የልባችንን ጤንነት እንዴት በቀላሉ መጠበቅ እንችላለን?

አጠቃላይ ሰውነታችን በአግባቡ እንዲሠራ ጤናማ ልብ ወሳኝ ነው።

በመላው ሰውነታችን የሚያስፈልገንን ኦክስጅን እና አስፈላጊ ንጥረ ምግቦችን የሚያቀርበውን ደም የሚያቀርብ ነው።

ከልብ እና ከደም ዝውውር ሥርዓት ጋር የተያያዙ በሽታ (ካርዲዮቫስኩላር) በመላው ዓለም በጣም የተስፋፋ የሞት መንስኤ ነው።

እንደ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ይህ የጤና ችግር 18 ሚሊዮን ሰዎችን በየዓመቱ ይገድላል።

ከደም ዝውውር ሥርዓት ጋር በተያያዘ ከአምስቱ አራቱ ሞቶች በልብ እና በስትሮክ ምክንያት ይከሰታሉ።

የልብን ጤንነት መጠበቅ ለአዋቂ ሰዎች የልብ ምትን በደቂቃ ከ60 እስከ 100 ለማድረስ በየቀኑ መሥራት እንደሚቻል የልብ ሐኪሞች ይናገራሉ።

በአሜሪካ የልብ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ኤቨን ለቪን "በሕይወት ዘመን በልብ ላይ የሚደርሰውን የትኛውንም ጉዳት በጤናማ አመጋገብ፣ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ሲጋራ በማቆም መመለስ ይቻላል" ይላሉ።

ነገር ግን እንደሚባለው በቀላሉ በጤናማ ልብ የልብ ድካም ስጋትን መቀስ ይችላል?

የልብ ድካም ምንድን ነው?

የልብ ድካም የሚፈጠረው ወደ የልብ የደም አቅርቦት በድንገት ሲገታ ነው።

በደም ዝውውር ወደ ልብ የሚሄደው ኦክስጅን ሲቋረጥ የልብ ጡንቻ ሊጎዳ ወይም ሊሞት ይችላል።

ፈጣን ሕክምና ማግኘት ካልተቻለ የልብ ጡንቻ ሊመለስ የማይችል ጉዳት ሊደርስበት ይችላል። በዚህ መንገድ ትልቅ የልብ ክፍል ከተጎዳ ልብ መምታቱን ያቆማል፤ ውጤቱም ሞት ነው።

ግማሽ የሚሆነው የልብ ድካም የሚከሰተው ምልክት መሰማት በጀመረ በሦስት ወይም በአራት ሰዓት ውስጥ ነው።

ስለዚህም የልብ ድካም ምልክቶች እንደ ድንገተኛ የጤና ችግር ማየት ወሳኝ ነው።

በጣም የተለመደው የልብ ድካም ዓይነት ኮሮናሪ የተባለው የልብ በሽታ ነው። ይህም በደም ቧንቧ የሚገኝ የስብ ንጥረ ነገር የደም ዝውውር በቀላሉ እንዳይንቀሳቀስ ያደርጋል።

በአሜሪካ በየዓመቱ 805 ሺህ ሰዎች የልብ ድካም ያጋጥማቸዋል።

ይህ እክል 605 ሺህ የሚሆኑት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገጥማቸው፤ 200 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ከዚህ ቀደም የልብ ድካም ሕመም ያጋጠማቸው ናቸው።

የአሜሪካ የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል እንደሚለው በየ40 ሰከንዱ አንድ ሰው የልብ ድካም ይገጥመዋል።

የልብ ድካም እንደገጠመን በምን እናውቃለን?

የልብ ድካም በተለያዩ ምልክቶች ሊከሰት ይችላል። ከሁሉም በላይ የተለመደው ግን የደረት ሕመም ነው።

ነገር ግን በደረት ጠንካራ ግፊት እና የመጨናነቅ ስሜት እንጂ ከፍ ያለ ሕመም አይደለም።

አንዳንድ ሴቶች የደረት ሕመም በተጨማሪ አንገታቸው እና ሁለቱም እጆቻቸው ላይ ሕመም ሊሰማቸው ይችላሉ።

በካሊፎኒያ የልብ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ኤሊን ባርሰግን እንደሚሉት የልብ ድካም መጀመሪያ ላይ የምግብ አለመፈጨት ነው ተብሎ ሊታሰብ ይችላል።

