አሜሪካዊቷ ባልፈጸመችው የግድያ ወንጀል ከ43 ዓመታት እስር በኋላ ተለቀቀች

ሳንድራ (በስተግራ) ከእስር ቤት ወጥታ ከእህቷ ስትገናኝ።

የፎቶው ባለመብት, Innocence Project

የምስሉ መግለጫ, ሳንድራ (በስተግራ) ከእስር ቤት ወጥታ ከእህቷ ስትገናኝ።

አሜሪካዊቷ ሴት ባልፈጸመችው የግድያ ወንጀል ለ43 ዓመታት ከታሰረች በኋላ ተለቀቀች።

ሳንድራ ሄመ ገና የ20 ዓመት ወጣት ሳለች ነበር በሰው ግድያ ወንጀለኛ ጥፋተኛ ተብላ የዕድሜ ልክ እስራት ተፍርዶባት የቆየችው።

ሳንድራ ግድያውን ስለመፈጸሟ በአእምሮ ጤና ሆስፒታል በማደንዘዣ ስር ሆነ ከሰጠችው ቃል ውጪ ምንም አይነት ማስረጃ አልነበረም።

ይሁን እንጂ ሳንድራ እአአ 1980 ማብቂያ ላይ በሚዙሪ ግዛት ፓትሪሺያ ጄስሻክ የተባለች ሴትን በስለት ወግታ ገድላለች በሚል የዕድሜ ልክ እስራት ተላልፎባት ነበር።

የሳንድራ ጠበቆች ደንበኛቸው ወንጀል ሳትፈጽም ለእስር ተዳርጋለች በማለት አቤቱታ አቅርበው ከ43 ዓመታት እስር በኋላ በነጻ ተሰናብታለች።

አሁን ላይ የ64 ዓመት አዛውንት የሆነችው ሴት በአሜሪካ ታሪክ በስህተት ፍርድ ተላልፎ ረዥም ዓመታትን በእስር ያሳለፈች ሴት ሆናለች።

ኢኖሰንት ፕሮጀክት የተባለው ድርጅት ባልደረባ የሆኑት የሕግ ቡድን አባላት፤ ሳንድራ ከእስር መውጣቷ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

የሕግ ባለሙያዎቹ ለፍርድ ቤት ያቀረቡት መከራከሪያ ወንጀሉን ሌላ የፖሊስ ባልደረባ ሳይፈጽም እንደማይቀር የሚጠቁም መረጃ እያለ ፖሊስ ያንን ፍንጭ ሳይመረምር ቀርቷል ይላል።

ማይክል ሆልማን የተባለው የፖሊስ አባል ሟቿ በተገደለችበት ዕለት እና ስፍራ መኪናው ቆሞ ታይቶ ነበር። የፖሊስ አባሉ ሟች በተገደለችበት ወቅት ወንጀሉ በተፈጸመበት ቦታ እንደነበረ ማሳምን ሳይችል ቀርቷል። ከዚህ በተጨማሪም ሟች ሕይወቷ ካለፈ በኋላ የሟችን የባንክ ካርድ የፖሊስ አባሉ ሲጠቀም ነበር።

ይሁን እንጂ ፖሊስ በአእምሮ ጤና መታወክ ሆስፒታል የነበረችው ሳንድራ ላይ ተደጋጋሚ ምርመራ አድርጓል። ሳንድራም ጠንካራ በሆነ ማደንዘዣ መድሃኒት ስር ሆና ወንጀሉን መፈጸሟን ማመኗን ተከትሎ የዕድሜ ልክ እስራት ተላልፎባታል።

ሳንድራ እስር ቤት ስትገባ እና አሁን ያላት ገጽታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሳንድራ እስር ቤት ስትገባ እና አሁን ያላት ገጽታ

ወንጀሉን ሳይፈጽም አይቀርም የተባለው የፖሊስ አባል በሌላ ወንጀል በእስር ላይ እያለ እአአ 2005 በሞት ተለይቷል።

ጉዳዩን የመረመሩት ዳኛ ራየን 118 ገጽ በሚረዝመው ውሳኔያቸው ሳንድራ ከ43 ዓመታት በፊት ፍርዱ ሲተላለፍባት እራሷን እንድትከላከል ዕድል አልተሰጣትም ብለዋል።

“ፍርድ ቤቱ የቀረበው ማሰረጃ በወንጀሉ ጥፋተኛ እንዳልሆነች ያሳያል” ይላል የዳኛው ውሳኔ።

ሳንድራ ሄም ባሳለፍነው አርብ ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም. አስርት ዓመታትን ካሳለፈችበት እስር ቤት ወጥታ ቤተሰቧን ተቀላቅላለች።