የነዳጅ ድጎማ መነሳትና ሊያስከትል የሚችለው ጫና

የኢትዮጵያ መንግሥት የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ ማድረጉን አሳውቋል። በዚህም አስካሁን ከታዩት የዋጋ ጭማሪዎች ሁሉ ከፍተኛው እንደሆነ ተነግሯል።

መንግሥት እንደሚለው የነዳጅ ምርቶችን ለመደጎም በወር በአማካይ 10 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ በመግለጽ፣ በአሁኑ ወቅት 146 ቢሊየን 624 ሚሊየን 248 ሺህ 889 ብር የነዳጅ ድጎማ ዕዳ አለበት ተብሏል።

ቀደም ሲል መንግሥት በየወሩ በሚያደርገው የነዳጅ ዋጋ ክለሳ ላይ ጭማሪው ከ10 በመቶ የሚበልጥ አልነበረም።

አሁን ግን ይህንን የመንግሥት ድጎማውን ደረጃ በደረጃ ለማንሳት ባወጣ ዕቅድ መሠረት በቤንዚን ላይ ከ25 በመቶ በላይ፣ እንዲሁም በናፍጣ ላይ ከ35 በመቶ በላይ ጭማሪ ተደርጓል።

መንግሥት እንደሚለው በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ የነዳጅ ዋጋ ቢሰላ የ1 ሊትር ናፍጣ የመሸጫ ዋጋ ብር 91 ከ23 ሳንቲም እና የቤንዚን ደግሞ በሊትር 82 ብር ከ07 ሳንቲም መሆን ነበረበት። በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ ዋጋው ከዚህ ከፍ ይላል።

ነገር ግን አሁንም መንግሥት 75 በመቶውን ጭማሪ እራሱ በመሸፈን 25 በመቶውን ብቻ ወደ ተጠቃሚው እንዲተላለፍ ማድረጉ ተገልጿል።

የትኛውም የምርትና የአገለግሎት አቅርቦት በአንድም ሆነ በሌላ በኩል ከነዳጅ ዋጋ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ፣ ሕዝቡን ባስጨነቀው የኑሮ ውድነት ላይ ሌላ ጫናን ሊፈጥር ይችላል እየተባለ ነው።

የአሁኑ የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ ክለሳ እንዲሁም በቀጣይ የሚደረገው የዋጋ ማስተካከያ የሚያስከትለውን ውጤት በተመለከተ ከጥቂት ሳምንት በፊት ያዘጋጀነው ጥንቅር በዝርዝር ይዳስሳል። እነሆ . . .

መንግሥት የውጭ ምንዛሬን በስስት ነው የሚያየው። እንደ ስእለት ልጅ።

የዶላር ጥሪት እንደዋዛ አይቋጠርማ። በብዙ አበሳ፣ በብዙ የወጭ ንግድ፣ በብዙ ተጋድሎ ነው የሚመጣው።

እንዲያም ኾኖ ጥሎበት ከአራት ቢሊዮን ዶላር አይዘልም። እሱም ቢኾን መጥቶ አይበረክትም፤ አብዛኛውን ነዳጅ ይጠጣዋል።

ይሁን እንጂ፣ እስከዛሬ ድረስ ለነዳጅ የሚከፈለው ዶላር በወጭ ንግድ ከሚገኘው ዶላር በልጦ አያውቅም ነበር።

አሁን ግን ታሪክ ተቀየረ፤ ነገሩ ከፋ።

ይህ በይፋ የታወቀው ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ነው። ለ2015 ነዳጅ መግዣ የሚያስፈልግህ ስንት ነው ሲባል 5.6 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል አለ።

እንዲህ ያለ አሃዝ ተሰምቶ አይታወቅም ነበር፤ ይህም የመርከብና የነዳጅ ዋጋ መናር ያመጣው ነው ይባላል።

ታዲያ ይህ ገንዘብ ከየት ይመጣል?

