ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተወገዱት አሊ ቦንጎ ከቁም እስር ተለቀቁ
በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተወገዱት የቀድሞው የጋቦን ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎ ከቁም እስር መለቀቃቸውን ከሥልጣን የገለበጣቸው ጦር አመራሮች ገለጹ።
ባለፈው ሳምንት ከሥልጣን ከተወገዱ አንስቶ በቤታቸው በቁም እስር ላይ ነበሩ።
አሁን ከቁም እስር ነጻ ስለሆኑ ወደ ውጭ ሄዶ መታከምን ጨምሮ ሌሎችም እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉ መፈቀዱ ተገልጿል።
እአአ በ2018 በስትሮክ መያዛቸው አይዘነጋም። በ2023 ምርጫ ሲወዳደሩ የሕመማቸው ጉዳይ በርካቶችን አስግቶም ነበር።
የአገሪቱ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጥያቄ ያነሱበትን ምርጫ አሊ ቦንጎ ማሸነፋቸውን ከገለጹ በኋላ ጦሩ መፈንቅለ መንግሥት አድርጎ ሥልጣን ይዟል።
አሊ ቦንጎ ከቁም እስር የተለቀቁት ከጎረቤት አገራትና ከቀጠናው የትስስር መድረክ ኢካስ ጫና ከተደረገ በኋላ ነው።
የጦሩ ቃል አቀባይ ኮለኔል ኡልሪች ማንፎምቢ በብሔራዊ ቴሌቭዥን በሰጡት ማብራሪያ፣ አሊ ቦንጎ ከቁም እስር የተለቀቁት በጤናቸው ሁኔታ ምክንያት ነው።
ውጭ አገር ሄደው መታከም እንደሚችሉም ገልጸዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኮንጎን ከ2009 ጀምሮ መርተዋል። አባታቸው ደግሞ ለ41 ዓመት ገዝተዋል።
መፈንቅለ መንግሥቱን የአፍሪካ አገራትና ምዕራባውያንም ተቃውመዋል።
ጋቦንም ከአፍሪካ ኅብረት ታግዳለች።
ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ አሊ ቦንጎ “ድምጻችሁን አሰሙ” ሲሉ የቪድዮ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጀነራል ብሪስ ኢሊጉይ ንጉዬማ ባለፈው ሰኞ የሽግግር ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሀላ ገብተዋል።
አገሪቱ ወደ ሲቪል አስተዳደር እንደምትመለስና ፍትሐዊና ነጻ ምርጫ እንደሚካሄድ ቃል ገብተዋል።
የዴሞክራሲ አቀንቃኝ የሆኑ የመብት ተሟጋቾችን ከእስር የለቀቁ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ ተጽዕኖ ያለው የንግድ ማኅበር መሪ ጄን ረሚ ያማ ይገኙበታል።