በኢትዮጵያ ለሚታየው የነዳጅ እጥረት ምክንያቱ ምንድን ነው?

በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ አሽከርካሪዎች ነዳጅ ለመቅዳት ለሰዓታት ረጅም ሰልፍ ለመጠበቅ ከተገደዱ ቀናት ተቆጥረዋል።

በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን ተከትሎ መንግሥት ለዓመታት ለነዳጅ ሲያደርግ የነበረውን ድጎማ ቀስ በቀስ ለማቋረጥ ወስኖ ተግባራዊ ለማድረግ እየተዘጋጀ ነው።

ኢትዮጵያ ለነዳጅ የምታደርገው ድጎማ ነዳጅ ለሁሉም ተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ አስችሎ ቆይቷል፤ ነገር ግን ይህ ድጎማ ከዚህ በኋላ ዘላቂ እንደማይሆን በነዳጅና ፔትሮሊየም ባለሥልጣን ውስጥ የሚሰሩ አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን የነዳጅ ስታንዳርድ ጥናት ዳይሬክተር አቶ ለሜሳ ቱሉ እንደሚሉት መንግሥት ለነዳጅ በሚያደርገው ድጎማ ምክንያት በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወጪ ያደርጋል።

በግንቦትና በሰኔ መካከል ባሉ ሰላሳ ቀናት ውስጥ ብቻ መንግሥት 16 ቢሊዮን ብር ወይም 268 ሚሊዮን ዶላር ነዳጅን ለመደጎም ሲል ወጪ ማድረጉን አቶ ለሜሳ ተናግረዋል።

ከዋጋ ጭማሪው ባሻገር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚከሰቱት ግጭቶች የትራንስፖርት መስመሮችን በማስተጓጎል በቅርብ ወራት ውስጥ የነዳጅ አቅርቦት ችግር በአገሪቱ ውስጥ እንዲከሰት ምክንያት እየሆኑ ነው።

ነገር ግን አሁን ለተከሰተው የነዳጅ እጥረት መባባስ ከጂቡቲ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን ነዳጅ መድረስ ካለባቸው ቦታ ውጪ መውሰድና የነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ትራንስፖርት መዘግየት ምክንያት እንደሆነ አቶ ለሜሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አንዳንድ አከፋፋዮችም መንግሥት በተወሰነ ደረጃ ድጎማውን በማንሳት አዲስ የነዳጅ ታሪፍ ይፋ በሚያደርግበት ጊዜ በተጨማሪ ዋጋ ለመሸጥ ሲሉ ነዳጅ ያከማቻሉ ሲሉም ባለሥልጣኑ ይከሳሉ።

ባለፈው ሳምንት በአፋር ክልል ነዳጅ ጭነው ተደብቀው የነበሩ 15 ቦቴዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበው ነበር።

የተሽከርካሪዎችን መዘግየት ለማስቀረትም ከአዋሽ ጀምሮ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች መመደባቸው ተገልጿል።

 አንዳንድ ሪፖርቶች ወደ አገሪቱ ከሚገባው ነዳጅ ውስጥ የተወሰኑት ቦቴዎች በጦርነት ምክንያት ዝግ ወደ ሆነችው ትግራይ ክልል እንዲገባ እንደሚደረግ ቢያመለክቱም፣ ባለሥልጣኑ ግን ይህንን የሚያረጋግጥ በቂ መረጃ እንደሌለ ይናገራሉ።

“እስካሁን የምናውቀው አንዳንድ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ይዘው ከሚጠበቁበት ቦታ ላይ አለመድረሳቸውን ነው” ሲሉ አቶ ቱሉ ስላልታወቁት ቦቴዎች ተናግረዋል።

ስለዚህም በአገሪቱ ውስጥ ለሚስተዋለው የነዳጅ እጥረት፣ በተለያዩ ጊዜያት በነዳጅ ማመላለሻ መስመሮች አካባቢ የሚከሰቱ የፀጥታ መደፍረሶች፣ ተሽከርካሪዎች አቅርቦታቸውን በሚፈለጉበት ቦታ ዘግይተው ማድረስ፣ ነዳጅ መድረስ ካለባቸው ቦታዎች ውጪ ወደ ሌሎች ቦታዎች መሸጋገር እንዲሁም አከፋፋዮች ነዳጅን ደብቆ ማስቀመጥ ምክንያት ናቸው ብለዋል።

በተለይ ነዳጅ ለመቅዳት ተሽከርካሪዎች የታሪፍ ክለሳ ከሚደረግባቸው የወራት መጨረሻ ቀናት ቀደም ብሎ መኪናቸውን ሙሉ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት ሰልፎች እንዲበራከቱ ያደርጋሉ።

ከቀጣዩ ሐምሌ ወር ጀምሮ መንግሥት በነዳጅ ላይ የሚያደርገውን ድጎማ ለማንሳት ለሚወስደው እርምጃ የመጀመሪያው ደረጃ በመሆኑ ካሉት ተደራራቢ ችግሮች በተጨማሪ የነዳጅ ሰልፉን እንዳባበሰው አሽከርካሪዎች ይናገራሉ።

የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች የነዳጅ ድጎማ መነሳቱ ላይ የተለያየ ሃሳቦችን ያንጸባርቃሉ። አንዳንዶች የተቀናጀ ቁጥጥር እና በቂ ግንዛቤ ለሕብረተሰቡ ከደረሰ የከፋ ጫና አያስከትልም ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ ባለው የኑሮ ውድነት ላይ መሠረታዊ የሆነውን የነዳጅ ድጎማን ማንሳት “ እየነደደ ባለ እሳት ላይ ነዳጅ ማርከፍከፍ ነው” ሲሉ ውሳኔውን ተቃውመውታል።