አንደኛ ከውጭ ንግድ እንዲህ ዓይነት ገቢ በጭራሽ ኖሮን አያውቅም። ቡናው፣ ሌጦው፣ ሰሊጡ ተረባርበው ከአገር ወጥተው እንኳ እንዲህ ዓይነት ገቢን አያመጡም።

አሳሳቢው ይህ ብቻ በሆነ መልካም።

ነዳጁ ከዚህም ከዚያም ዶላር ተፈልጎ ሊገዛ ይችላል።

ከተገዛ በኋላም ግን መደጎም አለበት።

ከተገዛበት ዋጋ በግማሽ ቀንሶ እንዲሸጥ መደጎም አለበት። ለዚህ ድጎማ ደግሞ አገሪቱ በወር በአማካይ 10 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋታል።

አንድ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ከሰሞኑ ለኢዜአ እንደተናገሩት ድጎማው መንግሥትን በጠቅላላው 132 ቢሊዮን ብር ለሚደርስ የዕዳ ክምችት ዳርጎታል።

መንግሥት ይህን ህመሙን ለዓመታት ቻል አርጎት ቆየ።

በኮቪድ ዘመን የዓለም የነዳጅ ዋጋ መሬት ሲነካ ህመሙን ለጊዜውም ቢኾን አስታግሶለት ይሆናል።

ከኮቪድ በኋላ ግን የነዳጅ ዋጋ በድጋሚ ተቀጣጠለ።

በእንቅርት ላይ. . . እንዲሉ የዩክሬን ጦርነት ተቀሰቀሰ። በዚህ ጊዜ በዓለም ነዳጅ ዋጋ ላይ ‘ሰደድ እሳት’ ተነሳ።

ነዳጅ በዩክሬን ጦርነት ማግስት በበርሜል 140 ዶላር የደረሰበት ጊዜ ነበር።

ይህ ዋጋ ሃብታም አገራትን ሳይቀር ሚዛናቸውን አስቷቸዋል። እዚህ ግባ የሚባል የተፈጥሮ ሃብት ለሌላት፣ የባሕር በር ለሌላትና ሰላም ለራቃት አገር ይህ ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል ማብራሪያ አይሻውም።

“የማይካደው ነገር በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ከአንዳንድ የነዳጅ አምራች አገራት ጋር ሲነጻጸር እንኳ ርካሹ ነው” ይላሉ ተቀማጭነታቸውን በኩዌት ያደረጉት የምጣኔ ሃብት ተመራማሪው አየለ ገላን።

“ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ጋር ቢነጻጸር እንኳ የኢትዮጵያ ነዳጅ ዋጋ በትንሹ አነስ ሳይል አይቀርም።”

ይህን የሚሉት ድጎማው ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ለማስረዳት ነው።

እኚህ ተመራማሪ ድጎማው ከፍተኛ መሆኑን ይግለጹ እንጂ መንግሥት ድጎማውን፣ በተለይ አሁን ላይ፣ ለማንሳት መወሰኑን በፍጹም አይስማሙም።

“የነዳጅ ድጎማውን ማንሳት እየነደደ ያለ ቤት ላይ ነዳጅ ማርከፍከፍ ነው” ሲሉ የመንግሥትን ዕቅድ ይተቹታል።

የነዳጅ ድጎማ የሚለው ሐሳብ ከየት የመጣ ነው?

የነዳጅ ድጎማ በሂደት የተወለደ ሐሳብ ነው። የሕዝብ የመግዛት አቅም ሲያሽቆለቁል፣ የነዳጅ ዋጋ ሲያሻቅብ ድጎማ ተወለደ። ፖሊሲ ሳይሆን ሒደት ወለደው ማለቱ ይቀላል።

“በመሠረቱ ይህ ድጎማ ሲጀመርም በፖሊሲ ተደግፎ አያውቅም” ይላሉ የነዳጅና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር በቀለች ኩማ።

“ነዳጅ እንዲሁ በቁጥጥር ሥርዓትና በዋጋ ማረጋጊያ ሰነድ የሚመራ እንጂ በፖሊሲ የተደገፈ የድጎማ ሥርዓት ኖሮት አያውቅም።”

ለነዳጅ ሁነኛ መመሪያ የወጣለት ከሦስት ዐሥርታት በፊት ነው። በ1993 ዓ.ም. የነዳጅ ፈንድ ተመሠረተ።

የነዳጅ ፈንድ ዋጋን የማረጋጋት ሚናን እንዲጫወት ነበር የታሰበው።

ይህም ማለት መንግሥት ከዓለም ገበያ ነዳጅ ይገዛል። ከዚያ አገር ውስጥ ሲሸጥ ሽርፍራፊ ሳንቲሞችን ወደዚህ የነዳጅ ፈንድ እያስገባ ያጠራቅማል።

