ኢትዮጵያን ያገለለው በግብፅ እና በሳዑዲ የሚመራው የቀይ ባሕር መድረክ ዓላማው ምንድን ነው?

አገራት በየቀጠናቸው ለተለያየ ዓላማ ይቧደናሉ።

አንዳንዴ ንግድን ለማሳለጥ፤ ሌላ ጊዜ ምጣኔ ሃብታቸው ለማፈርጠም።

አንዳንዴ ሰላም እና ደኅንነት ሲያሰጋቸው፣ ሌላ ጊዜ የጋራ ጠላት ሲያስበረግጋቸው።

ኔቶ ራቅ አለ እንጂ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ለነገሩ በዚህ ዘመን ሩቅ የሚባል ነገር አለ?

የሶቭየት ኅብረት የወረራ ፍርሃት የዛሬ 70 ዓመት የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶን ወደለ።

ሶቭየት ኅብረት የቅርጫ ያህል ፈራርሳ 15 አገራትን ወለደች፡፡

ኔቶ ግን ጸና እንጂ አልፈረሰም።

እንዲያውም እየጎመራ መጣ። 12 አገራት መሥርተውት፣ አሁን 30 ደረሰ።

በአጭሩ ኔቶ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ተወልዶ በሦስተኛው የዓለም ጦርነት የስጋት ደጅ ላይ ቆሟል።

ዓላማ አና ተግባራቸው፣ ሥሪትና ተልዕኳቸው ይለያይ እንጂ በምዕራባዊ አፍሪካ "ኢኮዋስ"፣ በአፍሪካ ቀንድ ደግሞ 'ንቁ አይደለም' የሚባለው ኢጋድ ይገኛሉ።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ብቅ ያለው ኅብረት መነጋገሪያ ሆኗል። የቀይ ባሕር የትብብር መድረክ ይሰኛል። ኢትዮጵያን ያሰጋታል? ስለሱ እናውራ።

የቀይ ባሕር የትብብር መድረክ የማን ነው?

የዚህ መድረክ መሥራች አባቶች ሁለት ናቸው። ግብፅ እና ሳዑዲ አረቢያ። ከእነርሱ ሌላ አበዛኞቹ የኢተዮጵያ ጎረቤት የሆኑ 6 አባል አገራት አሉ።

ጎረቤት ኤርትራ፣ ጎረቤት ሱዳን፣ ጎረቤት ሶማሊያ፣ ጎረቤት ጂቡቲ፣ ዮርዳኖስ እና የመን።

የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እና የአፍሪካ ቀንድ ተፈጥሮ አጎራብቷቸዋል። ከቀይ ባሕር ማዶ ለማዶ ይተያያሉ።

እርግጥ ነው ይህ ቀጠና የማንንም ብልጹግ አገርን ቀልብ ወከክ የሚያደርግ ነው። ለምን ከተባለ በዚህ አካባቢ ቅልጥ ያለ የንግድ እንቅስቃሴ ይካሄዳል።

ዶላር በውሃ አካል የሚንሳፈፍበት ቦታ ነው።

በዓለም ላይ ከባድ የባሕር ትራንስፖርት የትራፊክ መጨናነቅ አለበት የሚባል ቦታ ነው።

እሲያ፣ መካከለኛው ምሥራቅ አና አውሮፓ ሄደው ሄደው የሚገጥሙበት ቦታ ነው።

በሜዲትራኒያን፣ ሱዩዝ ካናልን፣ ቀይ ባሕርን ዘልቆ ሕንድ ውቅያኖስ መድረስ የሚቻልበት ብቸኛ መስመር ነው።

ታዲያ በዚህ ቁልፍ ቀጠና ኃያልነቱን ማሳየት የማይሻ ኃያል አገር ከየት ይኖራል?

