በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር

ምንም እንኳን በዓለም ገበያ ላይ ዋጋው ቢጨምርም ለወራት ባለበት የቆየው የኢትዮጵያ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ማስተካከያ መደረጉን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቋል።

በዚህም መሠረት በመላው አገሪቱ በታኅሣሥ ወር የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ አዲስ የዋጋ ማስተካከያ የተደረገ ሲሆን፤ በዚህም በተለያዩ የነዳጅ እምርቶች ላይ ቀላል የማይባል ጭማሪ ታይቷል።

በዚህ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ካስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል፤ የዓለም አቀፍ የነዳጅ ምርቶች መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ መኖሩና ከጎረቤት አገራት ጋር ሲነጻጸር በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ የነዳጅ ምርቶች ለከፍተኛ ኮንትሮባንድ መጋለጡ ተጠቅሷል።

የኮሮናቫይረስ ክስተትን ተከትሎ የነዳጅ ፍላጎት ዝቅ በማለቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቶ የቆየ ቢሆንም፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ዋጋው ቀስበቀስ እየጨመረ አሁን ካለበት ላይ ደርሷል።

ባለፉት ወራት ጭማሪው ያለመቋረጥ የቀጠለ ሲሆን፣ በወረርሽኙ ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው የዓለም ምጣኔ ሀብት ለማንሰራራትና ወደነበረበት ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የነዳጅ ፍጆታ ከፍ እያለ መሆኑ ለዚህ ተጠቃሽ ነው።

በኢትዮጵያ የተደረገው የዋጋ ክለሳ

ለወራት በሊትር 25 ብር ከ85 ሳንቲም ይሸጥ የነበረው ቤንዚን፤ አሁን በተደረገው የዋጋ ማስተካከያ አንድ ሊትር ቤንዚን 31 ብር ከ74 ሳንቲም እንዲሸጥ ተወስኗል።

ይህም ከስደስት ብር በላይ ጭማሪን በአንድ ሊትር ላይ ያስከተለ ሲሆን፣ ጭማሪው በሌሎችም ሸቀጦችና አገልግሎቶች ላይ ሊንጸባረቅ እንደሚችል ከዚህ ቀደም የታዩት ልምዶች ያመለክታሉ።

ነጭ ናፍጣ 28 ብር ከ94 ሳንቲም፣ ነጭ ጋዝ 28 ብር ከ94 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ 23 ብር ከ73 ሳንቲም እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ 58 ብር ከ77 ሳንቲም በሊትር ከኅዳር 30 ቀን 2014 ጀምሮ እንደሚሸጥ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ኢትዮጵያ የነዳጅ ዋጋ ከጎረቤት አገራት ሲነጻ

በየጊዜው እየተደረገ ካለው የዋጋ ጭማሪ ጋር ቢሆንም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኙ አገራት ነዳጅ በአነስተኛ ዋጋ ከሚሸጥባቸው አገራት መካከል ተጠቃሽ ነች።

በዓለም ዙሪያ ባሉ አገራት ውስጥ የነዳጅ መሸጫ ዋጋን እንደሚያቀርበው 'ስታቲስታ' መረጃ ከሆነ ኢትዮጵያ ነዳጅ አምራች ከሆኑት አንጎላ፣ ናይጄሪያ እና አልጄሪያ በመቀጠል በአፍሪካ ውስጥ በአስተኛ ዋጋ የነዳጅ ምርቶች ለሕዝቧ የምታቀርብ አገር ናት።

የኢትዮጵያ ጎረቤት የሆነችው ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኬንያ በቀጠናው ካሉ አገራት ነዳጅ በውድ የምታቀርብ አገር እንደሆነች ይነገራል። በስታቲስቲክስታይምስ መረጃ መሠረት በኬንያ 1 ሊትር ነዳጅ 1.19 ዶላር ይሸጣል።