ለምሳሌ ነዳጅ ተገዝቶ ተተምኖ ወደ ገበያ ሲወጣ 21 ብር ከ80 ሳንቲም ቢሆን መንግሥት 22 ብር ይሸጠውና 20 ሳንቲሟ ተጠራቅማ ለሚቀጥለው ድጎማ ትውላለች።

በዚህ አሠራር የተወሰኑ ቢሊዮን ብሮች በዚህ የነዳጅ ፈንድ እየተጠራቀሙ ቆዩ።

ኾኖም ነዳጅ የሚጨምርበት ፍጥነትና ይህ ፈንድ የሚለቃቅማቸው ሳንቲሞች ሊገናኙ አልቻሉም።

የእርምጃና የ100 ሜትር ሩጫ ተወዳዳሪዎችን በአንድ መም የማሮጥ ነገር መሰለ።

ይህ ሁኔታ በተለይ ከ2003 ዓ.ም. ወዲህ ጭራሽ ሊገናኝ አልቻለም።

ከዚህ ወዲያ ነበር ከመንግሥት ካዝና ቢሊዮን ብሮች እየወጡ ነዳጅን በቀጥታ መደጎም የተያዘው።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነዳጅ ድጎማው በየወሩ እየተከለሰ ዋጋው ከዓለም ዋጋ ከፍና ዝቅ ጋር እየተነጻጸረ እንዲስተካከል ይደረግ ነበር።

“ይሁንና ከ2009 ጀምሮ የነዳጅ ዋጋ የተከለሰው ለ5 ጊዜ ብቻ ነው’’ ይላሉ በቀለች ጫናውን ምን ያህል መንግሥት ተሸክሞት እንደቆየ ለቢቢሲ ሲያስረዱ።

ይህ ግን አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ሁኔታ አንጻር የሚያስቀጥል አልሆነም።

በዚህ የተነሳ አገሪቱ ከነዳጅ ጋር በተያያዘ በቀጣይ አካሄዷን ለማስተካከል ተገዳለች።

የዓለም ዋጋን ያንጸባረቀ ዋጋን ከሕዝብ ጋር ለመጋራት ቆርጣለች። ሕመሜን አስታሙልኝ ነው ነገሩ።

ድጎማውን ለማንሳት ጊዜው አሁን መሆን ነበረበት?

በዚህ ጊዜ ለምን እዚህ ውሳኔ ላይ ተደረሰ? ስንል የነዳጅና ኢነርጂ ሚኒስትር መሥሪያ ቤትን ጠይቀናል።

“በዚህ ኑሮ እሳት በሆነበት ጊዜ መሆኑ አደጋ የለውም ወይ?’’ ስንል የምጣኔ ሃብት አዋቂዎችን አወያይተናል።

በቀለች ኩማ ድጎማውን በዚህ ወቅት ማንሳቱን የሚመለከቱት በተለየ መነጽር ነው።

ነገሩን መንግሥት ላይ እያሳደረ ካለው የዕዳ ጫና ብርቱነት፣ የዓለም የነዳጅ ዋጋ መቀጣጠል እና ከሕገ ወጥ ንግድ መበራከት አንጻር መመልከትን ይመርጣሉ።

“ድጎማው ከጥቅሙ ጉዳቱ በዛ” የሚሉት በቀለች በዋቢነት የሚያነሱት ሕገ ወጥ የኮንትሮባንድ ነዳጅ ንግድ መበራከትን ነው።

ይህ አየር በአየር ሽያጭ አገሪቱን ለከፍተኛ ዕዳ ዳረጋት። በውድ የውጭ ምንዛሬ የሚደጎመው ነዳጅ እያከበረ ያለው ኮንትሮባንዲስቶችን ነው፤ ባለጸጎችን ነው፤ ሲሉ ያስረዳሉ።

እርግጥ ሕዝብ ይደጉማል የተባለ ውድ ነዳጅ ማደያ ሳይደርስ ጎረቤት አገር ይቸበቸብ እንደነበር አገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው።

ቢሆንም ግን በዚህ ወቅት ቁጥጥርን ማጥበቅ እንጂ ድጎማን ማንሳት ያስኬዳል?

ይህ ብቻ ግን አይደለም ድጎማ የማንሳቱ መንስኤ ይላሉ በቀለች፣ “ድጎማው በፖሊሲም ያልተደገፈ ከመሆኑ የተነሳ ጥቅል ድጎማ ነው የነበረው።’’

እርግጥ ድጎማው የጅምላ ድጎማ መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይም አጥብቀው የሚኮንኑት ጉዳይ ነው።

ጥቅል ድጎማ ሲባል ምን ማለት ነው?

