የኦሊምፒክ አዘጋጆች በመክፈቻው ዕለት በቀረበው ትዕይንት ክርስቲያኖችን ይቅርታ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty/AP
የፓሪስ ኦሊምፒክ አዘጋጆች በመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻ እራትን መሠረት በማድረግ የቀረበውን ትዕይነት በተመለከተ ይቅርታ ጠየቁ።
በኦሊምፒክ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የክርስቶስ የመጨረሻ እራት በቀረበበት ትዕይነት ላይ እንደ ሴት የሚለብሱ ወንዶች፣ፆታቸውን የቀየሩ ሰዎች እና በግሪክ አማልክት የተመሰለ ሰው ታይቷል።
ይህም ትዕይነቱ ክርስትናን የሚያንቋሽሽ እና ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር የሚጻረር ነው በሚል በርካቶች ሲቃወሙ ቆይተዋል።
ክርስቲያኖች እና ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች የፓሪስ ኦሊምፒክን “ሰይጣናዊ” ሲሉ ገልጸውታል። ሌሎች ደግሞ የኦሊምፒክ ተሳታፊ የሆኑ ክርስቲያን አትሌቶች የተቃውሞ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጠይቀዋል።
የፈረንሳይ የካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያንም እንዲሁ ሥነ ሥርዓቱ በክርስትና ላይ የሚሳለቅ እና ሃይማኖቱን የሚያንጓጥጥ ትዕይነት ነበረበት ብላለች።
በተለያዩ የዓለም አገራት ውስጥ የሚገኙ የክርስትና እምነት አብያተ ክርስቲያናት በትዕይንቱ ማዘናቸውን በመግለጽ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ይህንንም ተከትሎ እየተካሄደ ያለው የፓሪስ ኦሊምፒክ አዘጋጆች በትዕይንቱ የተቀየሙትን ይቅርታ ጠይቀዋል።
የአዘጋጆቹ ቃል አቀባይ አን ዴስካምፕስ፤ “የየትኛውንም እምነት ተከታዮች ለማስቆጣት ሆነ ተብሎ የተደረገ ነገር የለም። የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ የማኅብረሰብ መቻቻልን ለማሳየት ያለመ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“ይህ ዓላማችን [የማኅብረሰብ መቻቻልን ማሳየት] ተሳክቷል ብለን እናምናለን። ነገር ግን በዚህ ቅር የተሰኙ ሰዎችን ይቅርታ መጠየቅ እንፈልጋለን” ብለዋል አን ዴስካምፕስ።
የፓሪስ ኦሊምፒክ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ክሬኤቲቭ ዳይሬክቲ የሆነው ቶማስ ጆሊ በበኩሉ በትዕይነቱ ሰዎችን ቅር የማሰኘት ፍላጎት አልነበረኝም ይበል እንጂ፤ ባስተላለፈው መልዕክት እንደሚያምንበት ተናግሯል።
ቶማስ ጆሊ “ማንም ላይ የመሳለቅ ሃሳብ አልነበረኝም” ካለ በኋላ፤ “በፈረንሳይ የፈቀድነውን፤ እንደፈለግነው እንድንወድ መብት አለን። በፈረንሳይ አማኝ እና ኢ-አማኝ አለ። . . . በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እነዚህን እሴቶች ማሳየት ፈልጊያለሁ” ብሏል።
በፈረንሳይ ሃይማኖት መሳደብ መብት ነው። ብዙዎች ይህ መብት የመናገር ነጻነት መብት መሠረት ነው ይላሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በፈረንሳይ በተለይ ከእስልምና ሃይማኖት ላይ በተሰነዘሩ አስተያየቶች እና በተሠራጩ ምሥሎች የተነሳ ብዙ ያነጋገሩ ክስተቶች አጋጥመዋል።