ነገር ግን የልብ ድካም እንደ የምግብ አለመፈጨት ሳይሆን በተለያየ የሰውነታች ክፍሎች ላይ ሕመም ያስከትላል።

ለምሳሌ ያህል ግራ እጅ፣ መንጋጋ፣ ጀርባ እና ሆድ በመሰሉ ክፍሎች ላይ ሕመም ይሰማል።

የልብ ድካም ሌሎች ምልክቶች ራስ ማዞር፣ በጣም ማላብ፣ ትንፋሽ ማጠርን ያካትታል።

አንዳንድ የልብ ሕመሞች በድንገት የሚከሰቱ ቢሆንም የሚያስጠነቅቁ ምልክቶች ለሰዓታት ወይም ለቀናት አስቀድመው ሊታዩ ይችላሉ።

እረፍት ከተደረገ በኋላም የሚሰማ የደረት ሕመም ማስጠንቀቂያ ሊሆን ይችላል።

"ከሦስት ሰዓታት በኋላ፤ ጉዳት የደረሰባቸው የልብ ጡንቻዎች የደም ዝውውር የማይመለስ ከሆነ ሊሞቱ ይችላሉ። የሕክምና ባለሙያዎች እስኪደርሱ ድረስ አስፕሪን እንዲያኝኩ እመክራለሁ" ይላሉ ዶ/ር ኤሊን።

የልብ ሐኪሞች የልብ ድካም ከተከሰተ በኋላ ሕክምና በፍጥነት ማግኘት አስፈላጊ እንደሆነ ያሰምራሉ።

"ዕድሜ፣ ክብደት፣ አልኮል እና ትንባሆ የመውሰድ ልማድን ጨምሮ የቤተሰብ ታሪክን ማወቅ እና የተጋላጭነት ስጋትን ማወቅ ያስፈልጋል። እነዚህ ጫና የሚያደርሱ ሁሉም ነገሮች ካለባቸው እና የደረት ግፊት ከተከሰተ አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ማግኘት የግድ ነው" ይላሉ ዶ/ር ኤቨን።

የልብ ድካምን እንዴት መከላከል ይቻላል?

የልብ ድካም ስጋትን መከላከል የሚያስችሉ በርካታ መንገዶች አሉ።

ለምሳሌ የደም ግፊትን ዝቅ ማድረግ እና የኮሌስትሮል መጠንን በምግብ እና በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማስተካከል ይቻላል።

ኮሌስትሮል በደም ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ነገር ሲሆን፤ ጤናማ ሕዋስን ለመገንባት ወሳኝ ነው።

ይሁን እንጂ ከፍተኛ የኮሌስትሮል ዓይነቶች የልብ በሽታ አደጋን ከፍ ያደርጋሉ።

የልብ ሐኪሞች የሚመክሩት በዕለት ተዕለት ኑሯችን ልባችንን ለመጠበቅ ልናደርግ የምንችለው ወሳኙ ነገር ጤናማ የሕይወት ዘይቤ መከተልን ነው።

ብዙ ጨው መጠቀም የደም ግፊትን ስለሚጨምር ጨውን በመቀነስ በቀን ከ6 ግራም በላይ ጨው ካለመጠቀም በተጨማሪ ዝቅተኛ ስብ እና ከፍተኛ ፋይበር ያላቸውን ምግቦችን መመገብ ይመከራል።

በፋብሪካ የተቀነባበሩ እና በስብ የተሞሉ ምግቦች የደም ውስጥ የኮሌስትሮል መጠንን ከፍ ስለሚያደርጉ እነዚህን ምግቦች መመገብ አይመከርም።

እነዚህም ምግቦች ሥጋ፣ ከረሜላ፣ ኬኮች፣ ብስኩቶች፣ ሶሴጅ (ቋሊማ)፣ ቅቤ እና የፓልም ዘይት የያዙ ምግቦች ናቸው።

የተመጣጠነ አመጋገብ የልብ ቧንቧን ለመዝጋት የሚዳርገውን እና የኮሌስትሮል መጠንን ከፍ የሚያደርግ ቅባት ማካተት የለበትም።

ለጤናማ አመጋገብ የሚመከሩ ምግቦች ዘይታማ ዓሳ፣ አቮካዶ፣ ለውዝ እና የአትክልት ዘይቶች ናቸው።

ጤናማ አመጋገብን እና መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የልብ ጤናን ለመጠበቅ በጣም ጤናማ መንገድ ነው።