ሃብታምና ድሃን፣ ቤንትሌና ሃይገርን፣ ሊሞዚን፣ መርሴዲስን እና ‘ቅጥቅጥ አይሱዙን’ በእኩል መደጎም ማለት ነው።

ኢኮኖሚስቱ አቶ ዋሲሁን፣ “መንግሥት የኤምባሲ መኪናንም የከተማ አውቶቡስንም በአንድ ሲደጉም ነው የኖረው” የሚሉት ለዚሁ ነው።

የእስከዛሬው የነዳጅ ድጎማ ከመሠረታዊ የድጎማ (subsidy) ጽንሰ ሐሳብ ጋር የሚጻረር እንደነበር ቢቢሲ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሃብት አዋቂዎች የሚስማሙበት ነጥብ ነው።

ድጎማ በባህሪው የአጭር ጊዜ መፍትሄ ነው።

የአጭር ጊዜ መሆን ብቻም ሳይሆን ማሳካት የፈለገው ግብ በውል ተለይቶ መቀመጥ አለበት። መቀመጥ ብቻም ሳይሆን ዓላማውን አሳክቷል ወይ ተብሎ መፈተሽ አለበት። ሁሉም ባለሙያዎች የሚሉት ይህንን ነው።

በዚህ ሚዛን ላይ ሲቀመጥ ድጎማው ውሉን የሳተ ነበር ብለው ያምናሉ አቶ ዋሲሁን። እሳቸው መደጎም ያለበት የሚሉት በዋናነት ምርትን ማሳደግ የሚችለውን ዘርፍ ነው።

ነዳጅ በኢትዮጵያ ሁለት ሚና አለው፤ አንዱ ለፋብሪካዎች የኃይል ምንጭ መሆን ነው፤ ሌላው ትራንስፖርት ነው።

በኢትዮጵያ ብዙ አምራች ተቋማት የማምረት አቅማቸው 40 ከመቶ አይሞላም። አንዱ ምክንያታቸው ታዲያ በቂ ኃይል ስለማያገኙ ነው። ስለዚህ መብራት በጠፋ ጊዜ ጄኔሬተር ይለኩሳሉ። ጄኔሬተር ነዳጅ ይጠጣል።

ለእነዚህ አምራቾች ቢቻል አስተማማኝ ኃይል ማቅረብ ወይም መደጎም ምርታማነትን ይጨምራል። የኤምባሲ መኪናን ነዳጅ መደጎም ግን ምርታማነት አይጨምርም።

ነዳጅን የምትደጉመው ኢትዮጵያ ብቻ ናት?

ጥቂት የማይባሉ አገራት ነዳጅን ይደጉማሉ። ካልደጎሙም የኅብረተሰቡ የመግዛት አቅማቸው ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል።

ታዲያ ድጎማ ግቡ ምንድነው?

“ማክሮ ኢኮኖሚ እንዳይዛባ፣ ምርትና ምርታማነት እንዳይጎዳ፣ ባለመደጎም የሚመጣ ውስብስብ ኢኮኖሚያዊ መዘዝ ሲኖር ድጎማ አግባብ ሆኖ ሊታይ ይችላል’’ ይላሉ አቶ ዋሲሁን።

“ይሄ መንግሥት ግን ከአቅሙ በላይ ብዙ ነገር የሚደጉም መንግሥት ነው፤ ክፋቱ ደግሞ መደጎም የሌለበትንም ይደጉም ነበር።”

መቅደም ያለባቸው ነገሮች

ለነዳጅ ድጎማ የሚወጣው ከፍተኛ ገንዘብ የኢትዮጵያ መንግሥትን ጀርባው መጉበጡን የምጣኔ ሃብት አዋቂው አቶ አየለ ገላን ያምናሉ።

ነዳጅ በኢትዮጰያ የሚሸጥበት ዋጋ አገሪቱን ነዳጅ አምራች እንዳስመሰላትም አልሸሸጉም።

የእርሳቸው ልዩነት የሚነሳው ድጎማን በማንሳት ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ነው።

“የኢትዮጵያ ሸማች የመግዛት አቅም ደቃቃ ነው። ከሕዝብ አንጻር ስናየው እንዲያውም ድጎማው በቂ አልነበረም ልንል እንችላለን’’ ካሉ በኋላ መንግሥት ከድጎማ በፊት መሥራት የነበረበትን የቤት ሥራ አልሠራም ሲሉ ሂደቱን ክፉኛ ይተቻሉ።

እነዚህ የቤት ሥራዎች ምን ነበሩ?

