መጥፎ ከሚሉት ሥራ በሳምንት ሊለቁ ይገባል?

መጥፎ አለቃ ቢያጋጥምዎ፣ የሥራ ሁኔታው ምቹ ያልሆነ እንዲሁም ጥሩ የማይከፍል ቢሆን ወዲያውኑ ከሥራ ይለቃሉ?

አንዳንዶች መጥፎ የሚሉትን ሥራ ከሳምንት ወይም ከቀናት በኋላ መልቀቅ እንደ ጥሩ ውሳኔ ይመለከቱታል።

እርስዎስ ምን ያህል ይጠብቁ ይሆን? ዓመታት ቀናት? ...ሥራ ሳያገኙስ ይለቃሉ?

ኒኮል በአሜሪካዋ ማያሚ መቀመጫውን ያደረገ የሕዝብ ግንኙነት ድርጅት ውስጥ ባለፈው ዓመት ነበር የተቀጠረችው።

ነገር ግን በተቀጠረች በሰዓታት ውስጥ ነበር ኩባንያው እንደማይሆናት ያወቀችው።

በመጀመሪያው ቀን የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ አዲስ ሠራተኛ መሆኗን አላስተዋወቀም።

ሙሉ ስብሰባው የእሱ ነበረ በሚባል ሁኔታ አንድም ሠራተኛ እንዲናገር ዕድል አልሰጠም። ኒኮልም ይህ የመጀመሪያ ቀን ነው ነገሮች ይቀየራሉ ብላ አስባ ነበር።

በሁለተኛው ቀን ይኸው አለቃ በስብሰባ መሃል በአንደኛው ሠራተኛ ላይ ሲጮህ እና ሲሳደብ ማየቷ የበለጠ አስደነገጣት።

በሦስተኛው ቀን ኒኮል የአለቃዋ ባህርይን በተመለከተ ሌላ ሠራተኛን ጠየቀች። አለቃዋ ሠራተኞቹን ማመናጨቅ እና መሳደብ የተለመደ ይሆን ወይ? ለሚለው ጥያቄዋም “አዎ የተለመደ ባህሪው ነው”፤ “ሁሉም ሰው ይፈራዋል” የሚል ምላሽም አገኘች።

በ20ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ኒኮል በአራተኛ ቀኗ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤዋን ጻፈች። ጊዜም አላባከነች በሳምንቱ መገባደጃ ላይም ሥራዋን ለቀቀች።

በርካታ ሠራተኞች በግል እና በሙያዊ ሕይወታቸው ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ጉዳዮች ደጋግመው በሚገመግሙበት ወቅት አንዳንድ ሠራተኞች ደስተኛ ያልሆኑባቸውን ሥራዎች ለመልቀቅ አያመነቱም። ከቀናት ወይም ከሳምንታትም በኋላ ለቀው ይወጣሉ።

ሠራተኞች ደክመው ያገኙትን ሥራ በአጭር ጊዜ ለቀው የሚወጡባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ ። የሥራ ድርሻው ከሥራው በበለጠ ሲጋነነን፣ የሥራ ኃላፊዎች ያልተገባ ጥብቅ ቁጥጥር፣ ምቹ ያልሆነ የሥራ ባህል እንዲሁም የድርጅቱ እሴቶች አጠራጣሪ ሲሆኑ የሚሉት የሚጠቀሱ ናቸው።

በአንዳንድ ሁኔታዎች ሠራተኞች በችኩልነት እና በግዴለሽነት ውሳኔያቸውን ሳያጤኑ የሚለቁበት አጋጣሚ እንዳለም ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ውሳኔያቸውን አጢነው እና ጊዜያቸውንም ሳያባክኑ ለተሻለ አማራጭ ሥራውን ይለቃሉ።

ሆኖም በዓለማችን ያሉ ሠራተኞች በሥራ ገበታቸው ላይ ለዓመታት ይቆያሉ።

እንደ የአሜሪካ የሠራተኞች ስታቲስቲክስ ቢሮ ከሆነ፣ በአሜሪካ ሠራተኞች በሥራ ላይ የሚቆዩበት አማካይ የሥራ ጊዜ አራት ዓመታት ነው።

