በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሆነው የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ከባለፈው ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል ጭማሪ አሳየ?

የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መናሩን በምክንያትነት በመጥቀስ ከአራት ወራት በፊት ባወጣው የዋጋ ተመን ላይ ከሚያዝያ 30/2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ መንግሥት ባለፉት አራት ወራት የነዳጅ ዋጋን ለመደጎም ባወጣው ወጪ ከፍተኛ ጫና ላይ መውደቁን ያተተ ሲሆን "በነዳጅ ማረጋጊያ ፈንድ ላይ በወር በአማካይ ወደ ተጠቃሚው መተላለፍ የነበረበት 10 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንዲመዘገብ" አድርጓል ሲል አክሏል።

በዚህም ምክንያት ከእሁድ ሚያዝያ 30 ጀምሮ በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ለውጥ ተደርጓል።

ቤንዚን በሊትር 36 ብር ከ87 ሳንቲም፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር 35 ብር ከ43 ሳንቲም፣ ኬሮሲን በሊትር 35 ብር ከ43 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ በሊትር 52 ብር ከ45 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ በሊትር 51 ብር ከ78 ሳንቲም እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ በሊትር 78 ብር ከ87 ሳንቲም ሆኖ እንደሚሸጥ መወሰኑንም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው።

ተግባራዊ ከተደረገው የተመን ማሻሻያ በፊት ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት ታኀሣሥ ወር ላይ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ ላይ ጭማሪ አድርጋ ነበር። የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በእነዚህ አራት ወራቶች ውስጥ የነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ "በከፍተኛ ሁኔታ" መጨመሩን ገልጿል።

በዚህም በታኅሣሥ ወር ቤንዚን በሜትሪክ ቶን 870 የአሜሪካን ዶላር ይሸጥ እንደነበር ጠቅሶ ከአራት ወራት በኋላ ዋጋው በ27 በመቶ በመጨመር 1028 የአሜሪካ ዶላር መግባቱን አስታውሷል።

በተመሳሳይ ናፍጣ በሜትሪክ ቶን 730 የአሜሪካን ዶላር ይሸጥ ከነበረበት በ55 በመቶ ወይም በ408 ዶላር ጭማሪ በማሳየት ወደ 1138 የአሜሪካን ዶላር ማሻቀቡን አውስቷል።

ሚኒስቴሩ በመግለጫው መንግሥት ለነዳጅ የሚያደርገውን ድጎማ ቢያቆም በአዲስ አበባ አንድ ሊትር ናፍጣ 73 ብር እንዲሁም የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ 66 ብር ከ78 ሳንቲም ይሆን ነበር ብሏል።

"ሆኖም አገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ከዓለም መሸጫ ዋጋ ልዩነትን 85 በመቶ የሚሆነውን ጫና መንግሥት በመሸከም፣ ቀሪውን 15 በመቶ ለተጠቃሚው እንዲተላለፍ በመወሰን የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ መጠነኛ ክለሳ" ማድረጉን አሳውቋል።

የነዳጅ ዋጋ በታኅሣሥ እና ሚያዚያ ምን ያህል ልዩነት አለው?

መንግሥት በታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መጨመሩን በመግለጽ ጭማሪ ማድረጉን አስታውቆ ነበር። ለመሆኑ ከታኅሣሥ እስከ ሚያዚያ መገባደጃ በኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ በምን ያህል ጫማሪ አሳየ?