ለዚህ አንድ ማሳያ ጂቡቲን ናሙና አድርገን እንውሰድ።

የመዳፍ ያህል ከምትሰፋው ጂቡቲ ኩርማን መሬቷ ላይ እነማን ከትመዋል የሚለውን ማየት ብቻ ብዙ ይነግረናል።

ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ጃፓን እና ቻይና አሉ። ሕንድ እና ሩሲያም አገራቸውን ለማስገባት እየጣሩ ነው።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኳታር፣ ቱርክ አና ኢራን በቀጣናው ባሉ ወዳጆቻቸወ በኩል ቦታቸውን ይዘዋል፤ ሌሎችም እየቋመጡ ነው።

ተፈጥሮ በቀይ ባሕር ሰፈር ያስቀመጠቻቸው አገራት ብቻ ሳይሆኑ ራቅ ያሉትም ቢሆን የንግድ መርከባቸው በዚህ ማለፉ ስለማይቀር የአካባቢው ሰላም እና ፀጥታ ልክ እንደ ደጃቸው ያሳስባቸዋል።

የቀይ ባሕር ደቡባዊ በር፣ ባብ ኤል ማንደብ፣ አንዳች እክል ቢገጥመው የብዙ አገሮች ጉሮሮ ላይ አጥንት የመሰንቀር ያህል ከባድ ነው።

ለዚህም የጋዛን ጦርነትን ተከትሎ የኢራን ወዳጅ የሆነው የየመን ሁቲ የምዕራባውያን መርከቦችን ዒላማ ሲያደርግ የተከሰተው ቀውስ ይታወሳል።

በምላሹም በአሜሪካ አዝማችነት በአካባቢው የምዕራባውያን የባሕር እና የአየር ኃይል እንዲሰማራ መደረጉ የቀይ ባሕር ነገር ሁሉንም እንቅልፍ የሚነሳ መሆኑን ያሳያለ።

የሩቅ ኃያል አገራት በአካባቢው የሚያሳዩትን የቅርምት ፍላጎት በማገናዘብ ይመስላል የቀይ ባሕር ኩታ ገጠም አገራት ከአውእሮፓውያኑ 2018 ጀምሮ በጋራ ለመቆም በማሰብ የጀመሩት።

ነገሩ ከላይ ከላዩ ሲታይ ከሩቅ የሚመጣን ጉልበተኛ አብሮ ለመመከት ያለመ ይመስላል።

ምክክሩ እየጎለበተ መጥቶ በ2019 ቅርጽ እየያዘ መጣ። በ2020 ደግሞ ተመሠረተ።

ለጋራ ጥቅምም፣ ለጋራ ስጋትም ሰብሰብ ብንል ነው የሚሻለው በሚል ከሁለት ዓመት በፊት ጉባኤ ተቀመጠው የቀይ ባሕር የትብብር መድረክን ስምንቱ አገራት መሠረቱ።

አቶ ነአምን አሸናፊ የአፍሪካ እና ኦሪየንታል ጥናት ዘርፍ ተመራማሪ ናቸው።

እሳቸው ይህ መድረክ በሳዑዲ እና በግብፅ ጽኑ ፍላጎት እንጂ በአባል አገራት ሙሉ ፍቃድ የተመሠረተ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል።

ለዚህ የሚያነሱት አንዱ ምክንያት ቀሪ አባላቱ ያላቸው አሁናዊ ቁመና ነው።

"ከግብፅ ውጪ አብዛኞቹ አገራት በራሳቸው ለመቆም የሚችሉ አይደሉም፤ ይልቅ ሳዑዲን የማጀብ ሚና ነው ያላቸው" ይላሉ።

ይህን ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? ቆየት ብለው ያስረዱናል፤ አሁን አንድ ጥያቄ እናንሳ።

መድረኩ ኢትዮጵያን ለምን አገለለ? ብለን እንጠይቅ። ይህ ጥያቄ የእኛ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ በሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤትም የነሳው ጥያቄ ነበር።

የግብፅ ኢትዮጵያን የማግለል አሻጥር ይሆን?

