ጣት የሚያስቆረጥሙ ምግቦችን የሚያበስሉ ሮቦቶች ሥራ ላይ መዋል መነጋገሪ እየሆነ ነው

ምናልባት በዓላት ሲደርሱ ለቤተሰቦቼ ቆንጆ ምግብ ባበስልላቸው ብለው አስበው ይሆናል። በዓላት ወቅት አብዛኛው ሰው ጣፋጭ ምግብ ሰርቶ ቤተሰቦቹን ስለማብላት ያስባል።

ነገር ግን ወደፊት ለሚመጡ በዓላት የተሻለ አማራጭ ሊኖር ይችላል። ምግብ ማብሰል የሚችሉ ሮቦቶች ደርሰናል እያሉ ነው።

ጥቂት የማይባሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ለግለሰብም ሆነ ለድርጅቶች ጥፍጥ ያለ ምግብ ማብሰል የሚችሉ ሮቦቶችን በመስራት ላይ ይገኛሉ።

ከእነዚህ ኩባንያዎች አንዱ የሆነውና መቀመጫውን እንግሊዝ ለንደን ያደረገው 'ሞሊ ሮቦቲክስ' በሚቀጥለው ዓመት ምግብ አብሳይ ሮቦቶችን ለገበያ ለማቅረብ አቅዷል።

በኩሽና ጣሪያ ላይ የሚገጠሙት ሮቦቶች ሁለት ከብረት የተሰሩ እጆች የሚኖራቸው ሲሆን እርስዎ ማደረግ የሚጠበቅብዎት ነገር ቢኖር ምን አይነት ምግብ መብላት እንደሚፈልጉ መናገር ብቻ ነው።

እስከ 5 ሺህ አይነት ምግቦችን ማብሰል የሚችለው ሮቦት ታዲያ የሚያስፈልጉትን ግብአቶች ካሟሉለት በኋላ በፍጥነት መጣፈጡ የተረጋገጠ ምግብ ያቀርብሎታል።

መቅመስ ብቻ ሲቀር መላጥ፣ መክተፍ፣ ማማሰል፣ ጨው መጨመርም ሆነ ሁሉንም አብሳይ ሮቦቱ ማድረግ ይችላል።

ይህ የእንግሊዝ ድርጅት ታዲያ ሮቦቶቹ የሚሰሯቸውን ምግቦች አይነት ለማዘጋጀት ከታዋቂው የምግብ ማብሰል ባለሙያ ቲም አንደርሰን ጋር አብሮ እየሰራ ነው። ቲም ከዓመታት በፊት 'ማስተር ሼፍ' በቢቢሲ የምግብ ማብሰል ውድድር አሸናፊ ነበር።

ሮቦቶቹ ታዲያ ቲም ምግቦቹን ሲሰራ የሚያደርጋቸውን ነገሮች በሙሉ በተመሳሳይ መንገድ መስራት እንዲችሉ ተደርገው ተዘጋጅተዋል።

"እኔ ማብሰያ ክፍል ውስጥ ገብቼ ምግብ መስራት ስጀምር የሞሊ ሮቦቲክስ ኮምፒውተሮች እያንዳንዱን እንቅስቃሴዬን መዝግበው ያስቀምጣሉ። ከዚህ በኋላ ይህንን መረጃ ለሮቦቶቹ ይሰጧቸዋል'' ይላል።

"የድርጅቱ ሠራተኞች የሮቦቶቹ እጆች በትክክል እንዴት መስራት እንዳለባቸውና እንዴት መመጠን እንደሚችሉ ለማወቅ የሚያስፈልጋቸውን መረጃዎች በሙሉ ይሰጧቸዋል። ከዚህ በኋላ ሁሌም ተመሳሳይ የሆነና ጣዕሙ የማይቀያየር ምግብ ማዘጋጀት ይቻላል።"

ሞሊ ሮቦቲክስ ሚያዘጋጀው ምግብ አብሳይ ሮቦት በትንሹ እስከ 150 ሺህ ፓውንድ ወይም ከ9.5 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ተቆርጦለታል። ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ሮቦቶች ከእንግሊዝ በተጨማሪ እስራኤል እና አሜሪካ ውስጥ እየተሰሩ ነው።

የእንደዚህ አይነት አገልግሎት ሰጪ ሮቦቶች ዋጋ በጊዜ ብዛት እንደሚቀንሱ የምትናገረው ደግሞ በአሜሪካ በከፍተኛ የማማከር ሥራ ላይ የተሰማራችው ጁሊያ ሴጋል ነች።

"አሁን ላይ እነዚህ ሮቦቶች ለአብዛኛው ሰው ኩሽና ውስጥ መገኘታቸው የማይታሰብ ነው። ነገር ግን ከሆኑ ዓመታት በኋላ ቴክኖሎጂዎቹ በጣም እየተራቀቁ ሲሄዱ አሁን ላይ በጣም የሚያስገርሙንና በጣም ውድ የሆኑት ሮቦቶች ዋጋቸውም እየቀነስ መምጣቱ አይቀርም።"

