በትግራይ ክልል የተወሰደው እርምጃ በስኬት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ

ከሶስት ቀናት በፊት በፌደራል መንግሥት ትግራይ ላይ የተጀመረው እርምጃ በስኬት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው በሰጡት መግለጫ ህወሃት በትግራይ የሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ያደረሰው ጥቃት ድንገተኛ መሆኑን ገልፀው የመጀመሪያው ዙር ዘመቻ ብለው የጠሩት የሃይል እርምጃ ሙሉ ለሙሉ ተሳክቷል ብለዋል።

የፌደራል መንግሥቱ የተለያዩ እቅዶችን ይዞ እንደተነሳ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመጀመሪያም ጥቃትን መግታት እንደነበር አስረድተዋል።

"በሰራዊቱ፣ በፖሊስ ላይና በአንዳንድ ወሳኝ የመሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰውን በሁሉም አቅጣጫ የሚሰነዘር ጥቃት መግታት ተችሏል" ብለዋል።

የክልሉ ኃይል ጥቃት የሚሰነዝርባቸው አካባቢዎች የመከላከያ ኃይሉ በብዛት ያልሰፈረበት እንደነበር ገልፀው የሰራዊቱ አባላትንም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማንቀሳቀስ ጥቃት መሰንዘር ወደማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በባድመ፣ በፆረና እና በዛላንበሳ የሚገኙ የሰራዊት አባላት፣ ወሳኝ የጦር መሳሪያዎችን እና ትጥቆች በሙሉም "ከክልሉ ኃይል ውጭ መደረጋቸውንም" ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በዳንሻ ግንባር ላይ የነበረውን የክልሉን ጦር ሙሉ በሙሉ ተደምስሶ አካባቢው መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል።

የአማራን ክልል በሚያዋስነው የምዕራብ ትግራይ ድንበር በኩል ግጭቶች እንዳሉና ውጊያው መቀጠሉን የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በትናንትናው እለት ገልፀዋል።

ደብረፅዮን (ዶ/ር) ውጊያው የአማራ ክልል በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ ቀጥሏል ከማለታቸው ውጭ የትኛው ግዛት (ግዛቶች) እንደሆኑ አልጠቀሱም።

የአማራ ልዩ ኃይልና የፌደራል ሰራዊቱ በጥምረት በመሆን የትግራይ ኃይል ጋር መዋጋታቸውን ተናግረዋል።

የትግራይ ኃይል በክልሉ የሚገኙትን የመከላከያ ሰሜን ዕዝ ጦር መሳሪያም ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር አውሏል ብለዋል።