ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የክልሉ መንግሥታዊ መዋቅር መልሶ እየተደራጀ መሆኑን ገለጹ
በቅርቡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው የተሾሙት አቶ አረጋ ከበደ ከታችኛው እርከን ጀምሮ የክልሉን መንግሥታዊ መዋቅር እንደ አዲስ እየተደራጀ መሆኑን ገለጹ።
አቶ አረጋ ከበደ ዛሬ ጳጉሜን 2/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያለውን የመንግሥት መዋቅር መልሶ የማደራጀት ሥራ መጀመራቸውን እና የመልሶ መዋቅሩ ሥራም በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ እየሠሩ መሆኑን የክልሉ ቴሌቭዥን ጣቢያ ዘግቧል።
በክልል ደረጃ የፖሊስ፣ የሚሊሻና ሌሎች የጸጥታ አስከባሪ ተቋማትን እንደገና ለማደራጀት ጥረት ማድረጋቸውንም የገለጹት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ አዲስ የሚዋቀረው አስተዳደር የሕዝብን መብትና ጥቅም ማስከበር እንዲችልና ተልዕኮውን በብቃት እንዲወጣ ሥራ እየተሠራ ነው ማለታቸው ተዘግቧል።
ክልሉን መልሶ የማደራጀቱ ሥራ እስከ መስከረም 2016 ዓ. ም. መጨረሻ ድረስ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን፣ መደበኛ የመንግሥት መዋቅር ወደ መደበኛ ሥራው እንዲገባ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የትምህር ተቋማት እንዲከፈቱ ማድረግ እንዲሁም በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች መደበኛ የመንግሥት አገልግሎት እንዲጀምር ማድረግ አስተዳደራቸው ትኩረት የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ያስታወሱት አቶ አረጋ፣ የክልሉ ነዋሪም የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
የተሻለ የጸጥታ ሁኔታ
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር በዛሬው መግለጫቸው “ክልሉ አሁን ላይ በጣም በተሻለ የጸጥታ ሁኔታ” ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ “ወደ ነበረበት ሰላም እየተመለሰ መሆኑን ለሕዝባችን ማብሰር እወዳለሁ” እንዳሉ አሚኮ ዘግቧል።
አቶ አረጋ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ክልሉ በከፍተኛ የጸጥታ ችግር ውስጥ መቆየቱን አስታውሰው፣ በሕዝብ እና በጸጥታ መዋቅሩ ትብብር “ቀውሱ አደጋ ወደማይሆንበት ደረጃ ደርሷል” ማለታቸው ተዘግቧል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው “ክልሉ አሁን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ ገብቷል . . . ክልሉን እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የማፍረስ ተልዕኮ ከሽፏል” ማለታቸውንም አሚኮ ጨምሮ ዘግቧል።
“ለአገር መብትና ጥቅም የቆመን ኃይል ስም ማጥፋት ስህተት ነው” ያሉት አቶ አረጋ፤ የክልሉ ሕዝብ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጋር እየተመካከረ ሰላሙን እያስከበረ ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ርዕሰ መስተዳደሩ ክልሉ እንዲረጋጋ ላደረጉ የፖለቲካና የጸጥታ አመራሮች ምስጋና ማቅረባቸው የተዘገበ ሲሆን፣ የተጀመረው ሰላም እንዲጸና ሁሉም ትብብር ያድርግ ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውም ተገልጿል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት በቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ምትክ አቶ አረጋ ከበደን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ነሐሴ 19/ 2015 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ባካሄደው ጉባኤ መሾሙ ይታወሳል።