ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኒው ዚላንድ የአየር ብክለትን ለመከላከል ለላሞች ግሳት ግብር ልታስከፍል ነው
ኒው ዚላንድ የአየር ብክለትን ለመከላከል ለከብቶች እና ለበጎች ግሳት እና ሽንት ገበሬዎችን ግብር ማስከፈል ልትጀምር ነው።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚወሰደው እርምጃ ኒው ዚላንድ በግብርና ምክንያት ለሚመጣ ብክለት ገበሬዎችን ግበር እአአ 2025 ላይ የምታስከፈል የመጀመሪያዋ አገር ትሆናለች።
የአገሪቱ የግብርና ኢንዱስትሪ ለአካባቢ በክለት ገሚሱን ድርሻ ይወስዳል። ኒው ዚላንድ ጠቅላላ የሕዝቧ ቁጥር 5 ሚሊዮን ገደማ ሲሆን፣ የሥጋ እና የወተት ተዋጽእኖ የሚሰጡ ከብቶች ቁጥሮቿ ግን የሕዝብ ቁጥሯን በእጥፍ ይበልጣሉ። የኒው ዚላንድ በጎች ቁጥር ደግሞ ከ25 ሚሊዮን እንደሚሻገር ይገለጻል።
እነዚህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቤት እንስሳት ሲያገሱ የሚያወጡት ሚቴን የተባለ በካይ ጋዝ እና ሽንታቸው የያዘው ኒትረስ ኦክሳይድ ለአካባቢ ሙቀት አንዱ ምክንያት ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ጃሲንዳ አርድነር በዚህ ሕግ የሚገኘው ገቢ አዲስ ቴክኖሊጂዎችን ለመጠቀም፣ ምርምሮችን ለማካሄድ እና ለገበሬዎች ማበረታቻ ለመስጠት ገንዘቡ ወደ ዘርፉ ተመልሶ የሚገባ ይሆናል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሯ አዲሱን ዕቅዳቸውን ሲያስተዋውቁ፤ የኒው ዚላንድ ገበሬዎች ከግብርና ሥራ የሚከሰት የአየር ብክለትን በመከላከል በዓለም የመጀመሪያዎቹ ይሆናሉ ብለዋል።
መንግሥት የቤት እንስሳቱ በከባቢ አየር ላይ ለሚያስከትሉት ብክለት የሚጥለው ዋጋ ምን ያህል እንደሆነ ግልጽ ባይደረግም፤ ገበሬዎቹ ግን ለአካባቢ አየር ተስማሚ የሆኑ ምርቶችን ለገበያ በማቅረባቸው ለምርቶቻቸው ከፍ ያለ ዋጋ በመጠየቅ ወጪያቸውን ማካካስ ይችላሉ ብሏል።
ይሁን እንጂ ገና ከአሁኑ ይህ የኒው ዚላንድ መንግሥት ዕቅድ ከአገሪቱ የግብርና ሠራተኞች ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠመው ነው።
የኒው ዚላንድ መንግሥት ዕቅድ ከተሰማ በኋላ አንዳንድ ገበሬዎች ከብቶቻቸውን እና በጎቻቸውን በፍጥነት እንሸጣለን ሲሉ ተናግረዋል።
አንድ የገበሬዎች ማኅብር ፕሬዝዳንት የመንግሥት ዕቅድ የእርሻ መሬቶችን ወደ ደን የሚቀይር ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።