በዋጋ ጭማሪው እንደ ጥቁር ናፋጣ ያሉ ምርቶች በሊትር እስከ 121 በመቶ ጭማሪ ወይም እስከ 28 ብር ያሻቀቡ ሲሆን ዝቅተኛው የዋጋ ማሻሻያ ጣሪያ ቤንዝን ላይ የተደረገው ሲሆን የ15 በመቶ ጭማሪ የታየበት ነበር።

በታኅሣሥ ወር ቤንዚን ላይ በተደረገ የዋጋ ማስተካከያ በሊትር 31 ብር ከ74 ሳንቲም እንዲሸጥ ተወስኖ የነበረ ሲሆን በአዲሱ ተመን መሰረት በሊትር 36 ብር ከ87 ሳንቲም ይሸጣል። በዚህ መሰረት የቤንዚን ዋጋ በ15 በመቶ ወይም በ4 ብር ከ87 ሳንቲም ጫማሪ አሳይቷል።

በሌላ በኩል ከአራት ወራት በፊት ነጭ ናፍጣ በሊትር 28 ብር ከ94 ሳንቲም እንዲሸጥ ነበር የተወሰነው። አሁን ላይ ነጭ ናፍጣ በ22 በመቶ ወይም በ6 ብር ከ49 ሳንቲም በመጨመር በሊትር 35 ብር ከ43 ሳንቲም ይሸጣል።

ነጭ ጋዝ ወይም ኬሮሲን 28 ብር ከ94 ሳንቲም ሲሸጥ የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ ተመን በሊትር 35 ብር ከ43 ሳንቲም ይሸጣል። ይህም የ22 በመቶ ወይም 6 ብር ከ49 ሳንቲም ጭማሪ የታየበት ነው።

ቀላል ጥቁር ናፍጣ በታኅሣሥ ወር የወጣለት ተመን 23 ብር ከ73 ሳንቲም የነበረ ሲሆን በአዲሱ የመሸጫ ዋጋ በ121 በመቶ ወይም 28 ብር 72 ጨምሮ በሊትር 52 ብር ከ45 ሳንቲም እንዲሸጥ ተወስኗል።

ይህ በተመሳሳይ የከባድ ጥቁር ናፍጣም ዋጋ በ121 በመቶ ወይም 28 ብር 49 በማሻቀብ በሊትር ሲሸጥበት ከነበረው 23 ብር ከ29 ሳንቲም ወደ 51 ብር ከ78 ከፍ ብሏል። የከባድ እና ቀላል ናፍጣ ዋጋ ማሻሻያ ከሌሎቹ የነዳጅ አይነቶች እጅግ ከፍተኛው ሆኖ የሚታይ ነው።

የአውሮፕላን ነዳጅ ደግሞ በሊትር ከ58 ብር ከ77 ሳንቲም ወደ 78 ብር ከ87 ሳንቲም ያሻቀበ ሲሆን የ33 በመቶ ወይም 20 ብር ጭማሪ አሳይቷል።

የነዳጅ ምርቶች የዋጋ ጭማሪ በአራት ወራት ውስጥ - በሊትር

  • ቤንዚን ከ31 ብር ከ74 ወደ 36 ብር ከ87 ሳንቲም [15% ጭማሪ]
  • ነጭ ናፍጣከ28 ብር ከ94 ወደ 35 ብር ከ43 ሳንቲም [22% ጭማሪ]
  • ነጭ ጋዝ/ኬሮሲን ከ28 ብር ከ94 ሳንቲም ወደ 35 ብር ከ43 ሳንቲም [22% ጭማሪ]
  • ቀላል ጥቁር ናፍጣከ23 ብር ከ73 ወደ 52 ብር ከ45 ሳንቲም [121 % ጭማሪ]
  • ከባድ ጥቁር ናፍጣ ከ23 ብር ከ29 ሳንቲም ወደ 51 ብር ከ78 [121 % ጭማሪ]
  • የአውሮፕላን ነዳጅከ58 ብር ከ77 ሳንቲም ወደ 78 ብር ከ87 [33 % ጭማሪ]

ከወራት በፊት ሩሲያ እና ዩክሬን የገቡበት ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ እንዲያሻቅብ ሰበብ ሆኗል። ሩሲያ የዓለምን 10 በመቶ ገደማ የሚሆን የነዳጅ ምርት ታቀርባለች።