ድምጽ ማስፋት ችለዋል።

      ፕሬዝደንት ሆኖ ለመመረጥ 270 ድምጽ ያስፈልጋል።

    • የአሜሪካ ምርጫ፡ በወሳኝ ግዛቶች ምን እየተከናወነ ነው?

      አሁን የምርጫውን ውጤት የሚወስኑ ጥቂት ግዛቶች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ ባይደን 243 የኤሌክቶራል ኮሌጆች ድምጽ ሲኖራቸው ትራምፕ ደግሞ 214 አላቸው።

      ኋይት ሃውስ ለመግባት 270 ማግኘት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ቀሪዎቹ ወሳን ግዛቶች አሪዞና፣ ጆርጂያ፣ ኔቫዳ፣ ፔንሲልቬንያ፣ ሰሜን ካሮላይና እና ዊስኮንሲን ናቸው ፡፡ ወደ ድል የሚወስዱ የተለያዩ መንገዶች አሉ ፡፡

      270ን ቁጥር ለመድረስ ትራምፕ በዊስኮንሲን በአስር ድምፅ ተሸንፈው በጆርጂያ (16 ድምጽ)፣ በሰሜን ካሮላይና (15)፣ በፔንሲልቬንያ (20)፣ በአሪዞና (11) ወይም በኔቫዳ (6) ማሸነፍ አለባቸው ፡

      ፡ ባይደን በበኩላቸው ያለ ፔንሲልቬንያ (ውጤት በቅርቡ የማይጠበቅበት ነው) ሊያሸንፉ ይችላሉ። ሆኖም አሪዞና፣ ጆርጂያ እና ኔቫዳን ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል ፡፡

      አንዳንድ የዜና አውታሮች በዊስኮንሲን እና አሪዞና ባይደን አሸናፊ እንደሆኑ ቢገልጹም ቢቢሲ ግን ውጤቱን ለመግለጽ ገና መሆኑን በወኪሎቹ በኩል ለማረጋገጥ ችሏል፡፡ ባይደን ከዊስኮንሲን ጋር አሪዞና እና ኔቫዳ ላይ ብቻ በማሸነፍ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ፡፡ ቆጠራው እንደቀጠለ ሲሆን ባለሥልጣናቱ ውጤት በቀጣይ ሰዓታት ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡

    • የኔቫዳ ሪፐብሊካኖች በመራጮች ማጭበርበር ሊከሱ ነው

      በኔቫዳ የሪፐብሊካን ፓርቲ የመራጮች ድምፅ ተጭበርብሯል በሚል ሊከሱ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

      በመራጭነት ተመዝግበው ድምፃቸውን ከሰጡት መካከል 10 ሺህ ድምፅ በግዛቷ መኖር አቁመዋል ብሏል ፓርቲው።

      በርካቶች በፖስታ ከመረጡባቸው ግዛቶች መካከል አንዷ ኔቫዳ ናት።በፓስታ ድምፅ መስጠትን ሲቃወሙ የነበሩት ትራምፕ ቅስቀሳቸውም ላይ ወደ ማጭበርበር ይመራል በሚልም ሲናገሩ ተሰምተዋል።

      ምንም እንኳን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህንን ይበሉ እንጂ የመራጮች ድምፅ ተጭበርብሯል ለሚለው ምንም አይነት ማስረጃ አልተገኘም።

      ኔቫዳ የመራጮች ድምፅ ተጭበርብሯል በሚል ሪፐብሊካኖች ወደ ህጋዊ እርምጃ የሄዱባት አራተኛ ግዛት ሆናለች። በአምስተኛዋ ግዛት ዊስኮንሰንም እንደገና ድምፅ እንዲቆጠር እየጠየቁ ነው።

    • የተለያየ የምርጫ ውጤት የምንመለከተው ለምንድነው?

      በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተለያየ ምርጫ ውጤትን ተመልክተው ሊሆን ይችላል።

      ይህ ግራ ሊያጋባዎ አልያም ‘ይሄ የዘገየ ውጤት ነው’ ሊያስብልዎ ይችላል።

      በምርጫ ውጤቱ ላይ ልዩነቱ የተፈጠረው አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን በአሪዞና እና ዊስኮንስን ግዛት አሸናፊው ማን ሊሆን እንደሚችል አውቀናል ማለታቸውን ተከትሎ ነው።

      አንዳንድ የዜና ወኪሎች፤ 11 ኤሌክቶራል ድምጽ ባላት አሪዞና እና 10 ኤሌክቶራል ድምጽ ባላት ዊስኮንሲን ግዛት፤ ጆ ባይደን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ መገመታቸውን ተከትሎ በትራምፕ እና ባይደን መካከል ያለውን ልዩነት ከፍ አድርገውታል።

      በዚህም ምክንያት ባይደን 264 ለ 214 በሆነ ድምጽ እየመሩ ነው ይላሉ። ቢቢሲ ግን አሁንም በእነዚህ ግዛቶች ማን ሊያሸንፍ እንደሚችል መገመት አይቻልም ብሎ ያምናል።

      በዊስኮንሲን 99 በመቶ የሚሆነው ድምጽ ቢቆጠርም ሁለቱም እጩዎች እጅግ ተቀራራቢ ውጤት ነው ያላቸው።

      በአሪዞና ደግሞ 85 በመቶ ድምጽ ተቆጥሯል። ከተቆጠረው ድምጽ ባይደን 51 በመቶ የሚሆነውን ማግኘት ችለዋል። ትራምፕ ደግሞ 48 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል። ከቀሪው ድምጽ ትራምፕ ብዙ ድምጽ ማግኘት የሚችሉ ከሆነ ውጤቱ ሊቀየር ይችላል።

      በዚህም ምክንያት ቢቢሲ በእነዚህ ሁለት ግዛቶች አሸናፊውን ለመለየት ተጨማሪ ድምጾች ተቆጥረው ማለቅ አለባቸው ብሎ ያምናል።

      ዓለም የምርጫውን ውጤት በትዕግስት እየተጠባበቀ ነው። እኛም የተረጋገጠውን የምርጫ ውጤት እናደርሳችኋለን።

    • “ምርጫው ‘ተጭበርብሯል’ መባሉ የመራጩን እምነት ይሸረሽራል”

      ዓለም አቀፍ የታዛቢዎች ቡድን፤ ሕጋዊ ውዝግብ እና በሌሎችም ተያያዥ ድርጊቶች የመራጮችን እምነት እየሸረሸሩ ነው አለ።

      ኦርጋናይዜሽን ፎር ሰኪውሪቱ ኤንድ ኮፕሬሽን ኢን ዩሮፕ እንዳለው፤ የኮቪድ-19 ጫና እንዳለ ሆኖ ምርጫው “በፉክክር የተሞላ እና በአግባቡ የተመራ ነው” ብሏል።

      ሆኖም ግን ጽንፈኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ምርጫ አካሄድ ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ማድረጋቸውን ገልጿል። ይህም ያለ ማስረጃ “ምርጫው ተጭበርብሯል” ማለትን ያካትታል።

      ታዛቢ ቡድኑ “በተለይም ፕሬዘዳንቱ መሠረት አልባ ክሶች ማቅረባቸው ሕዝቡ በዴሞክራሲያዊ ሂደት ያለውን እምነት ያሳጣል” ብሏል።

      ከማክሰኞው ምርጫ በፊት በፖስታ ስለሚላክ ድምጽ፣ ድምጽ ተቀባይ ስለሚሆንበት ቀነ ገደብና ተያያዥ ጉዳዮች ከመቶ በላይ ክሶች ተከፍተዋል።

      ትራምፕ ምርጫው “የአሜሪካ ሕዝብ የተጭበረበረበት ነው” ብለዋል።

      በፔንስልቬንያ፣ ዊስኮን፣ ጆርጅያ እና ሚችጋን የድምጽ ቆጠራ እንዲቆም ይፈልጋሉ።

    • ባይደን በጠባብ ውጤት መምራታቸውን ተከትሎ ትራምፕ እከሳለሁ ብለዋል

      ትራምፕ ቁልፍ በሆኑት ዊስኮንሰን፣ ጆርጅያ፣ ፔንስልቬንያ እና ሚችገን ግዛቶች ድምጽ ቆጠራ ላይ ጥያቄ አለኝ ብለዋል።

      የቢቢሲ ጥቆማ ባይደን ሚችጋን ውስጥ እንዳሸነፉ ያሳያል። የአሜሪካ ሚዲያ ዘገባ ደግሞ ዊስኮንሰን ውስጥ አብላጫ ድምጽ እንዳገኙ ያሳያል።

      የፔንስልቬንያ ውጤት ገና አልታወቀም።

      በሦስቱ ግዛቶች ማሸነፍ ባይደንን ባለ ድል ያደርጋቸዋል።