ጤናማ የሆነ ክብደት መቀነስ በከፍተኛ የደም ግፊት የመያዝ ስጋትን ይቀንሳል።

የልብ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር ኤቨን ሌቪን በሳምንት አምስት ቀን በየቀኑ ቢያንስ ለ30 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግን ይመክራሉ።

ለጤናማ የሕይወት ዘይዜ ቁልፉ ግን "በፍፁም" አለማጨስ እንደሆነ ያመለክታሉ።

የአሜሪካ የልብ ማኅበር በ23,927 ሰዎች ላይ በተደረገ የጥናት ውጤት ሲጋራ እና የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ (ኢ-ሲጋሬት) የሚያጨሱ ሰዎች ተመሳሳይ የልብ ሕመም ይገጥማቸዋል።

ሆኖም የኤሌክትሮኒክ ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ከልብ ጋር የተያያዙ ክስተቶችን ሪፖርት የማድረግ ዕድላቸው ከ30 እስከ 60 በመቶ ብቻ ነው።

አንድ ጊዜ የልብ ሕመም ካጋጠማቸው ሰዎች እንደ አሜሪካ የልብ ማኅበር መረጃ አምስት በመቶ የሚሆኑት በአምስት ዓመታት ውስጥ በድጋሚ ሆስፒታል ይገባሉ።

በለንደን የሚገኘው የኢምፔሪያል ኮሌጅ እና በስዊድን የሚገኘው የሉንድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ስታቲንስ እና ኢዝቲሚብ የተባሉ መድኃኒቶችን ለልብ ድካም ታካሚዎች ማዘዝ ሁለተኛ የልብ ድካም ክስተት ስጋትን ይቀንሳል ይላሉ።

ሁለቱ መድኃኒቶች የኮሊስትሮልን መጠን ዝቅ የሚያደርጉ ናቸው።

ዶ/ር ኤሊን "ዝቅተኛ የኮሌስትሮል መጠን ዝቅተኛ የልብ ደም ዝውውር ሕመም የመጋለጥ ስጋትን እንደሚቀንስ የሚያሳዩ የአስርት ዓመታት መረጃ አለን" ይላሉ።

በወጣቶች ላይ እየጨመረ ያለው የልብ ሕመም

አጠቃላይ የልብ ድካም ስጋት ከዕድሜ መጨመር ጋር ከፍ ቢልም፤ የአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ስታትስቲክስ ማዕከል መረጃ የልብ ድካም በወጣትቶች ላይ እንደጨመረ ያሳያል።

በአውሮፓውያኑ 2019 ከ18 እስከ 44 ዓመት የሆናቸው 0.3 በመቶ ሰዎች ብቻ የልብ ድካም ሕመም አጋጥሟቸዋል።

በ2023 ይህ ቁጥር ወደ 0.5 በመቶ ከፍ ብሏል።

ዶ/ር ኤቨን ሌቪን ይህን ዕድገት ከሕይወት ዘይቤ ልምድ መለወጥ ጋር ያያይዙታል።

ይህም በዚህ ዕድሜ ቡድን ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ከፍተኛ የተቀነባባሩ ምግቦችን መመገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግን ያካትታል።

"ሁላችንም መንቀሳቀስ ይኖርብናል። ወደ ጂምናዚየም መሄድ ባይሆንም የተወሰነ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል። ከኮቪድ ወረርሽኘ በኋላ ከቤታቸው የሚሠሩ ሰዎች አደገኛ እና እንቅስቃሴ የሌለው የአኗኗር ዘይቤ መፍጠራቸው ያሳስበኛል" ይላሉ።

ሲጋራ ማጨስ በደም ቧንቧ ውስጥ ስብ እንዲከማች በማድረግ የታወቀ ምክንያት ቢሆንም፤ እንደ ዶ/ር ኤቨን ያሉ የልብ ሐኪሞች በወጣቶች የሚመረጠው ቬፕ (ኤሌክትሮኒክ ሲጋራ) ያልታወቀ ተፅዕኖ ያሳስባቸዋል።

ከዚህ ባሻገር ዶ/ር ኤሊን "የቤተሰብ [የዘር] የሕክምና ታሪክ የልብ ድካም ስጋትን ከፍ ያደርጋል። እንደ ጭንቀት እና ደካማ እንቅልፍ ያሉ አካባቢያው ስጋቶች አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የታወቁ ምክንያቶች ናቸው" ይላሉ።