“አንደኛ ኢኮኖሚው ተመሰቃቅሏል። ምርት አላደገም፣ የሕዝብ የመግዛት አቅም አልጨመረም። ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች በእግራቸው እንዲቆሙ አልተደረገም። የሕዝብ ደኅንነት አልተጠበቀም።...”

መንግሥት እነዚህን መልከ ብዙ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ምስቅሎሽን ሳያስተካክል፤ ኢኮኖሚውን ጠንካራ መሠረት ላይ ሳያስቀምጥ ድጎማ ማንሳት (የእርሳቸው ቃል ለመጠቀም) “ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ነው።’’

የድጎማው ገንዘብ ምን ላይ ይውላል?

አቶ ዋሲሁን ከድጎማው መነሳት ማግስት ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለውን ትንቢታዊ ጥያቄ በቀጥታ መጋፈጥን የመረጡ አይመስልም።

ነገር ግን የመንግሥት ድጎማን የማንሳት ውሳኔን ከጥንቃቄ ጋር በአውንታዊ መልኩ ይረዱታል።

“የድጎማ ሥርዓቱ (በአንድ ጥናት ላይ እንደታየው) 70 ከመቶ የሚሆነውን ድሃና 30 ከመቶ የሚሆነውን ሃብታም ነው ሲደጉም የኖረው። ስለዚህ ጤናማ ድጎማ አልበረም። ለድሃ የታሰበው ድጎማ ሃብታም ሲደጉም ነው የኖረው።’’

ስለዚህ በእሳቸው ዕይታ ከዚህ ወዲህ ድጎማው ለታሰበለት ሕዝብ ብቻ ስለመድረሱ እርግጠኛ መሆን ያሻል።

“ድጎማ ዘዴኛና መለኛ (ታክቲካል) ካልሆነ ውሉን ሳተ ማለት ነው። ድሃው ነው የሚደጎመው ከተባለ ድጎማው ድሃው ጋር መድረሱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል’’ የሚሉት አቶ ዋሲሁን ነዳጅ በሞያሌ እየወጣ ሲሸጥ፣ አውቶቡስና የኤምባሲ መኪና አብሮ ተሰልፎ በአንድ የዋጋ ተመን ነዳጅ ሲቀዳ ድጎማ ግብ እንደተሳተ ምልክቶች ሆነው ይታያሉ።

በዚህ ሐሳብ የነዳጅና ኢነርጂ ሚኒስትርም ባልደረባም ይስማማሉ። “የሚደጎምና የማይደጎምን በጥናት መለየት ያስፈለገውም ለዚሁ ነው ይላሉ” በቀለች ኩማ።

ከድጎማ የተረፈው ገንዘብ ምን ላይ ይውል ይሆን?

አቶ ዋሲሁን ከድጎማ መነሳቱ ይልቅ ከድጎማ የዳነው ገንዘብ የት እንደሚውል በእጅጉ ያሳስባቸዋል።

“አሁን ያለው ኢኮኖሚ በግጭትና በጦርነት የቆሰለ ኢኮኖሚ ነው። ከፍተኛ ወጪዎች ይጠብቁታል። በወጪና ገቢ ልዩነት ማጥበብ ላይ ካልተሠራ የከፋ ሀኔታ ሊመጣ ይችላል” ይላሉ።

ከፍተኛ የበጀት ጉድለት ደግሞ ወደ ገንዘብ ማተም ስለሚወስድ ለበለጠ የበጀት ቅርቃርና ኑሮ ውድነት ሊወስድ ይችላል የሚል ፍርሃት አላቸው።

ስለዚህ መንግሥት ከድጎማ ወጪ ያዳነውን ገንዘብ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሊያውለው ይገባል።

“መንግሥት ማኅበረሰቡ ወጪውን እንዲጋራው መሞከሩ መጥፎ ነው ወይ? ብትለኝ እኔ መጥፎ ነው ብዬ አላስብም። ነገር ግን ገንዘቡ ለአበልና ለድግስ ከዋለ ነው ችግሩ።”

መንግሥት ድጎማውን አለማንሳት ይችል ነበር?