ነገር ግን ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሥራቸውን የሚለቁ ሠራተኞች ቁጥር እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ 10 በመቶ ገደማ ጭማሪ ማሳየቱንም ባለፈው ዓመት በሊንክደን የተሠራ ጥናት አመልክቷል።

በሌላ አገላለጽ ሠራተኞች ደስተኛ ባይሆኑም በሥራ ገበታቸው ለዓመታት ከመቆየት ይልቅ ጊዜ ሳያባክኑ የሚለቁ ሰዎች እየጨመሩ መጥተዋል።

ለዚህ ክስተት አንደኛው ምክንያት በአሰሪዎች እና በሠራተኞች መካከል ያለው “ማኅበራዊ ውል” መበጣጠሱ መሆኑን የሚናገሩት በቦስተን ዩኒቨርስቲ ክዩስትሮም የንግድ ትምህርት ቤት የማኔጅመንት መምህር የሆኑት ሞሼ ኮኸን ናቸው።

“ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን አይንከባከቡም። ሠራተኞች ጊዜያዊ እና አላስፈላጊ እንደሆኑ እየተሰማቸው መጥቷል። ስለዚህ ለቀጣሪዎቻቸው የሚያሳዩት ታማኝነት የለም። ለዚህም ነው ሠራተኞች በተለያዩ ድርጅቶችም የተለያዩ ሥራዎችን እየሞከሩ የሚገኙት” ይላሉ ኮኸን።

የሥራ ገበያውም እንደተቀየረ የሚናገሩት ኮኸን ከሥራ መባረሮች፣ የሠራተኞች ቅነሳ እንዲሁም ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው የገቡትን ቃል አለማክበር እየተበራከተ መምጣቱን ይጠቅሳሉ።

እንዲሁም ከቢሮዎች ሳይሆን በርቀት ከሚሰሩ ሠራተኞች ምርታማነት ጋር በተያያዘ የሥራ ኃላፊዎች የሚያደርጓቸው ጥብቅ ክትትሎች የነበረውን መተማመን የሸረሸረ መሆኑንም ያስረዳሉ።

አንዳንድ ሠራተኞች በእነዚህ ኩባንያዎች እና ድርጅቶች ላይ ያሉ ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎችን ከመቃወም ይልቅ ሥራቸውን ለቀው መሄድን አማራጭ አድርገውታል።

በ30ዎቹ ዕድሜ የሚገኘው ጋዜጠኛው ጄምስ በዘንድሮው ዓመት ጥር ወር አካባቢ ነበር በኒውዮርክ በሚገኝ አንድ ጀማሪ ሚዲያ ሥራ የጀመረው።

ምንም እንኳን የበርካታ ዓመት ልምድ ያለው ጄምስ የሥራ ድርሻውን መወጣት ቀላል ቢሆንም ሥራውን በጀመረ በሳምንት ነበር ለእሱ የማይሆን ሥራ እንደሆነ የተረዳው።

“በሚዲያው የተቀጠርኩት በዜና ክፍል በነበረኝ አመራር ነበር። ነገር ግን ሥራ በጀመርኩበት ወቅት የዕለት ተዕለት አርትዖቶቼን እግር በእግር መከታተል እና ትናንሽ ስህተቶችንም በማጉላት መጠቆም ጀመሩ” የሚለው ጄምስ፣ አክሎም “ቀኑን ሙሉም እነዚህ ስህተቶች እንዳይፈጠሩ ሙሉ ጉልበቴን በእሱ ላይ ማጥፋት ጀመርኩ። ይህም በአጠቃላይ በሚዲያው ዕድገት ስትራቴጂ ላይ እንዳላተኩር ስላደረገኝም አሠሪዎቼ ቅር መሰኘት ጀመሩ” ብሏል።

