ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ሴኔት ምርጫ ትንቅንቅ እስከ ጥር ሊቀጥል ይችላል
በጆርጅያ ሁለተኛ ዙር ውድድር ሊደረግ ስለሚችል የአሜሪካ ሴኔት ምርጫ ትንቅንቅ እስከ ጥር እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።
የትኛውም እጩ 50 በመቶ ድምጽ አላገኘም። ሕጉ ደግሞ 50% ድምጽ ያስፈልጋል ይላል።
ሁለተኛው ዙር ውድድር ጥር 5 ሊካሄድ ይችላል።አሁን ላይ ሪፐብሊካኖች 53 ለ 47 በሆነ መቀመጫ የሴኔቱን የበላይነት ይዘዋል።
ዴሞክራቶች አራት ድምጽ በማግኘት የበላይ ለመሆን ተስፋ ጥለዋል።
በሪፐብሊካኖች ደጋፊነት በምትታወቀው ጆርጅያ ዴሞክራቶች ሁለቱንም ድምጽ ካገኙ ሴኔቱ እኩል 50-50 ይሆናል።
ከሴኔት ተወዳዳሪዎቹ አንዱና አሁንም በሴኔቱ መቀመጫ ያላቸው ሪፐብሊካን ዴቪድ ፕሩድ፤ ከ50 በመቶ በታች ድምጽ ነው ያገኙት።
ተፎካካሪያቸው ዴሞክራቱ ጆን ኦሶፍ እና የሊበሬሽን ፓርቲ ሼን ሀዝል ናቸው።
እስካሁን 98% ድምጽ ተቆጥሯል።
የዴቪድ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን መሪ ቤን ፌይ እንደሚያሸንፉ ተናግረዋል። የጆን ኦሶፍ ቡድን ሁለተኛ ዙር ውድድር ሲካሄድ ባለ ድል እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
በጆርጅያ ሌሎቹ የሴኔት ተወዳዳሪዎች ማለትም ዴሞክራቱ ራፋኤል ዋርኖክ 32.8% አግኝተዋል።
በሁለተኛው ዙር 26% ካገኙት ሪፐብሊካን ኬሊ ሎፈር ጋር ይወዳደራሉ።
ለውድድር ከቀረቡት 35 መቀመጫዎች 23ቱ በሪፐብሊካኖች፤ 12ቱ በዴሞክራቶች የተያዘ ነው።
ዴሞክራቶች ብዙ መቀመጫ ለማግኘት ቢጠብቁም፤ ከኮልዶናዶ ሁለት ወንበር አንዱን ብቻ ነው ያገኙት።
በሌላ በኩል ለዘብተኛ ሪፐብሊካኗ ሱዛን ኮለንስ ከዴሞክራቷ ሳራ ጊዶን ጋር ከፍተኛ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።
ዴሞክራቶች ላለፉት ስድስት ዓመታት ሴኔቱን መቆጣጠር አልቻሉም።