መሰል ቴክኖሎጂዎችን ከሚጠቀሙ ድርጅቶች መካከል የፈረንሳዩ ፒዛ ሻጭ ድርጅት 'ፓዚ' ነው።

ይህ ድርጅት የተቋቋመው በሁለት የሮቦቶት ቴክኖሎጂ መሀንዲሶች ነው። እነዚህ መሀንዲሶች ታዲያ የእነሱ ድርጅት በሮቦቶች በመታገዝ ፒዛ በመስራት ይሸጣል።

በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በአውሮፓውያኑ 2019 የተጀመረው ይህ የንግድ ሥራ አሁን ላይ ሌላ ሁለተኛ የፒዛ መሸጫ በፓሪስ እንዲሁም አንድ ሌላ ደግሞ ቤልጂየም ብራስልስ ውስጥ ከፍቷል።

በዚህ ድርጅት ሁሉም ፒዛ የመስራት ሂደቶች የሚካሄዱት በሮቦቶች ነው። ደንበኞች መጥተው ፒዛ ሲያዙ ታዲያ ሮቦቶች በአምስት ደቂቃ ውስጥ የፈለጉትን አይነት ጣፋጭ ፒዛ ሰርተው ያቀርባሉ።

ከድርጅቱ መስራቾች መካከል አንዱ የሆነው ፊሊፕ ጎልድማን እንደሚለው ሮቦቶቹ በፍጹም ጥንቃቄ ጣፋጭ ፒዛ እንዲሰሩ ተደርገው መሰራታቸውን ይናገራል።

"ሮቦቶቹ ሊጡን በሚያዘጋጁበት ወቅት እንኳን ሊጡ ላይ የመሳሳትም ሆነ የመጠንከር ነገር ካገኙ ወዲያው ያስወግዱታል። ከላይ የሚጨመሩት ነገሮችም ቢሆን በከፍተኛ ጥንቃቄና እውቀት የሚዘጋጁ ናቸው።"

ምንም እንኳን የማብሰል ሥራው በሮቦቶች ይከናወን እንጂ ሮቦቶቹ ፒዛውን ማዘጋጀት የሚፈልጓቸውን ነገሮች በሙሉ የሚያቀርቡላቸው በድርጅቱ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰዎች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ደንበኞችን ከማስገባት ጀምሮ እስከ ማስተናገድ ድረስ ያለውን ሥራ በሙሉ የሚሰራው በሰዎች ነው።

አሁን ላይ እነዚህ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ለራሳቸው ብለው የሰሩት ፒዛ የሚያዘጋጅ ሮቦት ከ1 ሺህ በላይ ፈላጊዎች እንዲኖሩት አድርጓል። ከአሜሪካ፣ ጣልያን፣ ጀርመን እንዲሁም ሌሎች አገራት የሚገኙ ባለሀብቶች ሮቦቶቹን ለመግዛት ጥያቄ እያቀረቡ ነው።

ሚካኤላ ፒሳኒ የዘርፉ ባለሙያ ስትሆን ምግብ መስራት የሚችሉ ሮቦቶች ከጣዕም፣ ከደኅንነት እንዲሁም ከንጽህና ጋር በተያያዘ ምንም አይነት ቅሬታ የሚቀርብባቸው አይደሉም። ሮቦቶቹ የምግብ ዘርፉን በእጅጉ እንደሚያዘምኑና አካሄዱን በሙሉ እንደሚቀይሩት ታምናለች።

በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ሮቦቶች ሰዎች ሊሰሯቸው የሚችሉ ሥራዎችን እየተሻሙ መምጣታቸው እንደሚያሳስባት ገልጻለች።

በርካቶች ደግሞ ምንም እንኳን ሮቦቶች አሁን ላይ በትንሽ ደረጃም ቢሆን የሰዎችን ሥራ ሊሻሙ ቢችሉም ትልልቅ ሬስቶራንቶችና ሆቴሎች ግን እነዚህን ሮቦቶች የመጠቀማቸው ነገር አነስተኛ ነው። ምክንያቱም መቼም ቢሆን ሰዎች በሰው የተሰራ ምግብ መመገብ መፈለጋቸው አይቀርም።

ሰዎች በጥሩም ይሁን በመጥፎው ቢመለከቱት ምግብ መስራት የሚችሉ ሮቦቶች ግን በቅረብ ዓመታት ውስጥ የተለመዱ መሆናቸው አይቀርም። ሰዎችም በዓላት ሲደርሱ እስቲ ይሄን ምግብ ስራልን ብለው ሮቦቱን ማዘዝ የሚችሉበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።