ከአንድ ወር በኋላም ጄምስ በሥራው መሰላቸት ብቻ ሳይሆን ምሬት ገባው። ከዚያም ከሥራ ለመልቀቅ ባቀደበት አጋጣሚም ከሥራ እንደተቀነሰ ተነገረው። “እፎይታ ነው የፈጠረልኝ። እውነት ነው ለሥራው ትክክለኛ ሰው አልነበርኩም” ይላል።

በሥራዎ ደስተኛ ካልሆኑ ቶሎ መልቀቅ ለሠራተኞች ትክክለኛ ውሳኔ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በመጀመሪያ ደረጃ ትክክለኛ ባልሆነ የሥራ ገበታ ውስጥ መቆየት ሌሎች ዕድሎችን የሚያጡበትን አጋጣሚ ይፈጥራል። ሠራተኞች እርካታ በማይሰማቸው ሥራ ውስጥ በቆዩ ቁጥር በሌሎች ማደግ በሚችሉባቸው ሥራዎች እና ድርጅቶች የሚኖራቸው አጋጣሚ እና ዕድል የሚያጡበት እንደሆነ በካሊፎርኒያ ፔፐርዲን ግራዚያዶ የቢዝነስ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ቦቢ ቶማሰን ያስረዳሉ።

በተለይም በርካታ ቀጣሪ ኩባንያዎች እና ድርጅቶች ያሏቸው ክፍት የሥራ ድርሻዎች ከአመልካቾች ቁጥር በሚበልጥበት ወቅት በበለጠ እውነታውን ያጎላዋል።

ሆኖም በአንዳንድ የሥራ ዘርፎች በምጣኔ ሃብት አለመረጋጋት ምክንያት የሥራ ዕድሎች ዕጥረት ቢያጋጥምም በርካታ ሌሎች ኩባንያዎች የሠራተኞች ዕጥረት በሚያጋጥማቸው ሁኔታ አሁንም ቢሆን ሠራተኞች የበላይነት ድርሻ አላቸው።

በተለይም ሥራው ምቹ ካልሆነ እና የሥራ ባህሉም መርዛማ ከሆነ ሥራውን መልቀቅ ለራስ ክብርን መስጠት እንደሆነ ፕሮፌሰር ቦቢ ቶማሰን ይገልጻሉ። ሥራው ካልተስማማዎት በመልቀቅ ለራስዎም ያተርፋሉ ይላሉ ፕሮፌሰሯ።

በአንዳንድ ኩባንያዎችም ሆነ ሥራዎች ያሉ ጉድለቶች እና ስህተቶች ግልጽ ሆነው የሚታዩበት አጋጣሚ እንዳሉ ሁሉ የተሰወሩ ሊሆኑም እንደሚችሉ ያስረዳሉ።

ለምሳሌ ያህል የማይሳካ ፕሮጀክት ወይም የተከፋፈለ የሥራ ቡድን ግልጽ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን ሠራተኞች ያላቸው የሥራ ችሎታም ሆነ እሴት ከኩባንያው የሥራ አካሄድ ጋር የማይጣጣምበት አጋጣሚ ይፈጠራል።

የተቋሙ ባህል በመሠረታዊነት ችግሩ የስር የሰደደ ከሆነ እና ባህሉን እና ልምዱን ሠራተኞች ለመቀየር አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ ከሌላቸው በተቻለ ፍጥነት መልቀቅ የተሻለ አማራጭ መሆኑን መረዳት ይቻላል ይላሉ ፕሮፌሰሯ።

“ችግሩ ከሠራተኞቹ ገዝፎ መቀየር የማይችሉት ከሆነ ሠራተኞች ሲለቁ ማየት የተለመደ ነው” ይላሉ።

እንዲህ አይነት ውሳኔ ብዙ ጊዜ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ኒኮል ወስና በአራተኛ ቀኗ ሥራ ከለቀቀች በኋላ በአንድ ወር ውስጥ አዲስ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አገኘች።

“ሥራ ማግኘት እችል ይሆን የሚለው አስፈርቶኝ ነበር። ነገር ግን በቀድሞው ድርጅቴ ሌላ ቀን መቆየት እንደማልችልም አወቅኩኝ” ትላለች።

