ትግራይ፡ ዶ/ር ደብረጺዮን ጦርነት ቆሞ ድርድር እንዲካሄድ መጠየቃቸው ተሰማ

የፌደራል መንግሥት ከአማራ ክልል ጋር በመሆን ከትግራይ ክልል ኃይሎች ጋር ወደ ግልጽ ጦርነት ከገቡት ስድስት ቀናት አልፈዋል።

ባለፉት ሁለት ቀናት አዳዲስ ነገሮች ተሰምተዋል። ከእነዚህም መካከል የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት ደብረጸዮን (ዶ/ር) ድርድር እንዲካሄድ መጠየቃቸው አንዱ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ቢያንስ በ8 ቦታዎች ጦርነቶች እየተካሄዱ ይገኛል ብሏል።

የድርድር ጥያቄ

የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጦርነቱ ቆሞ ድርድር እንዲካሄድ መጠየቃቸው ተሰምቷል።

ደብረጺዮን (ዶ/ር) የአፍሪካ ሕብረት በፌደራል እና ትግራይ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ጦርነቱን እንዲያስቆም እና ከእርስ በእርስ ጦርነት አገሪቷን እንዲታደግ ጠይቀዋል።

የክልሉ ፕሬዝደንት ለወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር እና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት በጻፉት ደብዳቤ ሁሉን አካታች የሆነ ውይይት እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

ደብረጺዮን (ዶ/ር) በደብዳቤያቸው "ፖለቲካዊ ችግሮች በወታደራዊ አማራጮች እንደማይፈቱ ጽኑ እምነት አለኝ" ብለዋል።

በተመሳሳይ ሮይተርስ የዜና ወኪል ደብረጺዮን (ዶ/ር) ጦርነቱ ቆሞ ድርድር እንዲደረግ መጠየቃቸውን ትናንት ምሽት አስነብቧል።

ይህ ይሁን እንጂ በፌደራል መንግሥቱ በኩል ለድርድር ፍላጎት ያለ አይመስልም። ጠቅላይ ሚንስትሩ ትናንት ለውጪ ማህብረሰቡ በእንግሊዘኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር መንግሥት የጀመረውን እርምጃ ያጠናቅቃል ብለዋል።

ከሁለት ቀናት በፊትም ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በትዊተር ገጻቸው ላይም "ወንጀለኛ አካላት ዕርቅ እና ድርድር ፈላጊ በመምሰል ከሕግ የበላይነት ሊያመልጡ አይችሉም። የሚከናወነው ኦፕሬሽን ዓላማው፣ የሚገባቸውን ቅጣት ሳያገኙ ከገደብ አልፈው የቆዩትን አጥፊ ግለሰቦች እና ቡድኖች በሀገራችን ሕግጋት መሠረት ተጠያቂ ማድረግ ነው" ብለው ነበር።

የተመድ መግለጫ

የተባበሩት መንግሥት ድርጅት በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ቢያንስ በ8 ቦታዎች ጦርነቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ ብሏል።

ተመድ ከዚህ ጦርነት ጋር በተያያዘ እስከ 9 ሚሊዮን ሕዝብ ሊፈናቀል ይችላል ሲል አስጠንቅቋል። የተባበሩት መንግሥት ወደ ትግራይ የሚወስዱ መንገዶች በሙሉ ዝግ መሆናቸውን እንዲሁም የኮሚኒኬሽን አገልግሎት በመቋረጣቸው የእርዳታ ቁሳ ቁሶች የሚደርሱበት አማራጭ የለም ብሏል።

ድርጅቱ በጦርነቱ በርካቶች መገደላቸውን እና በርካታ የአየር ጥቃቶች ስለመፈጸማቸው ሪፖርት ደርሶናል ብሏል።

መከላከያ ድል አደረኩ ስለማለቱ

የአገር መከላከያ ኢንዶክትሬኔሽን እና የሕዝብ ግነኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል መሐመድ ተሰማ ለአገር መገናኛ ብዙሃን ባለፉት ቀናት በምዕራብ ትግራይ በኩል በተደረገው ጦርነት መከላከያ ሠራዊት ድል እያደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ሜ/ጀነራል መሐመድ ትናንት በሰጡት መግለጫ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኙትን እንደ ማይዳሉ፣ ዳንሻ፣ ባአካር፣ ሉግዲ በቁጥጥር ሥር አውለናል ብለዋል። ሜ/ጀነራሉ ጨምረውም፤ ቅራቅር እና ጸገዴ ወረዳን እንዲሁም ዳንሻ አከባቢ የሚገኘውን አውሮፕላን ማረፊያ ተቆጣጥረናል ብለዋል።

በትግራይ የሚገኙ ባንኮች መዘጋት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ "ሕወሓት በትግራይ ክልል የሚገኙ የባንክ ቅርንጫፎች ላይ ዘረፋ እየፈፀመ ነው" በሚል በክልሉ የሚገኙ ሁሉም የባንክ ቅርጫፎች እንዲዘጉ ወስኗል።

ብሔራዊ ባንክ በተለያዩ ባንኮች ውስጥ ያለው ገንዘብ ደህንነቱ አደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኛል ያለ ሲሆን በትግራይ ክልል 616 የባንክ ቅርንጫፎች አሁን ባለው ሁኔታ በክልሉ የሚገኙ ባንኮች አገልግሎት መስጠት ስለማይችሉ ተዘግተው እንዲቆዩ ተወስኗል ብሏል።

'ተዋጊ ጄት መትተን ጥለናል'

የሕውሃት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ በድምጸ ወያኔ ቴሌቪዥን ቀርበው በምዕራብ ትግራይ ከባድ ጦርነት እየተካሄደ ነው ብለዋል።

አቶ ጌታቸው በአፋር ክልል እና በራያ በኩል የፌደራል መንግሥቱ ተጨማሪ ኃይል በማሰማራት ጦርነት ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በምዕራብ ትግራይ በኩል መከላከያ ሠራዊት ድል አደረኩ ማለቱ እውነት አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል።

አቶ ጌታቸው የፌደራሉ መንግሥት ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረው፤ ትናንት እሁድ አንድ ተዋጊ ጄት ተመትቶ ወድቋል ብለዋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ግን ይህ ሃሰት ነው ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተናግረዋል።

ሜጀር ጄኔራል መሐመድ አየር ኃይሉ አሁንም ቢሆን የተመረጡ ቦታዎችን ማጥቃቱን አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።