በኢትዮጵያ እና በሌሎች አገራት የተቋረጠውን የአሜሪካ እርዳታን ቻይና ትሸፍን ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን መመለሳቸውን ተከትሎ የአሜሪካ የውጭ እርዳታ በድንገት መቋረጥ ክፍተቱን ማን ይሞላው ይሆን? የሚል ዓለም አቀፍ ስጋትን ፈጥሯል።
የአሜሪካ መንግሥት ዋነኛ የዓለም አቀፍ የልማት የረድኤት ኤጀንሲ የረዥም ጊዜ ዕቅዱን አቋርጦ አፍግፍጓል። ልማትን እንደ ለስላሳ ኃይል የምትመለከተው ቻይና ይህንን አጋጣሚ ተጠቅማ ክፍተቱን ትሞላ ይሆን? በማለት የዘረፉ ባለሙያዎች እየጠየቁ ነው።
ቻይና ከወዲሁ ዓይኗን ካምቦዲያ ላይ ጥላላች። አገሪቱ ለአስርት ዓመታት ዓለም አቀፍ እርዳታን ተጠቅማ በጦርነት ጊዜ የተቀበሩ ፈንጂዎችን በማጽዳት ላይ ብትገኝም፣ ችግሩ አሁንም ሰላማዊ ዜጎችን እየገደለ እና እየጎዳ ይገኛል።
የትራምፕ አስተዳደር የውጭ እርዳታን ካቆመ ከአንድ ሳምንት በኋላ ፈንጂዎቹን የማጽዳት ኃላፊነት የተሰጠው የካምቦዲያ የፈንጂ ማምከን ማዕከል (ሲኤምኤሲ) ፕሮጀክቱን ለአንድ ዓመት ለማስቀጠል የሚያስችል የ4.4 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ከቻይና ቃል እንደተገባለት አስታውቋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ድንገተኛ ውሳኔን በመጠቀም ቻይና ለስላሳ ኃይሏን ለማጠናከር እና በአፍሪካ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በእስያ እና በኦሺንያ ካሉ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ዕድል መፈጠሩን አስታውቃለች።
የሲኤምኤሲ ኃላፊ የሆኑት ሄንግ ራታና እንደተናገሩት "የውጭ እርዳታ የፖሊሲ ግምገማ ካከናወነች በኋላ" ዩናይትድ ስቴትስ ድጋፏን ትቀጥላለች የሚል ተስፋ አላቸው።
ቻይና ለካምቦዲያ የሰጠችው አፋጣኝ ምላሽ ትኩረት የሚስብ ቢሆንም ዩናይትድ ስቴትስ እርግፍ አድርጋ የምትተወውን ልገሳ ለመረከብ ወይም ያለውን ክፍተት ለመሙላት መቻሏን አያመለክትም ይላሉ ባለሙያዎች።
ቤይጂንግ የምዕራቡ ዓለምን ማፈግፈግ በደስታ ተቀብላዋለች። የዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ የውጭ ድጋፍ ለማቋረጥ መወሰኑ ለዢ ጂንፒንግ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።
የቻይና እርዳታ የተለየ አቀራረብ
ቻይና በዓለም አቀፍ ልማት ውስጥ ዋና ተዋናይ ነች። በቨርጂኒያ በሚገኘው የዊልያም እና ሜሪ ኮሌጅ የምርምር ማዕከሉ ኤይድዳታ እንደዘገበው ቻይና ከአውሮፓውያኑ 2000 እስከ 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ 1.34 ትሪሊዮን ዶላር አውጥታለች።
በ2001 እና 2023 መካከል ዩናይትድ ስቴትስ 1.24 ትሪሊዮን ዶላር ማውጣቷን ላይ ቤይጂንግ ትልቋ የልማት ፋይናንስ አቅራቢ መሆኗን አመልክቷል።
ቻይናን እና ዓለምን በኢንቨስትመንት እና በመሠረተ ልማት ለማስተሳሰር ያለመው እና በአውሮፓውያኑ 2003 በተጀመረው በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ (ቢአርአይ) በኩል የቻይና የእርዳታ ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
ቻይና በ2018 የእርዳታ ድገፏን በቻይና ዓለም አቀፍ ልማት ትብብር ኤጀንሲ (ሲዲሲኤ) በማቋቋም መደበኛ አድርጋዋለች። ይህም ከአሜሪካው ዩኤስኤይድ ጋር የሚስተካከል ነው።
