ናሳ የአስትሮይድ አቅጣጫ ማስለወጡን አረጋገጠ

ናሳ ከሰሞኑ የግዙፍ አስትሮይድን አቅጣጫ ለማስቀልበስ ያደረገው ሙከራ እንደተሳካ ገለጸ።

አስትሮይድ በፀሐይ ዙርያ የሚሽከረከር አለታማ አካል ነው። የተለያየ መጠን ያላቸው አስትሮይዶች አሉ።

ናሳ አቅጣጫውን ያስቀየረው አስትሮይድ 160 ሜትር ይሰፋል።

ዲሞርፈስ የተባለው ይህ አስትሮይድ አቅጣጫውን እንዲቀይር የተደረገው ባለፈው ወር ነው።

አቅጣጫውን እንደቀየረ የተረጋገጠው በቴሌስከፕ ከታየ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።

ናሳ የዚህን አስትሮይድ አቅጣጫ የማስቀየር ሙከራ ያደረገው፣ ወደ ምድር የሚጓዙ ሌሎች ግዑዝ አካላትን መምታት እንደሚቻል ለማረጋገጥ ነው።

ዳርት የተባለው የአስትሮይድ አቅጣጫ የማስቀየር ፕሮጀክት፣ ናሳ የማንኛውንም ግዑዝ አካል አቅጣጫ ማስቀልበስ እንደሚችል ማሳያ እንደሆነ የናሳ አመራር ቢል ኔልሰን ተናግረዋል።

“ናሳ ምድርን መከላከል እንደሚችል አረጋግጠናል” ብለዋል።

ናሳ የአስትሮይዱን አቅጣጫ ማስቀየሩን በሀብል ስፔስ ቴሌስኮፕ ባነሳቸው ምሥሎችም አረጋግጧል።

ዳርት ወይም Double Asteroid Redirection Test ከምድር 11 ሚሊዮን ኪሎ ሜትሮች ርቆ ነበር የተከናወነው።

ናሳ የሠራው ማቀዝቀዣ ወይም ፍሪጅ የሚያህል ሳተላይት ዲሞርፈስ ከተባለው አስትሮይድ ጋር በሰዓት 22 ሺህ ኪሎ ሜትር ተጉዞ እንዲጋጭ የተደረገበት ፕሮጀክት ነው።

ሳተላይቱ ከአስትሮይዱ ጋር ከተጋጨ በኋላ ፈራርሷል። በግጭቱ ግን የአስትሮይዱን አቅጣጫ ማስለወጥ ተችሏል።

አስትሮይዱ ከራሱ የሚገዝፍ ሌላ ዲዳይሞስ የተባለ አስትሮይድን በ11 ሰዓት ከ55 ደቂቃ ፍጥነት እየዞረ ነበር።

ናሳ አስትሮይዱን በሳተላይት ከገጨው በኋላ ግን ዲዳይሞስን የሚዞርበት ፍጥነት ወደ 11 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ዝግ ብሏል።

በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስት የአፕላይድ ፊዚክስ ባለሙያ ዶ/ር ናንሲ ቻቦት እንደሚለው፣ የናሳ ሳተላይት አስትሮይዱን በስሱ ገፍቶ አቅጣጫ ማስለወጥ ቢችልም፣ በቀጣይ የአስትሮይድን አቅጣጫ በሰፊው ለማስቀየር ዓመታት ቀድሞ ሳተላይት ማስወንጨፍ ያስፈልጋል።

አስትሮይዶች በቅርጽና በአካሄድም የተለያዩ እንደሆኑ በመጥቀስ፣ የአንድ አስትሮይድን አቅጣጫ ማስቀየር የሌሎችም ማስለወጥ እንደሚቻል እንደማይጠቁም ገልጸዋል።

ተጨማሪ ጥናትና ሙከራ እንደሚያስፈልግም ባለሙያው መክረዋል።

የአውሮፓ የሕዋ ተመራማሪ (ኢሳ) ከአራት ዓመታት በኋላ ስለ ዲሞርፈስ እና ዲዳይሞስ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።