 አሁን በዓለም ገበያ ሰማይ የነካውን ነዳጅ መንግሥት በግማሽ ቀንሶ ነው ለሕዝብ የሚያደርሰው። ቀድም ባሉ ዓመታት በሊትር 5 እና 6 ብር ነበር የሚደጉመው። አሁን ያን ለማድረግ የሚያስችል አቅምን አጥቷል። በውስጣዊና ውጫዊ ዝርዝር ምክንያቶች።

ምክንያቶቹን አቆይተን ነገር ግን መንግሥት በዚህ ድጎማ አሠራር ከሐምሌ ወዲያ መሻገር ይችል ነበር ወይ ብለን እንጠይቅ።

በሌላ አነጋገር መንግሥት ደግ ሆኖ ልደጉም ቢልስ ይችላል ወይ?

የብዙ ኢኮኖሚስቶች ምላሽ በአጭሩ ሲቀመጥ “አይችልም” የሚል ነው።

ምክንያቱም፣ “...ሚያዝያ ወር ላይ ብቻ ዕዳው 124 ቢሊዮን ደርሰ” ይላሉ የነዳጅና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባልደረባ በቀለች ኩማ።

ምክንያቱም፣ “...561 ቢሊዮን ብር ይዞ የተነሳ ኢኮኖሚ ነው ያለው። በዚህ ዓመት በዘጠኝ ወር የተሰበሰበው 290 ቢሊዮን ብር ነው። ልዩነቱ ሰፊ ነው። ይህን የበጀት ጉድለት ይዞ ብዙ መጓዝ አይቻልም” ይላሉ አቶ ዋሲሁን።

ይሁንና ነዳጅ ድጎማው የኑሮ ውድነቱን እንዳያባብስ ምን ማድረግ ይቻላል?

አቶ ዋሲሁን የነዳጅ ድጎማው በኑሮ መወደድ ላይ የሚያስከትለውን ጣጣ ማንም አያጣውም ይላሉ። ነገር ግን ያን ማስቀረት በምጣኔ ሃብት ሳይንስ የሚቻልበትን ዕድል አይታያቸውም።

“የትኛውም ፖሊሲ ሁሉን አስታርቆ መሄድ አይችልም። ሁሉንም ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አስደስቶ የሚያቆይ የኢኮኖሚ ውሳኔ በምድር ላይ የለም።’’

ይልቅ በቀጥታ በድጎማ መነሳት ብቻ የሚፈጠር ዋጋ ንረት ሳይሆን ድጎማ የመነሳቱ ወሬ በራሱ የሚፈጥረው የገበያ ትኩሳት ይበልጥ ያሳስባቸዋል።

“እኛ አገር ነጋዴው በአጋጣሚው እንዴት በአቋራጭ ልክበር ነው የሚለው፤ የድጎማውን ጭማሪ ብቻ ደምሮ ይሸጣል ብዬ አልገምትም” ይላሉ አቶ አየለ ገላን።

“ታክሲም ሆነ የሕዝብ አውቶቡስ የምንደጉመው ለ5 ዓመት ብቻ ነው”

ከሐምሌ ወዲህ የሕዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪ ማደያ ገብቶ ነዳጅ ሲቀዳ ጂፒኤስ ተገጥሞለት ነው። ነዳጅ አቅራቢዎች ለማደያዎች ደረሰኝ ይሰጣሉ። ባለታክሲው በታሪፍ የተቀመጠውን ዋጋ ከፍሎ ይሄዳል። ማደያው በደረሰኝ ቀሪውን ያወራርዳል።

ይህ አሠራር በመተግበሪያ የሚሠሩት ታክሲዎችን አይጨምርም። የመንግሥት ሰርቪሶችንም አይጨምርም።

“ከዚህ በኋላ በየትኛውም ማደያ ነዳጅ ሲራገፍ የኛ ተቆጣጣሪዎች በያንዳንዱ ማደያ ተገኝተው ነው” ይላሉ የነዳጅና ኢንርጂ ሚኒስቴር ባልደረባ በቀለች ኩማ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሕዝብን ለማረጋጋት ይመስላል መንግሥት ድጎማ ማንሳቱ በኑሮ ላይ አንዳችም ጫናን አይፈጥርም የሚሉ ድምጾች እየተስተጋቡ ነው።