የቤይጂንግ የእርዳታ ሞዴል ግን ከዋሽንግተን በእጅጉ ይለያል።
እንደ ኤይድዳታ መረጃ ከሆነ ከ2012 እስከ 2021 ከተሰጠው እና 80 በመቶ የሚሆነው የአሜሪካ ድጋፍ በእርዳታ መልክ በመሰጠቱ መመለስ አይጠበቅም።
ከቻይና እርዳታ 3 በመቶው ብቻ በዚህ መልክ የሚሰጥ ነው። ቻይና በአብዛኛው ብድር ወይም የኤክስፖርት ብድር ትሰጣለች። ይህም በማደግ ላይ ላሉ አገራት ትልቋ ይፋዊ አበዳሪ ያደርጋታል።
በጤና እና በሰብአዊ እርዳታ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ካደረገው የአሜሪካ እርዳታ በተለየም ቻይና ለትላልቅ መሠረተ ልማቶች፣ የኃይል እና የማዕድን ፕሮጀክቶች ኢንቨስትመንት ቅድሚያ ትሰጣለች።
ቢአርአይ የዚህ ምሳሌ ነው። ከቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ ይልቅ በመሠረተ ልማት አማካይነት የኢኮኖሚ ዕድገትን ያበረታታል።
ቤይጂንግ ይህንን "የደቡብ-ደቡብ ትብብር" በማለት ትጠራዋለች። ይህም በዓለም ደቡባዊ ክፍል በሚገኙ አገራት መካከል ሀብት እና ዕውቀትን በመለዋወጥ ላይ የሚያተኩር ነው።
ቻይና ከተለመደው የምዕራባውያን የእርዳታ ሞዴል ራሷን ያገለለች ሲሆን፣ የምዕራባውያን እርዳታ በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ይገባል ስትልም ትከስሳለች።
ተቺዎች ግን የቻይና እርዳታ ብዙውን ጊዜ የሰብዓዊ መብትን የማይመለከት ነው ብለው ይከራከራሉ። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ሰብዓዊ መብት ለአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ መሠረት ነው።
ለምሳሌ ሩሲያ በዩክሬን ወረራ ምክንያት በምዕራቡ ዓለም ማዕቀብ ቢጣልባትም የቻይናን የልማት ፈንድ ከፍተኛ ተቀባይ ከሆኑት አገራት መካከል ነች።
በተመሳሳይ በሲሪላንካ ባለው ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት ዋሽንግተን እርዳታዋን ካቋረጠች በኋላ ቻይና መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረጓን ቀጥላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና የአሜሪካን ቦታ ለመሸፈን ዝግጁ ናት?
ብዙ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ቻይና የዩኤስኤአይድን ሚና የመተካት ዕድሏ አነስተኛ ነው። "ቻይና የምዕራባውያን መንግሥታት አንድ በአንድ በመተካት የእርዳታ ክፍተቱን አትሞላም። መሠረታዊ የፍልስፍና ልዩነት አለ" ብለዋል በኤይድዳታ የፖሊሲ ትንተና ዳይሬክተር የሆኑት ሳማንታ ከስተር።
ከፍልስፍና ባሻገር ዋናው ፈተና ደግሞ ሎጂስቲክስ ነው። መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ መንግሥታት እና ከማኅበረሰቦች ጋር በመተባበር አሜሪካ ሰፊ ዓለም አቀፍ የእርዳታ መረብን በመገንባት ለአስርት ዓመታት ሠርታለች።
ቻይና ይህ መሠረተ ልማት የላትም። "ይህን ለመገንባት ዓመታትን ይፈልግላል። ካልሆነም አሥርት ዓመታትን ይወስዳል" ሲሉ የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት ባልደረባ ዶ/ር ጂንግዶንግ ዩን ተናግረዋል።
