ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአሥር በላይ ሰዎችን ገድሎ ጓዳ ውስጥ ቀብሯል የተባለው ግለሰብ ታሰረ
ከአሥር በላይ ሰዎችን ገድሎ ጓዳ ውስጥ በመቅበር የተጠረጠረውን የ34 ዓመት ግለሰብ የሩዋንዳ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አዋለ።
ግለሰቡ በመዲናዋ ኪጋሊ ተከራይቶ ከሚኖርበት ቤት ከተባረረ በኋላ ነው ፖሊስ ወንጀሉን የደረሰበት።
ግለሰቡ ለወራት የቤት ኪራይ ሳይከፍል ቆይቶ ፖሊስ ወደስፍራው ከተጠራ በኋላ ነው የታሰረው።
በግለሰቡ ተገድለዋል የተባሉት ሰዎች በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶችና ወንዶች ሊሆኑ እንደሚችሉ የፖሊስ ኃላፊ ለሩዋንዳ መገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።
‘ዘ ኒው ታይምስ’ ለተባለ ጋዜጣ ማብራሪያ የሰጡ ፖሊስ እንዳሉት ግለሰቡ ከቤቱ በፖሊስ እንዲወጣ ሲደረግ ላለመውጣት ታግሏል።
“ደጋግሞ ይቅርታ እየጠየቀ ሲያለቅስ ጥርጣሬ ገባን። ከዚያ ፖሊስ ጣቢያ ከወሰድነው በኋላ የተወሰኑ ሰዎች መግደሉን አመነ። ምርመራም ከፈትን” ብለዋል።
የሩዋንዳ ፖሊስ ምርመራ ቃል አቀባይ ቴሪ ሙራንጊራ እንዳሉት፣ የተገደሉት ሰዎችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ ምርመራ ያስፈልጋል።
“አብዛኞቹ የገደላቸው ሰዎች በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ናቸው። ቤቱ አታሎ ከወሰዳቸው በኋላ ስልካቸውንና ሌላም ንብረታቸውን ይሰርቃቸዋል። ከዚያም አንቆ ይገድላቸውና በተከራየው ቤት ጓዳ ውስጥ በቆፈረው ጉድጓድ ይቀብራቸዋል” ሲሉ አብራርተዋል።
ከዚህ በፊት ግለሰቡ በዝርፊያ፣ በመድፈርና ሴቶችን በማስፈራራት ቢታሰርም በቂ ማስረጃ ስላልተገኘ ተለቋል።
በቁጥጥር ሥር የመዋሉ ዜና ሲሰማ ሩዋንዳውያን መደናገጣቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገልጸዋል።