በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምግብ ቤት ውስጥ አጥፍቶ ጠፊ ባደረሰው ፍንዳታ ቢያንስ 6 ሰዎች ሞቱ

በዲሞክራቲክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ከተማ ቤኒ በአንድ ምግብ ቤት በፈነዳ የአጥፍቶ ጠፊ ቦምብ ቢያንስ ስድስት ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ፖሊስ ቦምቡን ይዞ የነበረው ግለሰብ ወደ ህንጻው እንዳይገባ ከልክሎት የነበረ ቢሆንም ግለሰቡ መግቢያ በሩ ላይ ቦምቡን ራሱ ላይ በማፈንዳቱ ራሱንና እና ሌሎች አምስት ሰዎችን ገድሏል።

ሌሎች 13 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ባለሥልጣናት ቅዳሜ እለት የተፈፀመውን ይህንን ጥቃት ያደረሰው አላይድ ዲሞክራቲክ ፎርስስ [ኤዲኤፍ] የተባለውና ከአይኤስ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገረው ታጣቂ ቡድን እንደሆነ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ለደረሰው ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደ አካል የለም።

ጥቃቱ ሲፈፀም ከ30 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ ተሰባስበው የገና በዓልን እያከበሩ እንደነበር ሁለት የዐይን ምስክሮች ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

በወቅቱም በምግብ ቤቱ ውስጥ ህጻናትና የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደነበሩም ተነግሯል።

" እዚያ ተቀምጨ ነበር። በስፍራው ሞተር ሳይክል ቆሞ ነበር። ድንገት ሞተር ሳይክሉ ተነሳ። ከዚያም ከፍተኛ ድምጽ ተሰማ " ሲል ኒኮላስ ኢኪላ የተባለ የራዲዮ ፕሮግራም አቅራቢ ለኤኤፍፒ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

ፍንዳታው ከተከሰተ በኋላም በአገሪቷ ምሥራቃዊ ክፍል ለተጣለው አስቸኳይ ጊዜ ኃላፊነት ያላቸው የጦር ባለሥልጣናት ነዋሪዎች ለደህንነታቸው ሲሉ ወደ ቤታቸው እንዲሄዱ አሳስበዋቸዋል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በቤኒ በጦሩ እና በእስላማዊ ታጣቂዎቹ መካከል ተደጋጋሚ ግጭት አለ።

ኅዳር ወር ላይ የኮንጎ እና የኡጋንዳ ኃይሎች በተደጋጋሚ የሚፈፀሙ ጥቃቶች ለማስቆም በእስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ ኤዲኤፍ ላይ በጋራ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል።

የኡጋንዳ ባለሥልጣናት ቡድኑ በዋና መዲናዋ ካምፓላ ጨምሮ በአገሪቷ በተደጋጋሚ ለተፈፀሙ ጥቃቶች ተጠያቂ ነው ብለዋል።

ታጣቂ ቡድኑ እአአ በ1990ዎቹ የተቋቋመው መንግሥት በሙስሊሞች ላይ በሚወስደው እርምጃ ቅር በተሰኙ ኡጋንዳውያን ሲሆን ይንቀሳቀሱበት ከነበረው ከምዕራብ ኡጋንዳ ተወግደው ቀሪዎቹ ድንበር ተሻግረው ወደ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ገብተዋል።

ከዚያም በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ እራሱን ያቋቋመ ሲሆን ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ጨምሮ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ግድያ ተጠያቂ ሆኗል።

መጋቢት ወር ላይ አሜሪካ ኤዲኤፍን ከአይኤስ ጋር ግንኙነት ባላቸው የሽብር ቡድኖች ዝርዝር ውስጥ አስገብታዋለች።

አይኤስም በበኩሉ ኤዲኤፍ ከቡድኑ ጋር ግንኙነት እንዳለው ገልጿል።