የቻይና መንግሥት አይፎንን ካገደ በኋላ የአፕል የገበያ ድርሻ ቀነሰ

የቻይና መንግሥት ሠራተኞቹ አይፎን እንዳይጠቀሙ ካሳሰበ በኋላ የአፕል የገበያ ድርሻ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ቅናሽ አያሳየ።

የድርጅቱ የድርሻ ገበያ ከ6 በመቶ በላይ የቀነሰ ሲሆን ማለትም በ200 ቢሊዮን ዶላር ባለፉት ሁለት ቀናት ቀንሷል።

ቻይና የአፕል ምርቶች ሦስተኛዋ ትልቁ ገበያ ስትሆን ከዓመታዊ ገቢው 18% የሚገኘውም ከቻይና ገበያ ነው።

ግዙፉ የአፕል ምርቶች አምራች የሆነው ፎክስኮን በርካታ የአፕል ምርቶችን የሚሠራው በቻይና ነው።

ዋል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው የማዕከላዊ ቻይና መንግሥት ሠራተኞች አይፎን ለሥራ እንዳይጠቀሙና መሥሪያ ቤት ይዘውም እንዳይሄዱ ታግደዋል።

ብሉምበርግ እንደዘገበው ዕገዳው በመንግሥት የሚተዳደሩ ተቋሞችን እንዲሁም መንግሥት የሚደግፋቸውን ተቋሞችም ይጨምራል።

ስለዘገባዎቹ ከቻይና መንግሥት የተሰጠ ምላሽ የለም። ይህ በቻይና መንግሥት ይፋ የተደረገው ዕገዳ የተጣለው አይፎን 15 ከመውጣቱ ከ5 ቀናት በፊት ነው።

አፕል የዓለም ትልቁ የስቶክ ገበያ ያለው ሲሆን፣ ገበያው ወደ 2.8 ትሪሊዮን ዶላር ይደርሳል።

ድርጅቱ ከቢቢሲ ስለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

በቻይና እና አሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት እንደሻከረ ነው።

አሜሪካ ከአጋሮቿ ጃፓን እና ኔዘርላንድስ ጋር በመሆን ቻይና የምትገዛው ቺፕ ላይ ገደብ ጥላለች።

ቻይናም ሰሚኮንዳክተር የሚመረትባቸው ሁለት ቁልፍ ግብዓቶችን ባለመላክ ምላሽ ሰጥታለች።

ቻይና የቺፕ ኢንዱስትሪዋን ለማሳደግ 40 በሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታደርግ ተዘግቧል።

የቻይና የንግድ ኃላፊ ጂና ሬይሞንዶ በቤዢንግ ጉብኝት ሲያደርጉ ሁዋዌ ሜት 60 ፕሮ ስልክን ለገበያ አቅርቧል።

ቴክኢንሳይትስ የተባለው የካናዳ የቴክኖሎጂ ተቋም እንዳለው፣ የቻይናን የሰሚኮንዳክተር ምርት ዕድገት በሚያሳይ ሁኔታ ነው ስልኩ የተሠራው።