ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ምርጫ፡ በወሳኝ ግዛቶች ምን እየተከናወነ ነው?
አሁን የምርጫውን ውጤት የሚወስኑ ጥቂት ግዛቶች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡
ባይደን 243 የኤሌክቶራል ኮሌጆች ድምጽ ሲኖራቸው ትራምፕ ደግሞ 214 አላቸው።
ኋይት ሃውስ ለመግባት 270 ማግኘት ያስፈልጋቸዋል፡፡
ቀሪዎቹ ወሳን ግዛቶች አሪዞና፣ ጆርጂያ፣ ኔቫዳ፣ ፔንሲልቬንያ፣ ሰሜን ካሮላይና እና ዊስኮንሲን ናቸው ፡፡
ወደ ድል የሚወስዱ የተለያዩ መንገዶች አሉ ፡፡
270ን ቁጥር ለመድረስ ትራምፕ በዊስኮንሲን በአስር ድምፅ ተሸንፈው በጆርጂያ (16 ድምጽ)፣ በሰሜን ካሮላይና (15)፣ በፔንሲልቬንያ (20)፣ በአሪዞና (11) ወይም በኔቫዳ (6) ማሸነፍ አለባቸው ፡፡
ባይደን በበኩላቸው ያለ ፔንሲልቬንያ (ውጤት በቅርቡ የማይጠበቅበት ነው) ሊያሸንፉ ይችላሉ።
ሆኖም አሪዞና፣ ጆርጂያ እና ኔቫዳን ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል ፡፡
አንዳንድ የዜና አውታሮች በዊስኮንሲን እና አሪዞና ባይደን አሸናፊ እንደሆኑ ቢገልጹም ቢቢሲ ግን ውጤቱን ለመግለጽ ገና መሆኑን በወኪሎቹ በኩል ለማረጋገጥ ችሏል፡፡
ባይደን ከዊስኮንሲን ጋር አሪዞና እና ኔቫዳ ላይ ብቻ በማሸነፍ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ፡፡
ቆጠራው እንደቀጠለ ሲሆን ባለሥልጣናቱ ውጤት በቀጣይ ሰዓታት ያሳውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል ፡፡
ሁሉም ድምፆች እስኪቆጠሩ ድረስ ሌሊቱን በሙሉ ቆጠራቸውን እንደሚቀጥሉ የጆርጂያ ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡
በግዛቱ የትራምፕ መሪነት ወደ 24,000 ድምፆች ቀስ እያለ እየቀነሰ ነው ሲል ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
በኔቫዳ የድምጽ ልዩዩቱ ጠባብ ሲሆን ባይደን ከ8000 ባነሰ ድምፅ ይመራሉ፡፡ ቀጣይ ውጤቶች ሐሙስ ከሰዓት በኋላ እንደሚለጠፉ ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል፡፡
በፔንሲልቬንያ በሰፊ ልዩነት ሲመሩ የነበሩት ትራምፕ አሁን ልዩነታቸው ጠቧል። 90 በመቶ ድምጾች ተቆጥረው ትራምፕ በ164 ሺህ 414 ድምፅ ይመራሉ፡፡
ባይደን በአሪዞና በ80,000 ያህል ድምጽ እየመሩ ሲሆን ተጨማሪ ውጤቶች ሐሙስ ይጠበቃሉ።
በሰሜን ካሮላይና አብዛኛው ድምጽ የተቆጠረ ሲሆን ትራምፕ 77 ሺህ በሚጠጋ ጠባብ ድምጽ በመምራት ላይ ይገኛሉ።
ጆ ባይደን ከ 20 ሺህ በላይ ድምጽ እየመሩ ነው በሚባልበት ዊስኮንሲን አጋራችን ሮይተርስ አሸናፊነቱን ያልሰጣቸው ሲሆን ሌሎች የዜና አውታሮች ግን ባይደን በግዛቱ እንዳሸነፉ እየዘገቡ ነው።