ደቡብ ኮሪያ ከሰሜን ኮሪያ ከድተው የመጡትን ግለሰብ ሚኒስትር ዴኤታ አድርጋ ሾመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማት የነበሩት ታየ ዮንግ-ሆ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝደንት አማካሪ ምክር ቤት ሊቀ-መንበር ሆነው ተሾሙ።
ከሰሜን ኮሪያ ከድተው ደቡብ ኮሪያ ከገቡ በሺዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ከፍተኛውን የሚኒስቴር ዲኤዴታ ማዕረግ ያገኙ የመጀመሪያው ግለሰብም ሆነዋል።
የ62 ዓመቱ ታየ በአውሮፓውያኑ 2016 ወደ ደቡብ ኮሪያ ከመሸሻቸው በፊት በዩናይትድ ኪንግደም የሰሜን ኮሪያ ምክትል አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።
ፒዮንግያን ግለሰቡ “አታላይ ሰው ነው” ስትል ያጣጣለችው ሲሆን የሀገር ገንዘብ በመዝረፍ እና በሌሎች ወንጀሎች እንደሚፈለጉ ገልጻለች።
ታየ፤ ደቡብ ኮሪያ በ2020 ባደረገችው የብሔራዊ ጉባዔ ምርጫ ወንበር ያገኙ የመጀመሪያው ከሰሜን ሸሽተው የመጡ ሰው መሆናቸውም ይታወሳል።
ባለፈው ሚያዚያ በተደረገው የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ ግን ለሁለተኛ ጊዜ ሳይመረጡ ቀርተዋል። ቢሆንም የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት ግለሰቡን በሚኒስትር ዲኤታ ማዕረግ አማካሪ አድርገው ሾመዋል።
“ሊበራል ዴሞክራሲ ላይ የተመሠረተ ሰላማዊ የሆነ ጥምረት ለመመሥረት ትክክለኛው ሰው ናቸው። ከሀገር ቤትም ሆነ ከውጭ ዓለም ድጋፍ እንድናገኝ ያግዙናል” ሲሉ የፕሬዝደንቱ ፅ/ቤት ሐሙስ ዕለት መግለጫ አውጥቷል።
በአውሮፓውያኑ 1962 ፒዮንግያንግ የተወለዱት ታየ በ27 ዓመታቸው ነው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን የተቀላቀሉት። በ30 ዓመታት የሥራ ሕይወታቸው ሶስት የኪም መንግሥታትን አገልግለዋል።
ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በሰጧቸው አስተያየቶች ሰሜን ኮሪያን ለቀው የወጡት ልጆቻቸው “አሰቃቂ ሕይወት” እንዲኖራቸው ስለማይፈልጉ እንደሆነ ተናግረዋል። ለኪም ጁንግ ኡን መንግሥት ያላቸውንም ጥላቻ በተደጋጋሚ የገለጡ ሲሆን የደቡብ ኮሪያ ዲሞክራሲን እንደሚያደንቁም ገልጠዋል።
ሰውየው በያዝነው ዓመት ባሳተሙት ማስታወሻ መፅሐፋቸው የሰሜን ኮሪያ ጉምቱ ባለሥልጣናት ቁጥራቸው ከመጠን በላይ በዝቷል ብለው የኪም ቤተሰቦችን እንደ ጣዖት እስከማምለክ መደረሱንም አስፍረዋል።
ከሰሜን ኮሪያ ከድተው ከወጡ በኋላ የኪምን አገዛዝ ለማዳከም “ኃይል የማይፈልጉ መንገዶችን” መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነና በሁለቱ ሀገራት መካከል የእስረኞች ልውውጥ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ መካከል ያለው ውጥረት በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት የከረረ ሲሆን ሴኡል ባለፈው አርብ ሰሜን ኮሪያ ላይ ያነጣጠረ ፕሮፖጋንዳ በመገናኛ ብዙኃን ማሰራጨት ጀምራለች። ይህ የሆነው ሰሜና ኮሪያ ቆሻሻ የተሸከሙ በሺዎች የሚቆጠሩ ‘ባሉኖች’ ወደ ደቡብ ኮሪያ መልቀቋን ተከትሎ ነው።
ከሳተለይት የተገኙ ምስሎች መሠረት አድርገው የተሠሩ ዘገባዎቸ እንደሚያስረዱት ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ በሚያዋስናት ድንበር ላይ ያላትን ወታደራዊ አቅም እያጠናከረች እና አጥር እየገነባች ትገኛለች።
ካለፈው ዓመት ታኅሣሥ ጀምሮ 34 ሺህ ሰዎች ከሰሜን ኮሪያ ወደ ደቡብ ኮብልለዋል ይላል የሴኡል የጥምረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ያወጣው መረጃ።
አብዛኛዎቹ መጀመሪያ ወደ ቻይና ከገቡ በኋላ ነው ወደ ደቡብ ኮሪያ የሚመጡት። ደቡብ ኮሪያ ሲመጡ ወዲያውኑ ዜግነት የሚያገኙ ሲሆን የሚቋቋሙበት ገንዘብም ይሰጣቸዋል።
በያዝነው ሳምንት መባቻ በቅርቡ ኩባ ተሹመው ያገለግሉ የነበሩ ትልቅ ስም ያላቸው የሰሜን ኮሪያ ዲፕሎማት መሸሻቸውን የደቡብ ኮሪያ ስለላ መሥሪያ ቤት አረጋግጧል።
ግለሰቡ የ52 ዓመቱ ጉምቱ ዲፕሎማት ሪ ኢል ኪዩ እንደሆኑ የደቡብ ኮሪያ ጋዜጦች ፅፈዋል።
ባለፈው እሑድ ደቡብ ኮሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሜን ኮሪያ የሽሽት ቀን የሚል ክብረ በዓል ስታዘጋጅ ታየ ተገኝተው ከሰሜን ሸሽተው ለሚመጡ የተሻለ የገንዘብ እርዳታ እና እነሱን ለሚቀጥሩ ኩባንያዎች ደግሞ የግብር እፎይታ ቃል ገብተዋል።












