የአሜሪካ ምርጫ፡ ባይደን በጠባብ ውጤት መምራታቸውን ተከትሎ ትራምፕ እከሳለሁ ብለዋል

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን በምርጫው አብላጫ ድምጽ እንዳገኙ እየተናገሩ ነው።

ትራምፕ ቁልፍ በሆኑት ዊስኮንሰን፣ ጆርጅያ፣ ፔንስልቬንያ እና ሚችገን ግዛቶች ድምጽ ቆጠራ ላይ ጥያቄ አለኝ ብለዋል።

የቢቢሲ ጥቆማ ባይደን ሚችጋን ውስጥ እንዳሸነፉ ያሳያል። የአሜሪካ ሚዲያ ዘገባ ደግሞ ዊስኮንሰን ውስጥ አብላጫ ድምጽ እንዳገኙ ያሳያል።

የፔንስልቬንያ ውጤት ገና አልታወቀም። በሦስቱ ግዛቶች ማሸነፍ ባይደንን ባለ ድል ያደርጋቸዋል።

ማክሰኞ ድምጽ ለመስጠት የወጡ ሰዎች ብዛት ባለፉት ዓመታት ከታየው በላይ ነው።

ባይደን የ70.5 ሚሊዮን መራጮችን ድምጽ ሲያገኙ፤ ትራምፕ ደግሞ የ67.2 ሚሊዮን መራጮች ድምጽ አግኝተዋል። ይህም እአአ 2016 ላይ ካገኙት በአራት ሚሊዮን ይበልጣል።

የምርጫ ቅስቀሳ ኮሚቴዎች ምን አሉ?

ትላንት ባይደን “የድምጽ ቆጠራው ሲያልቅ አሸናፊ እንሆናለን” ብለው ነበር።

ባይደን በፔንስልቬንያ የማሸነፍ እድል እንዳለ ጠቁመዋል።

የትራምፕ ቅስቀሳ ኮሚቴ ባልደረባ ጄሰን ሚለር “በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ትራምፕና ምክትላቸው ማይክ ፔንስ እንደሚመረጡ ታያላችሁ” ብለዋል።

ትራምፕ ሊያሸንፉ ይችላሉ?

ባይደን 270 የኢሌክቶራል ኮሌጅ ድምጾችን አግኝተው ዋይት ሀውስ የመግባት እድላቸው የሰፋ ሆኗል። ዴሞክራቶች 243 ድምጽ ሲያገኙ፤ ሪፐብሊካኖች 214 ድምጽ አግኝተዋል።

ትራምፕ ዊስኮንሲን (10 ኤሌክቶራል ኮሌጅ ድምጽ) ካጡ ጆርጂያ (16 ድምጽ)፣ ኖርዝ ካሮላይና (15 ድምጽ)፣ ፔንስልቬንያ (20 ድምጽ) ወይም አሪዞና(11 ድምጽ)፣ ነቫዳ (ስድስት ድምጽ) እና ፕሬቪልን ማሸነፍ አለባቸው።

በጆርጂያ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ 90,000 ድምጾች እንዳልተቆጠሩ እና ትራምፕ በ31,000 ድምጽ እየመሩ እንደሆነ ተገልጿል።

በአሪዞና ባይደን ደግሞ በ 80,000 ድምጽ እየመሩ መሆኑ ተገልጿል።

ተፎካካሪዎቹ ትንንቅ ላይ ያሉባት ነቫዳ ውጤት እስካሁን አልታወቀም።

የትራምፕ ክስ ምንድን ነው?

የትራምፕ አማካሪዎች እንደሚሉት፤ ፕሬዘዳንቱ “ሕገ ወጥ አሠራር ስላለ” የዊስኮንሲን ድምጽ በድጋሚ እንዲቆጠር ይጠይቃሉ።

ውጤቱ ሙሉ በሙሉ ገና ባይታወቅም፤ ትራምፕ እና ባይደን ከአንድ በመቶ የጠበበ ልዩነት ነው ያላቸው።

ይህም ተፎካካሪዎቹ ድምጹ በድጋሚ ይቆጠርልን እንዲሉ ያስችላል።

ትራምፕ ሚችጋን ውስጥ የድምጽ ቆጠራ ሂደቱን የሚከታተል አካል “ፍቃድ ተከልክሏል” ብለው ቆጠራው እንዲቆም ሲሉ ክስ መስርተዋል።

ትላንት በዲትሮይት፣ ሚችጋን ፖሊስ ድምጽ ቆጠራ ጣቢያን እንዲጠብቅ ተጠርቷል።

ተቃዋሚዎች ሂደቱን ገብተን እንመልከት ብለው ግርግር ተነስቶም ነበር።

የዲትሮይት መገናኛ ብዙኃን እንዳሉት ከሆነ፤ ወደ 200 ሰዎች ቆጠራውን ታዝበዋል።

ትራምፕ በፔንስልቬንያም “ግልጽነት እስከሚኖር” ድምጽ ቆጠራ ይቁም ብለው ሁለት ክስ መስርተዋል።

ሌላው ትራምፕ ክስ የመሰረቱበት ግዛት ጆርጅያ ነው። በግዛቱ የሪፐብሊካን ታዛቢ 53 ዘግይተው የደረሱ ድምጾች በሕገ ወጥ መንገድ ሲቆጠሩ ተመልክተዋል ተብሏል።

ትራምፕ እአአ 2016 ላይ ዊስኮንሰን፣ ሚችጋን እና ፔንሰልቬንያ አሸንፈው ነበር።

ትላንት ከዋይት ሀውስ በሰጡት መግለጫ፤ የምርጫውን ውጤት በተመለከተ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ክስ እንደሚያስገቡ መናገራቸው ይታወሳል።

የሪፐብሊካን የምርጫ ቅስቀሳ ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ቦብ ባውር እንዳሉት፤ ትራምፕ ሕጋዊ ድምጽ ቆጠራን ለማሻር ክስ የሚመሠርቱበት አግባብ የለም።