አሁን ባለው ሁኔታ ቀይ ባሕርን በቀጥታ ባይዋሰኑም ከቅርበት እና ካላቸው ብሔራዊ ጥቅም አንጻር በባሕሩ ዙሪያ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው አገራት አሉ።

በዚህ መድረክ ላይ ሁለት ቁልፍ አገራት ገሸሽ ተደርገዋል። እንዲያውም ሦስት አገሮች። እስራኤል፣ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እና ኢትዮጵያ፤ ለምን?

ኢትዮጵያስ ለምን የበዛ ቅሬታ ገባት?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሦስት ዓመታት በፊት በተወካዮች ምክር ቤት በቀረቡ ጊዜ ዶ/ር ቶፊቅ አብዱላሒ ከተባሉ እንደራሴ ተያያዥ ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር።

"ቀይ ባሕር ለእኛ ብቸኛው መግቢያ መውጫችን ነው። ሳዑዲ እና ግብፅ ሆን ብለው ሲያገሉን እኛስ ምን እያደረግን ነው?" የሚል ጥያቄ አንስተው ነበር።

እንደራሴው ዶ/ር ቶፊቅ ጥያቄያቸውን ሲያጠናክሩ፣ ከስምንቱ አባል አገራት አራቱ የኢጋድ አባላት ሆነው እንዴት ይህን አግላይነት ማስቆም አቃተን? ብለዋቸው ነበር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቅል የሆነ እና ተስፋን ያዘለ ምላሽ ሰጥተው ነበር።

"ወፏ የተሰበረ ቅርንጫፍ ላይ የምታርፈው ዛፉን ተማምና አይደለም፤ የምትበርበትን ክንፍ ተማምና ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ ቀይ ባሕር ትላለች፤ አትጠራጠሩ ከ10፣ ከ15 ዓመት በኋላ በሌሎች ራቅ ባሉ አገራትም ጥቅም አለኝ ትላለች።…የእኛ ተጽእኖ እዚች የቀይ ባሕር ሰፈር የሚቀር አይመስለኝም።"

ምላሻቸው በተጨባጭ በዲፕሎማሲ ምን እየተሠራ እንደሆነ ምንም ፍንጭ የሚሰጥ አልነበረም።

አቶ ነአምን የኢትዮጵያን ገሸሽ መደረግ ከግብፅ ጋር ሊተሳሰር የሚችልበትን ሰበዝ መዘው ያወጣሉ።

"ውስጡ ሲፈተሸ ጠንሳሾቹ እነማን ናቸው? ብሎ መጠየቅ ግማሽ ምላሽን ይሰጣል" የሚሉት የቀጠናው ተንታኝ፣ ከጠንሳሾቹ መካከል ግብፅ ዋንኛዋ ናት።

ይህን ሐሳብ በአውሮፓውያኑ 2018 ከነበረበት ያንቀሳቀሰችው ደግሞ ግብፅ ናት። ግብፅ በማንኛውም መድረክ ኢትዮጵያን ከዲፕሎማሲ እና ከኢኮኖሚያዊ ከባቢ ማራቅ ነው የምትሻው" ይላሉ።

ለዚህም ከሌሎቹ የስብስቡ አባላት በተለየ ግብፅ በቀይ ባሕር ጉዳይ ውስጥ ፈጽሞ ቦታ እንደማይኖራት በይፋ እየተናገሩ ነው።

ቀሪዎቹ ስድስት አባል አገራት ደካማ የሚባሉ ከመሆናቸው አንጻር ከሳዑዲ ጋር ትከሻ ለትከሻ መታከክ የምትችለው ግብፅ በዚህ መድረክ ሚናዋ የጎላ እንደሚሆን አይጠረጠርም።

"ከአባል አገሮቹ አንጻር ከሳዑዲ ቀጥሎ አጀንዳዋን ማስፈጸም የምትችለዋ ብቸኛ አገር ግብፅ ትሆናለች። ግብፅ ደግሞ ኢትዮጵያን የማግለል አጀንዳዋ የሚታወቅ ነው" ይላሉ አቶ ነአምን።

ኢትዮጵያ እና ግብፅ የዓባይን ጉዳይ ተከትሎ በርካታ ተቃርኖ ውስጥ ያሉ ሆነው አንድ መድረክ ሊጋሩ የሚችሉበት ዕድል በሐሳብ ደረጃ ተነስቶ ከነበረም ልታከሽፈው የምትችለው ግብፅ አንጂ ሌላ አይሆንም።

የሕዝብ እንደራሴው ዶ/ር ቶፊቅ እንዳነሱት ከአባል አገራት አራቱ የኢጋድ አባል ሆነው፤ ኢትዮጵያ በኢጋድ ውስጥ እጇ ረዥም ሆኖ በዚያ በኩል በር ለማንኳኳት እንዴት እንዳልተሞከረም ግልጽ አይደለም።

"አረቦቹ ይህን የሚስቱት አይመስለኝም፤ ነገሩ የተጽእኖ ከባቢን የመፍጠር እና የማስፋት ሙከራ ነው። ጥያቄው መሆን ያለበት ኢትዮጵያ ይህን ከበባ ለመቀልበስ ምን እያደረገች ነው የሚለው ነው" ይላሉ አቶ ነአምን።

እንደሚፈራው ግብፅ ኢትዮጵያን ከቀጠናው ጂኦፖለቲክስ ተጽእኖ የማክሰም አና የማኮስመን ጉዞ ጀምራ ከሆነ ይህ የቀይ ባሕር ፎረም የመግቢያ ሽንቁሯ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ።

መድረኩ ወደ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት የመለወጥ ዕድል አለው?

ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ ቀለበት ውስጥ እየገባች ይሆን?

ዛሬ ሩሲያን ወደ ጦርነት ያስገባት አንድ ምክንያት በረዥም ዘመናት ውስጥ ቀስ በቀስ ከበባ ውስጥ መግባቷ ነው የሚሉ ተንታኞች ጥቂት አይደሉም።

አነዚህ ተንታኞች የዩክሬን ወረራን የሚነቅፉትን ያህል ላለፉት በርካታ አሥርታት ኔቶ ሩሲያ አንገት ላይ ሸምቀቆ እያጠበቀ ቆይቷል ይላሉ።

እርግጥ ነው ኔቶን ከቀይ ባሕር ምክክር መድረክ ጋር ማነጻጸር ስሜት አይሰጥም።

በዓላማም፣ በተልዕኮም፣ በግብርም የሚያመሳስላቸው ነገር የለም።

በዚያ ላይ የቀይ ባሕር መድረክ ገና ዳዴ እያለ ያለ ነው።

በዚያ ላይ የመድረኩ ዓላማ ተብለው የተቀመጡት የባሕር ውንብድናን መከላከል፣ ከስፍራው የሚገኝ ጥቅምን ማጎልበት እና መጋራት፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያን እና የሰው ዝውውርን መቆጣጠር ናቸው።

እርግጥ ነው እነዚህ ፍላጎቶች አንድ በአንድ እየተነሱ ቢታዩ ሁሉም የምዕራብ አገራት የጋራ ስጋቶች ሆነው ይገኛሉ።

የባሕር ውንብድና ለአሜሪካ እና ለምዕራብ አገራት ብቻም ሳይሆን ለምሥራቁም ስጋት ሆኖ የቆየ ነው።

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተቀዳሚ የአውሮፓ ራስ ምታት ነው።

በተጨማሪም፣ በዚህ አካባቢ ሰፋፊ የጋዝ ኃይል ማስተላለፊያዎች ግንባታን ጨምሮ ቻይና እፈጥረዋለሁ የምትለው ሰፊ የአውራ ጎዳና ቀለበት ወደፊት ቀጠናውን የላቀ የንግድ ትስስር የስበት ማዕከል ማድረጉ አይቀርም።

ያ ጊዜ ሲመጣ የአካባቢው አገራት ከሩቅ በሚመጡት ቻይናን፣ ሕንድን እና አሜሪካንን የመሰሉ ኃያላን የንግድ ብልጫቸው እንዲወሰድባቸው አይሹም።

ይህም የትብብር መድረኩን ለመፍጠር ሌላ ምክንያት ሆኖ ይሆናል።

ነገር ግን ሄዶ ሄዶ ይህ መድረክ ወደ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ቢያድግስ? ጊዜውን ያልጠበቀ ስጋት ነው?