“አዲሱ ሥራዬ በጣም የተሻለ ነው። የተቀጠርኩበት ድርጅትም ለሙያ እድገቴ ያስባል። ዋና ሥራ አስፈጻሚው መልካም ሰው እና ጮክ ብሎም ሠራተኛ የማይናገር ሰው ነው” በማለትም ታስረዳለች።

ለቀናት ያህል በሠራችበት ድርጅት ውስጥ የነበራትን አስከፊ አጋጣሚ እምብዛም አታስበውም። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ስታስበው በፍጥነት እንደዚህ አይነት ውሳኔ ላይ መድረስ በመቻሏ ራሷን ታመሰግናለች።

“ልምዱ በራሴ መቆም ምን ማለት እንደሆነ እና ለራሴም እንድቆም አስተምሮኛል። ለሠራተኞች ክብር የሌለው ድርጅት ባህል ምን እንደሚመስል ለመረዳት ችያለሁ። የዚህ ድርጅት አካል ላለመሆንም የወሰንኩት ለራሴ በቂ አክብሮት ስላለኝ ነው” ትላለች።

ሆኖም ኮኸን እንደሚሉት አንዳንድ ሠራተኞች በፍጥነት መውጣት እና መግባታቸው ድርጅቶችን እንዲጎዱ መንገድ እንደከፈተም ይናገራሉ።

“አንዳንድ ሠራተኞች ፍላጎታቸውን ለሟሟላት የአጭር ጊዜ ሥራዎችን ይመርጣሉ” ይላሉ።

በርካታ ሠራተኞች ከፍ ካለ ደመወዝ በተጨማሪ፣ የመማር ዕድሎችን እንዲሁም ተለዋዋጭ የሥራ ሰዓት እና ምቹ የሆነ የሥራ ባህልን ይፈልጋሉ። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ፍላጎቶች በመጀመሪያው ቀን ሊሟሉ አይችሉም።

“ሠራተኞች ወዲያውኑ ተቀጥረው ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ወይም ጉድለት ያዩበትን አለቃ መጥፎ ነው ብለው የማሰብ ነገር አለ። ነገር ግን ይህ እውነታው አይደለም” ይላሉ ኮኸን።

“ለተማሪዎቼ የምሰጠው ምክር በመጀመሪያ ከሥራ ለመለልቀቅ አትፍሩ። ነገር ግን በፍጥነት አትወስኑ። በችኮላ ምንም ነገር አታድርጉ። ተረጋግታችሁ ነገሮችን አጢኑ” በማለትም ያስረዳሉ።

ፕሮፌሰር ቦቢ ቶማሰንም በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ። ሠራተኞች የሥራ ቦታቸውን ሁኔታ ለመቀየር ከከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር ለመሥራት መሞከር እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል የሚቻልባቸውን መንገዶች እንዲያስቡ ይመክራሉ።

በተጨማሪም ከቀድሞ የሥራ ባልደረቦች፣ አማካሪዎች እና የሥራ አሠልጣኞች የሚሰጧቸውን ምክሮች መስማት ሠራተኞች አመለካከታቸውን እንዲያሻሽሉ ሊረዳቸው እንደሚችልም ያስረዳሉ።

“ሥራ ከመልቀቅዎ በፊት ቆም ብለው ቢያጤኑት መልካም ነው” ይላሉ።

ሆኖም ፕሮፌሰሯ ሠራተኞች የሚሰማቸውን ስሜትም መስማት ተገቢው ስፍራ ሊሰጠው እንደሚገባ ያምናሉ። በተለይም ደግሞ ሥራቸውን መልቀቅ የሚያስከትለውን አሉታዊ እና አዎንታዊ ሁኔታቸውን ላጤኑ ደግሞ በበለጠ ውሳኔው ትክክል ነው ይላሉ።

“በመጥፎ የሥራ ሁኔታ ሁሉንም ዋጥ አድርጎ መቀጠል የመማሪያ ብቸኛው መንገድ አይደለም።”