ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የነዳጅ ዋጋ እንዲንር ወይም እንዲቀንስ የሚያደርገው ምንድን ነው? የሚወስነውስ ማን ነው?
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ማብቂያ ላይ የዓለማችን ቀዳሚ ነዳጅ ላኪ አገራት ስብሰባ አድርገው ነበር።
አጀንዳቸው የነበረውም የድፍድፍ ነዳጅን ዋጋ ለመቀነስ ያለመ ነበር።
በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ዋጋ ካለፉት ስምንት ዓመታት የበለጠ ሆኗል። ነዳጅ ከውጭ አስመጥተው የሚጠቀሙ አገራት፣ ነዳጅ አምርተው የሚልኩ አገራት ስብስብ የኦፔክ ፕላስ (Opec+) የነዳጅ ምርትን እንዲጨምሩ ተማጽነዋል።
ዋነኞቹ ነዳጅ ላኪ አገራት እምብዛም ተማጽኖውን የሰሙ አይመስልም።
ይልቁንም በቀን የሚመረተውን ነዳጅ በሁለት ሚሊዮን በርሜል ለመቀነስ ተስማምተዋል።
ሩሲያን ጨምሮ የኦፔክ ፕላስ አባል አገራት የነዳጅ ዋጋን ለመጨመር እርምጃ እየወሰዱ ነው።
የነዳጅ ዋጋ ባለፈው ዓመት የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም፤ ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ ዋጋው ንሯል።
የነዳጅ ላኪ አገራት ስብስብ
ዋነኞቹ የዓለማችን የነዳጅ ዘይት አምራች አገራት የምርታቸውን መጠንና ዋጋን ለመቆጣጠር ኦፔክ ፕላስ በተባለ ማኅበር ተሰባስበዋል። አባላቱም 23 አገራት ናቸው።
በዓለም ገበያ ድፍድፍ ነዳጅ በስንት ይሸጥ የሚለውን ለመወሰን ውይይት ያካሂዳሉ።
በዚህ ስብስብ ውስጥ ካሉት አገራት መካከል 13ቱ ከመካከለኛው ምሥራቅ እና ከአፍሪካ ናቸው።
ከኦፔክ ፕላስ በፊት በ1960ዎቹ ኦፔክ ሲመሠረት አላማው የዓለምን የነዳጅ ዘይት ገበያ ፈር ማስያዝ ነበር። ዛሬ ላይ የዓለም 30 በመቶ ነዳጅ የሚመረተው በኦፔክ አገራት ነው።
ሳዑዲ አረቢያ በቀን ከ10 ሚሊዮን በርሜል በላይ ነዳጅ በማምረት የአንበሳውን ድርሻ ትይዛለች።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2016 የነዳጅ ዋጋ እጅግ አሽቆልቁሎ ነበር። ኦፔክ ከሌሎች 10 ነዳጅ አምራቾች ጋር ተዋህዶ ኦፔክ ፕላስ የተፈጠረውም የዚያን ጊዜ ነበር።
ኦፔክ ፕላስ የዓለምን 40 በመቶ ድፍድፍ ነዳጅ ያመርታል።
በኢነርጂ ኢንስቲትዩት የምትሠራው ኬት ዶውሪን “ኦፔክ ፕላስ ገበያውን ለማረጋጋት አቅርቦት እና ፍላጎትን ያመጣጥናል” ትላለች።
“የነዳጅ ፍላጎት ሲቀንስ፣ የነዳጅ አቅርቦትን ዝቅ በማድረግ ዋጋውን ይጨምራሉ” ስትልም ታስረዳለች።
በርከት ያለ ነዳጅ ገበያው ላይ በማቅረብ ዋጋ እንዲቀንስ ማድረግም ይችላሉ።
ለምን የነዳጅ ምርት እንዲቀንስ ተወሰነ?
