እስራኤል ማንኛውም እርዳታ ወደ ጋዛ እንዳይገባ መከልከሏን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አወገዘ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በጦርነት በወደመችው ጋዛ ማንኛውም ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ እስራኤል እገዳ መጣሏን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አወገዘ።
ይህ የእስራኤል እርምጃ ከተመድ በተጨማሪ ከአረብ አገራት እና ከሰብዓዊ ረድዔት ድርጅቶች በኩል ተቃውሞ ገጥሞታል።
ግብጽ እና ኳታር እስራኤል እየፈጸመችው ያለው የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነትን የሚጥስ ነው ሲሉ፤ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ ቶም ፍሌቸር በበኩላቸው "አሳሳቢ ነው" ብለዋል።
እስራኤል በጋዛ ሙሉ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቋረጥ ያደረገችው በአሜሪካ የቀረበው የጋዛ የተኩስ አቁም አንደኛ ምዕራፍ የማራዘም ሃሳብ ሐማስ አለመቀበሉን ተከትሎ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በተጨማሪ ሐማስ የእርዳታ አቅርቦቱን "በመስረቅ "የሽብር ተግባሩን" ለመደገፍ እየተጠቀመበት ነው ሲሉ ወንጅለው ማንኛውም እርዳታ እንዳይገባ እግድ ጥለዋል።
ሐማስ ከዚህ ቀደም እርዳታ እየሰረቀ ነው የሚለውን ክስ ፍጹም አልቀበለውም ብሏል።
ሐማስ እስራኤል የተኩስ አቁሙን ለማደናቀፍ እየወሰደችው ያለው እርምጃ እንደሆነ እና "የጦር ወንጀል እንዲሁም በተኩስ አቁሙ ላይ ቀጥታ ጥቃት ነው" ሲል ከሷል።
የተኩስ አቁሙ ለ15 ወራት የዘለቀውን የጋዛ ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመ ሲሆን በዚህም 33 እስራኤላዊ ታጋቾች እንዲሁም በእስራኤል እስር ቤት ያሉ 1 ሺህ 900 ፍልስጤማውያን ተለቀዋል።
የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስራኤልን እርምጃ "የተኩስ አቁም ስምምነትን በግልጽ የጣሰ እንዲሁም አለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግጋትን የተላለፈ "ሲል እሁድ ባወጣው መግለጫ በጽኑ አውግዟል።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ "እስራኤል ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ በፍልስጤማውያን ላይ እየተጠቀመች ነው "ሲል መውቀሱን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ኳታር እና ግብጽ የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ያሸማገሉ አገራት ናቸው።
ሳዑዲ አረቢያም በተመሳሳይ እስራኤል የወሰደችውን እርምጃ ማውገዟን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል መግለጫ አውጥታለች።
" አለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ ግልጽ ነው። ወሳኝ የሕይወት አድን እርዳታ እንድናቀርብ መፈቀድ አለበት" ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊ ቶም ፍሌቸር በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ያቀረቡትን የጋዛን የመጀመሪያውን ምዕራፍ ማራዘም ሐማስ አለመቀበሉ ይህንን የእርዳታ እገዳ እርምጃ እንዲወስዱ እንዳደረጋቸው ኔታንያሁ ገልጸዋል።ሐማስ ሁለተኛው ምዕራፍ ተግባራዊ እንደሚደረግ ዋስትና ከአሸማጋዮቹ ካላገኘ አንደኛው ምዕራፍ እንዲራዘም አልስማማም ብሏል።
ጥር 11/ 2017 ተግባራዊ የሆነው የጋዛ የተኩስ አቁም የመጀመሪያው ምዕራፍ የካቲት 22/ 2017 ዓ.ም ተጠናቋል።
በመጀመሪያው ዙር 33 እስራኤላውያን ታጋቾች እንዲሁም እስራኤል በምላሹ በእስር ቤቷ ካሉት 1ሺህ 900 ፍልስጤማውያን ተለቀዋል።
የእስራኤል ጦር ከምሥራቃዊ የጋዛ ክፍል እንደሚወጣ እና የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚፈቀድላቸውም ተገልጿል።
በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገቡም ይፈቀዳል።
በሁለተኛው የስምምነቱ ዙር ተጨማሪ ታጋቾች የሚለቀቁ ሲሆን፣ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ እና "ዘላቂ መረጋጋትን ማምጣት" ያለመ ሲሆን ይህም የሚተገበረው የመጀመሪያው ዙር 16 ቀን ሲሞላው ነው።
ሦስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ ጋዛን መልሶ መገንባት ሲሆን፣ ይህም ዓመታት ይወስዳል።
በዚህ ምዕራፍ የታጋቾች አስክሬንም ይመለሳል።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ48 ሺህ189 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕፃናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የተቀናጀ እና የማያባራ ጥቃት ሁለት ሦስተኛው የጋዛ ሕንጻዎች መውደማቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።