አቶ ነአምን አሸናፊ እንደሚሉት ይህን መድረክ ለመፍጠር ከታለመ ዘመን የለውም።

በሐሳብ ደረጃ ከኤርትራ ጀምሮ ግብፅ እና ሳዑዲ በተለያየ ጊዜ እና ሁኔታ ትልሙ ነበራቸው።

"በሳዑዲ አጋፋሪነት በ2020 ተመሠረተ እንጂ ግብፅ እና ሳዑዲ ከ2018 ጀምሮ ሲነጋገሩበት የነበረ ጉዳይ ነው። ከ1970ዎቹ ጀምሮ ይብዛም ይነስ ሙከራዎች ነበሩ" ይላሉ።

ይህ ማለት ግን ወደላቀ ኅብረት አያድግም ማለት ነው?

"ለምን ተመሠረተ የሚለውን ለመረዳት በቀጠናው ያለውን ካባቢያዊ ተጽእኖ ፈጣሪ የመሆን እሽቅድምምን መረዳት ይገባል" እንደ አቶ ነአምን።

ይህም በዋናነት የሚገለጸው በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እና በሳዑዲ መካከል ያለ ውስጣዊ ትግል ነው።

ይህ ሌላ ጥያቄን ያጭራል። የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ከመድረኩ ለምን ተዘነጋች?

ለአቶ ነአምን ይህ ሌላ መሠረታዊ ነጥብ ነው።

አረብ ኤምሬትስ ለምን ተዘነጋች?

እንዴት የተባበሩት አረብ ኢምሬት በዚህ መድረክ ተዘነጋች?

ተዘንግታ አይደለም።

የባሕረ ሰላጤው አገራት ኳታርን ያገለሉ ጊዜ ግብፅ፣ ሳዑዲ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ናቸው የኳታርን መንግሥት የነጠሉት፤ የአየር ክልል በመዝጋት፣ ምጣኔ ሃብታዊ ተጽእኖ በመፍጠር።

ይህ በጋራ የቆሙበት ጊዜ ነው። ይህን ኅብረታቸው ካጸኑ ብዙ አልቆዩም።

ታዲያ ይህ የቀይ ባሕር መድረክ ሲቋቋም እንዴት የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆነችው ኢምሬቶችን ሳይጋበዙ ቀሩ?

ኢምሬቶችን ካነሳን ሌላም ጥያቄ ማንሳት ይቻላል።

የኢምሬቶች ሚና በቀጠናው ወደር የለውም።

"ዲፒዎርልድ በጂቡቲ እና በሶማሊላንድ ወደቦችን የሚያስተዳድር እጅግ ግዙፍ ድርጅት ነው፡፡ ኢምሬቶች በሁሉም የቀጠናው አገራት ውስጥ ይነስም ይብዛ እዚያም እዚህም ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች አሏቸው።"

ታዲያ በዚህ ቀጠና ውስጥ ኢምሬቶችን ያላካተተ መድረክ እንዴ ተመሠረተ?

"ለዚህም ነው እኮ የዚህ መድረክ ግብ፣ መሥራቾቹ እንደሚሉት የንግድ ትብብር ነው ብሎ ለማመን የሚያስቸግረው" ይላሉ አቶ ነአምን።

"ከትብብር ይልቅ እሽቅድምድም ነው የሚታየኝ" የሚሉት የአካባቢው ተንታኝ ፤ ሳዑዲ እና ኢምሬቶች አካባቢውን በይበልጥ ለመቆጣጠር ሩጫ ላይ መሆናቸውን ያሰምሩበታል።

"የንግድ ትብብር መድረክ ነው የሚሉት ለወጉ ያህል (face value) ነው። ነገሩ ትብብር ሳይሆን ፉክክር ነው። ፉክክሩም የነዳጅ ገንዘብ ያላቸው የሁለት አገራት ብቻ ነው።"

ይህ ፉክክር እያየለ ከሄደ ምን ሊከሰት ይችላል? ኢምሬትስ ጉዳዩን በቸልታ ታየዋለች?