የኦፔክ ፕላስ አባል አገራት ከሁለት ዓመት በፊት ኦስትሪያ፣ ቪየና ውስጥ ከተገናኙ በኋላ፣ ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ በቀን የሚመረተውን ነዳጅ በሁለት ሚሊዮን በርሜል በመቀነስ ምርታቸውን ከ42 ሚሊዮን በርሜል በታች ለማድረግ ወስነዋል።
ይህ ውሳኔም ካለንበት ጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።
በዚህም የሚደረገው ቅነሳ ከዓለም አጠቃላይ የነዳጅ ምርት ሁለት በመቶውን ሲይዝ፣ ከሚጠበቀውም በላይ ነው።
ከአውሮፓውያኑ 2020 ወዲህ የኦፔክ ፕላስ አባላት ነዳጅ ምርት ላይ ያደረጉት ከፍተኛው ቅነሳ እንደሆነም ተገልጿል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ጊዜ የነዳጅ ምርትን በቀን ከዘጠኝ ሚሊዮን በርሜል በላይ ለመቀነስ ወስነው ነበር።
ውሳኔው የተላለፈው የነዳጅ ዋጋን ለመጨመር ነው። በወቅቱ የነዳጅ ዋጋ ከነበረበት 122 ዶላር ወደ 90 ዶላር ዝቅ ብሎ ነበር።
የነዳጅ ምርትን ለመቀነስ ውሳኔ ሲተላለፍ የነዳጅ ዋጋ ጨምሯል።
የነዳጅ ዋጋ መጨመር በመላው ዓለም የዋጋ ንረትን አስከትሏል።
አሜሪካ ኦፔክ ፕላስ የነዳጅ ምርትን እንዳይቀንስ ጠይቃለች። የነዳጅ ዋጋ አነስተኛ ከሆነ ሩሲያ የምታገኘው ገቢም ያንሳል ማለት ነው።
ዋይት ሐውስ የኦፔክ ፕላስን ውሳኔ “የረጅም ጊዜ ሁኔታን ያላጋዘበ” ሲል ተችቷል።
ያለፈው ሐምሌ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሳዑዲ አረቢያ ተጉዘው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን የነዳጅ ምርትን እንዲጨምሩ ጠይቀው ነበር። ነገር ግን ጥያቄውን አልተቀበሉትም።
የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንም በተመሳሳይ ሳዑዲ አረቢያ እና ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የነዳጅ ምርት እንዲጨምሩ ቢጠይቁም አልተሳካላቸውም።
የነዳጅ ዋጋ ለምን ናረ?
ከሁለት ዓመት በፊት ኮሮናቫይረስ ሲነሳ፣ አገራትም በራቸውን ሲዘጉ፣ ድፍድፍ ነዳጅ ገዢ አጥቶ ዋጋው አሽቆልቁሎ ነበር።
“ነዳጅ አምራቾች ምርታቸውን ለመሸጥ ለገዢዎች ገንዘብ እየከፈሉ ነበር። አምራቾቹ ነዳጁን የሚያከማቹበት ቦታ አጥተውም ነበር” ስትል በኢነርጂ ኢንስቲትዩት የምትሠራው ኬት ዶውሪን ታስረዳለች።
የኦፔክ ፕላስ አባላት የነዳጅ ምርትን በቀን በአስር ሚሊዮን በርሜል ለመቀነስ የወሰኑት የነዳጅ ዋጋ እንዲያንሰራራ ነበር።
ከዚያ ወዲህ ኦፔክ ፕላስ የነዳጅ ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ቀስ በቀስ ምርቱን እያሳደገ መጥቷል።
ሩሲያ ዩክሬንን ስትወር ግን የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ ሆነ።
በሩሲያ ላይ የተጣሉ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች የሩሲያ ነዳጅ ምርት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ተብሎ ተሰግቷል።
እየቀነሰ ያለው የነዳጅ ዋጋ እንዲያንሰራራ ኦፔክ ፕላስ አምራች አገራት ምርታቸውን ለመቀነስ መወሰናቸው ተጠቁሟል።
የሩሲያ ነዳጅ
ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ በርካታ አገራት ከሩሲያ የሚገዙትን የነዳጅ መጠን ቀንሰዋል።
የሩሲያ ነዳጅ ዋጋ እየቀነሰም መጥቷል።
የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል ከ30 ዶላር በላይ የተሸጠበት ጊዜም ነበር።
መስከረም መጨረሻ ላይ ወደ 20 ዶላር ወርዷል።
ሩሲያ ላይ ማዕቀብ ከጣሉት ምዕራባውያን አገራት ጋር ያልተባበሩት ሕንድ እና ቻይና፣ አሁን ላይ ከአገሪቱ ምርት ከግማሽ በላዩን ይረከባሉ።
በዚህም ሩሲያ የቻይና ትልቋ ነዳጅ አቅራቢ ሆናለች። ከዚህ ቀደም ወደ ቻይና ነዳጅ በዋናነት የምትልከው ሳዑዲ አረቢያ ነበረች።
መጋቢት ላይ ቻይና እና ሕንድ ከሩሲያ የገዙት ነዳጅ ከ27ቱ የአውሮፓ ኅብረት አባላት ይበልጣል።
በዚህ በጥቅምት ወርም የአውሮፓ ኅብረት በሩሲያ የድፍድፍ ነዳጅ ምርት ላይ ማዕቀብ ለመጣል አቅዷል።