ከኬንያ በመከተል በአካባቢው ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ያላቸው አገራት ሱዳን እና ኡጋንዳ ሲሆኑ፤ ነዳጅ የምታመርተው ሱፋን በሊትር 1.03 ዶላር ስታስከፍል፣ በቅርቡ የነዳጅ ዘይት ያገኘችው ኡጋንዳ ደግሞ አንድ ሊትር በ1.09 የአሜሪካ ዶላር ታቀርባለች።

በዓለም ላይ ዜጎቿን አነስተኛ የነዳጅ ዋጋ የምታስከፍለው ነዳጅ አምራች የሆነችው እና ምጣኔ ሀብቷ ክፉኛ የተጎሳቆለባት ቬንዙዌላ ነች። እንደ ግሎባል ፔተሮል ፕራይስ ከሆነ በቬንዙዌላ በ1 የኢትዮጵየ ብር (0.02 የአሜሪካ ዶላር) አንድ ሊትር ነዳጅ መሸመት ይቻላል።

በአፍሪካ ነዳጅ በከፍተኛ ዋጋ ከሚሸጡባቸው አገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ ተጠቃሽ ናት። በመረጃው መሠረት በደቡብ አፍሪካ አንድ ሊትር ነዳጅ የሚሸጠው በ1.25 ዶላር ነው።

የበለጸጉት እንደ ኔዘርላንስ፣ ኖርዌይ፣ ጣሊያ እና ሆንግ ኮንግ ለአንድ ሊትር ነዳጅ ከ2 የአሜሪካ ዶላር በላይ (ወደ 95 ብር ገደማ) ይጠይቃሉ።

ነዳጅ የማታመርተው ኢትዮጵያ፤ ነዳጅ አምራች ከሆኑ አገራት በላይ በአነሰ ዋጋ ነዳጅ ለዜጎች ታቀርባለች።

ይህ የሆነውም መንግሥት ለዘረፉ በሚያደርገው ድጎማ ምክንያት ነው። አገሪቱ ከዓመታዊ በጀቷ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ መድባ ነዳጅ ታቀርባለች።

ኢትዮጵያ ነዳጅ የምታስገባው ከየት ነው?

ኢትዮጵያ ለፍጆታዋ የሚውለውን ነዳጅ ከተለያዩ ነዳጅ አምራች አገራት የምታስገባ ሲሆን፣ በዋናነት ከመካከለኛው ምሥራቅና የባሕረ ሰላጤው አገራት ታገኛለች።

በዚህም መሠረት በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ የሚያስፈልጋትን የነዳጅ ዘይት ከሳዑዲ አረቢያ እና ከኩዌት በማስመጣት ላይ እንደምትገኝ የነዳጅ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት እንደሚለው በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚገባበት ብቸኛው መንገድ በጂቡቲ ወደብ በኩል ባለው መስመር ነው።

ከአራት ወራት በፊት ቢቢሲ ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ባገኘው መረጃ መሠረት ለአገሪቱ ፍጆታ በየዕለቱ 2.5 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን እና 8 ሚሊየን ሊትር ናፍጣ ይቀርባል ።

ይህንንም ለማሟላት በየዓመቱ ለአገሪቱ ፍጆታ የሚያስፈልገውን የነዳጅ መጠን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን፣ ኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በዓመት ምን ያህል የነዳጅ አቅርቦት እንደሚያስፈልግ የተለያዩ መረጃዎችን በመመርኮዝ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ያቅዳል። ።

ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸው የነዳጅ ምርቶች አምስት ዓይነት ናቸው። እነዚህም ቤንዚን፣ ናፍጣ፣ የአውሮፕላን ነዳጅና ለኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውሉ ሁለት ዓይነት ናፋጣዎች ናቸው።

በዚህም መሠረት ቤንዚን በዓመት እስከ 700 ሺህ ሜትሪክ ቶን፣ 2.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ናፍጣ፣ 600 ሺህ ሜትሪክ ቶን የአውሮፕላን ነዳጅና እስከ 70 ሺህ ሜትሪክ ቶን የተለያየ አይነት የኢንዱስትሪ ናፍጣ በየዓመቱ እንደሚገባ ታደሰ ኃይለማርያም ተናግረው ነበር።