አቶ ነአምን እንደሚገምቱት የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ኢምሬቶችም ተገዳዳሪ ሆነው ይቀርባሉ።

"ምናልባትም ሰፊ ሕዝብ ያላትን ኢትዮጵያን አካተው ሳዑዲን የሚገዳደር ሌላ ተፎካካሪ ኅብረት (Block) መፍጠራቸው የማይቀር ነው።"

የቀይ ባሕር መድረክ ወዴት ሊያድግ ይችላል?

አቶ ነአምን ገና ከመነሻው የመድረኩ ጥንካሬ እና የዓላማ ግልጽነት ላይ ጥያቄ አላቸው።

ለምሳሌ አስራኤል የለችበትም የሚሉት ባለሙያው፣ እስራኤል የቀይ ባሕር አካል ሆና፣ ኢትዮጵያ የአካባቢው ተጽእኖ ፈጣሪ ሆና ሁለቱ ቸል ሊባሉ የሚቸሉ አገራት አልነበሩም ይላሉ።

"ዋና ተዋናዮቹን የቀጠናውን ተዋናዮች ያገለለ የትብብር መድረክ መሆኑ የሚነግረን አንድ ነገር ቢኖር የአንድን አገር ሕልም ለማስፈጸም የቆመ መሆኑን ነው" ይላሉ አቶ ነአምን።

ወደ ጦር ቃል ኪዳን የማደግ ዕድል አለው ወይ? ተብለው ሲጠየቁ ነገሩ ሩቅ ይሆንባቸዋል።

ያለ ምክንያት አይደለም ታዲያ፤ የአባል አገራቱን ስብጥር እና ደካማነትን በማሰላሰል እንጂ።

"ሱዳን ቀውስ ውስጥ ናት፣ ኤርትራ ከዓለም የተገለለች ናት፣ ሶማሊያ እና የመን የት እንዳሉ ይታወቃል፣ ቀሪዎቹ ዮርዳኖስ እና ግብፅ ናቸው፤ እንኳንስ ሊጠናከሩ እርስ በርስ ቁርሾ ያለባቸው ናቸው። በአጭሩ ሳዑዲን ማጀብ ካልሆነ እነዚህ አገራት ሌላ ምን የረባ ሚና ሊኖራቸው ይችላል?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

"ኔቶን የመሰሉ ድርጅቶች ሲመሠረቱ እኮ በግልጽ የተበየነ ዓላማ እና አንድ የጋራ ትልም ይዘው ነው። ይህ መድረክ ትልም ካለው የሳዑዲን ትልም ይዞ ነው የተነሳው" ብለዋል አቶ ነአምን አሸናፊ የአፍሪካ እና ኦሪየንታል ተመራማሪው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር ተጎራባችነት እንደምትመለስ በተደጋጋሚ እየተናገሩ ነው።

የስብስቡ አባል የሆነችው ኤርትራ ደግሞ ሉዓላዊ ግዛቷን እንደማታስነካ እየገለጸች ነው።

ግብፅ ደግሞ በሁሉም መልኩ ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ለማራቅ ጥረት እያደረገች ነው።

በዚህ ሂደት ውስጥ የቀይ ባሕር ትብብር መድረክ ሚናው ምን ሊሆን እንደሚችል በጊዜ ሂደት የሚታይ ይሆናል።

_____________________

*ይህ ዘገባ ከሁለት ዓመት በፊት ቀርቦ የነበረ ሲሆን፣ ተጨማሪ መረጃ እና ማሻሻያ ተደርጎበት በድጋሚ የቀረበ ነው።