ይህ ለምጣኔ ሃብት አዋቂዎችም ሆነ ለሰፊው ሕዝብ እምብዛምም ስሜት የሚሰጥ አይደለም።

በቀለች ኩማ ግን “ድጎማ መነሳቱ በቀጥታ የሚባለውን ያህል የዋጋ ንረት አያስከትልም፤ ይህ በጥናት የተረጋገጠ ነው” ሲሉ የነገሩን ሀቅነት ይሞግታሉ።

እሳቸው ጥናቱን ለቢቢሲ ለማጋራት ባይፈቅዱም የነዳጅ ድጎማ መነሳት በቀጥታ የሚያስከትለው የዋጋ ንረት እዚህ ግባ የሚባል እንዳይደለ ይጠቅሳሉ።

“...ድጎማው ሲነሳ በእያንዳንዱ ሸቀጥ ላይ የሚያመጣው ጫና በሳንቲም ቤት እንደሆነ ተደርሶበታል” ይላሉ።

ይሁንና ምጣኔ ሃብት ሙያተኞቹ አቶ ዋሲሁን እና አቶ አየለ ግን በዚህ ብዙም አይስማሙም።

አንዱ ምክንያታቸው በኢትዮጵያ የንግድ ዘይቤ እንደታየው ዋጋ የሚወሰነው በቀጥታ በሚመጣ ጭማሪ ሳይሆን ገና በሥነ ልቦና በሚፈጠር ፍርሃትም ጭምር ስለሆነ ነው።

ለብዙዎች አዲስ ዜና የሆነው ደግሞ የታለመላቸው የሚባሉት ተደጓሚዎችም ቢሆኑ ድጎማቸው ጊዜያዊ መሆኑ ነው።

በቀለች ሁሉም ታክሲዎችና የሕዝብ አውቶቡሶች ሳይቀሩ በሂደት ከድጎማ ሥርዓት እንደሚወጡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በአምስት ዓመት ውስጥ ከድጎማው ሙሉ በሙሉ ይወጣሉ። በየሦስት ወሩም ዋጋ ክለሳ ይደረግባቸዋል።”

“የዚምባብዌ ዓይነት ግሽበት እንዳይፈጠር እሰጋለሁ”

የሰዉ ስሜቱ የተዘበራረቀ ነው።

ኑሮ መንደድ ያለበትን ያህል በመንደዱ ከዚህ በላይ ምን ሊመጣ? የሚል ስሜት ያላቸው አሉ።

ነገን በፍርሃትና በሰቀቀን የሚጠብቁም አሉ።

ድጎማው ሐምሌ ላይ ሲነሳ የዋጋ ጭማሪው እንደ ሐምሌ ዝናብ ዶፍ ሆኖ ሊወርድ የተሰናዳ ይመስላል።

ሐምሌ አሳሳቢ ሆኖ የሚታየው ታዲያ ለተርታው ሕዝብ ብቻ አይደለም። ለጎምቱ ኢኮኖሚስቶችም ጭምር እንጂ።

መቀመጫቸውን ኩዌት ያደረጉት አቶ አየለ ገላን፤ “በዚህ ጊዜ ድጎማን ማንሳት ለእኔ ስሜት የሚሰጥ አይደለም፤ ዚምባብዌ ወደ ገጠማት ኢኮኖሚ ሁኔታ የመንደርደር ያህል አድርጌ ነው የምመለከተው” ይላሉ።

ምርትና ምርታማነት ፈቅ ሳይል፣ መሠረታዊ የኑሮ ደረጃ ኢምንት ሳይጨምር የገጠሩ የግብርና ኢኮኖሚ ሳያድግ አሁን ባለው ኢኮኖሚ ላይ የነዳጅ ድጎማን ማንሳት ከድጡ ወደ ማጡ ነው፤ ለእርሳቸው።

በቀለች ኩማ ግን የተቀናጀ ቁጥጥርና በቂ ግንዛቤ ለኅብረተሰቡ ከደረሰ የከፋ ሁኔታ አይመጣም ባይ ናቸው።

አቶ አየለ በፍጹም በዚህ አይስማሙም፤ በዚህ እሳት በሆነ ኑሮ ይህን መሠረታዊ የነዳጅ ድጎማን ማንሳት “እየነደደ ባለ እሳት ላይ ነዳጅ ማርከፍከፍ ነው” ይሉታል።