ሥራ የማዘግየት ልማድን ለመቅረፍ የሚረዱ 8 ነጥቦች

ሥራ የማዘግየት ችግር አለብዎት? 'ቆይ ቡና ጠጥቼ እሠራዋለሁ? እስኪ ፌስቡክ አየት አየት አድርጌ እጨርሰዋለሁ? አይ ቆይ ነገ ልሥራው?' የሚሉት እርስዎ ብቻ አይደሉም። በርካቶች ሥራን 'ኋላ አከናውነዋለሁ' ብሎ የማዘግየት ልማድ አላቸው።

አንድን ሥራ ለማጠናቀቅ ቀነ ገደብ ከተቀመጠልዎ፤ ሥራ የማዘግየት ልማድዎ ከአለቃዎ ጋር ሊያጋጭዎ ይችላል። ሥራ የማዘግየት ልማድ ጤናን እንደሚጎዳም የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሥራ ማዘግየት [procrastination] ጭንቀት ሊያስከትል ይችላል።

ከዚህ ልማድ ለመላቀቅ የሚረዱ ስምንት መንገዶችን እንንገርዎ፦

1. የሥራ ሂደትን መውደድ

ኢን ታይለር የስፖርት ሥነ ልቦና ተመራማሪ ናቸው። አንድ ሰው የሚጠበቅበትን ሥራ ከማከናወኑ በፊት የሥራ ሂደቱ አስደሳች እንደሆነ ማመን እንዳለበት ይገልጻሉ።

ከሂደቱ ውስጥ እምብዛም ደስ የማይሉ ነገሮች ቢኖሩም፤ ሥራውን ለመጨረስ አስፈላጊ እንደሆኑ አምኖ መቀበል ያስፈልጋል።

ተመራማሪው እንደ ምሳሌ የሰጡት ሩጫን ነው። ከ30 ደቂቃ ሩጫ በኋላ ድካም ሊሰማን፣ መገጣጠሚያችንን ሊያመንም ይችላል። ይህ ህመም የአካል ብቃት እንቅስቃሴው አንድ አስፈላጊ አካል እንደሆነ ማመን ያሻል ሲሉም ተመራማሪው ይመክራሉ።

2. በፍርሀት ተይዞ ጊዜ ማባከን አያዋጣም

አንዳንዶች ሥራ የሚያዘገዩት 'ውጤታማ ላንሆን እንችላልን' በሚል ፍርሀት ሳቢያ ሊሆን ይችላል። ለ15 ዓመታት ሥራ በማዘግየት ልማድ ላይ ጥናት የሠሩት ፉሺራ ሲሮሲስ እንደሚሉት፤ የወጠነው ላይሳካልን ይችላል ብለው የሚፈሩ ሰዎች ሥራ የማዘግየት ልማድ አለባቸው።

ሥራን ማዘግየት ለፍርሀት መፍትሔ እንደማይሆን ፋሺራ ይናገራሉ።

"በፍርሀት ተውጠን ጊዜ ስናጠፋ የበለጠ ጭንቀት ውስጥ እንገባለን። በፍርሀት የሚያልፈው ጊዜ ሥራ ላይ ቢውል ይመረጣል"

3. እቅድ

አንድ ሥራን አስቀድሞ ማቀድ ሥራ ከማዘግየት ልማድ ለመላቀቅ ይረዳል።

ለምሳሌ ቅዳሜና እሁድ ከጓደኞችዎ ጋር ሻይ ቡና የማለት እቅድ ከያዙ፤ ቀጠሮው እስኪደርስ ለማጥናት ማቀድ ይችላሉ።

4. ቀለል አድርጎ ማየት

አንድ ሥራን ከመጀመር በፊት ሥራውን ቀለል አድርጎ መውሰድ አዋጭ ነው።

ለመሮጥ አስበው ከሆነ የስፖርት ልብስዎን ማግኘት የሚችሉበት ቦታ ቢያስቀምጡ ሂደቱን አቀለሉት ማለት ነው። አንድ ሥራ ከመጀመርዎ በፊት ማንኛውንም አይነት መሰናክል ማስወገድም አይርሱ። ለምሳሌ ጽሁፍ ከመጀመርዎ በፊት ከማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች መውጣት ይችላሉ።

5. እራስዎን ይሸልሙ

ኬትሊን ዉሊ የተባሉት ተመራማሪ እንደሚሉት፤ ሽልማት ሰዎችን ያበረታል። ስለዚህም አንድን ሥራ ካጠናቀቁ በኋላ እራስዎን በመሸለም ማበረታታት ይችላሉ።

6. 'ለወደፊት' አይበሉ

ብዙዎች ዛሬ ላይ ካለ ነገር ይልቅ ለወደፊት በሚመጣ ነገር ላይ ተስፋ መጣል ይመርጣሉ። 'ለወደፊት ጊዜዬን በአግባቡ የምጠቀም ሰው እሆናለሁ' የሚሉ በርካቶች ናቸው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ግን ይህ አካሄድ አያዋጣም።

7. ከራስ በላይ. . .

ሥራ የማዘግየት ልማድ ያላቸው ሰዎች እምብዛም ለራሳቸው የማያዝኑ ሰዎች እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ። አንድ ሥራ ሲያዘገዩ ራሳቸውን ይቅር ማለት የማይችሉ ሰዎች ከስህተታቸው አይማሩም።

ተመራማሪዋ ፉሺራ ሲሮሲስ እንደሚናገሩት፤ ራሳችንን ይቅር ባልን ቁጥር የተሻልን ሰዎች እየሆንን እንሄዳለን። ራስን መውደድ እና ቸር መሆን ሥራ የማዘግየት ልማድን ለመቅረፍ ከሚያግዙ መንገዶች አንዱ ነው።

8. ራስዎን በቀና መንገድ ይግለጹ

ራስን ከመውደድ ባሻገር ስለራስ ቀና ነገር መናገርም አስፈላጊ እንደሆነ ተመራማሮዎች ይናገራሉ።

ኢን ታይለር እንደሚሉት፤ አንድ ሰው ስለ ራሱ ሲያወራ የሚጠቀማቸው ቃላት ባህሪው ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።

"አዘውትረው የሚሮጡ ከሆነ 'አንዳንዴ እሮጣለሁ' ከማለት ይልቅ 'መሮጥ አዘወትራለሁ' ብለው መናገር አለብዎት"