ሌላው መሰናክል ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ናቸው። በአውሮፓውያኑ 2016 የቻይና ዓመታዊ የእርዳታ ወጪ 125 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ይህም በጠንካራ ኢኮኖሚዋ የተደገፈ ነው፤ ከዚያ ወዲህ ግን ቀንሷል። በ2021 ደግሞ በ2008 ወደነበረበት ተመልሷል። ይህ የሆነው አንድም አገሪቱ በገጠማት የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ነው።
በአገር ውስጥ የኢኮኖሚ ችግር ባለበት ቤይጂንግ ለምን የውጭ ሰብአዊ እርዳታዋን እንደምትጨምር ለሕዝቦቿ ለማስረዳት ልትችገር ትችላለች።
በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዲቦራ ብራውቲጋም "ለዚህ ዓይነቱ ወጪ በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት ግፊት በአገር ውስጥ የለም" ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ዕርዳታ ውስጥ የቻይና እና የአሜሪካ ሚና አንዱ ሲወጣ ሌላኛው የሚተካበት ዓይነት አይደለም። የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንደሚያመለክተው ቻይና የሰብዓዊ እርዳታዋን በከፍተኛ ደረጃ ለማጠናከር የምትችለበት አይደለም።
አንደምሳሌ ቻይና ኢትዮጵያ ውስጥ በመሠረተ ልማት ዝርጋት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች ተገኛለች። በአውሮፓውያኑ 2023 ዩኤስኤይዲ በሙስና ምክንያት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የምግብ እርዳታ ሲያቋርጥ ቻይና ክፍተቱን ለመሙላት የራሷን የምግብ እርዳታ ለኢትዮጵያ አላቀረበችም።
በላይደን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሳልቫዶር ሳንቲኖ ሬጊልሜ "ቻይና ለመግባት ብዙ ዕድሎች ነበሯት። በቁሳዊ ፕሮጀክቶች ረገድ ግን ቻይና ትልቁ ክፍተት አልሞላችም" ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የቻይና ስትራቴጂዊ ተጽዕኖ
ቻይና በዩኤስኤይዲ የተፈጠረውን የሰብዓዊ እርዳታ ክፍተት ባትሞላውም ዓለም አቀፋዊ ተጽእኖዋን በረጅም ጊዜ ስትራቴጂዎች እያሳደገች ትገኛለች።
ዩኤስኤይዲ የቤይጂንግን አካሄድ በመመልከት ቀደም ሲል የቻይናን ተጽእኖን ለመከላከል ልዩ ቡድን አቋቁሟል።
በቻይና ጉዳዮች ላይ የዩኤስኤይዲ ከፍተኛ አማካሪ የነበሩት ፍራንሲስኮ ቤንኮስሜ የእርዳታ እገዳውን የረዥም ጊዜ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ሲያስጠነቅቁ "ሙሉው ሥነ-ምኅዳር" እንደተስተጓጎለ እና ቻይና እንደ ኔፓል እና ካምቦዲያ ካሉ የዩኤስኤይዲ አጋሮች ጋር ግንኙነት መጀመሯን በመጥቀስ አስጠንቅቀዋል።
"ማብራት እና ማጥፋት ዓይነት ቀላል አይደለም" ሲሉም አክለዋል።
ይህ ስጋቱም ዋሽንግተን የደረሰ ይመስላል። በዓለም ላይ ብዙዎች የሚመኩበት ቁልፍ እርዳታ በድንገት መቋረጡ ለቻይና በር የከፈተ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ቻይና የትኛውም አጋር ብቻ ሳትሆን የዓለም ተመራጭ አጋር መሆኗን የምታሳይበትን ሃሳቧን ቤይጂንግ እንድታጠናክር አስችሏታል።
"ቻይና ምንም ነገር ባለማድረግ ዕድሉን ተጠቅማበታለች። አዎንታዊው የገጽታ ግንባታ የሚመጣው የአሜሪካን አስተማማኝነት ጥያቄ ውስጥ በማስገባት ነው" ብለዋል የኤይድዳታው ኩስተር።
ከትርክቱ ባለፈ ቻይና ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ለመሠረተ ልማት ግንባታ ያደረገችው ከፍተኛ ወጪ የበርካቶችን ልብ አሸንፏል። ቤይጂንግ እራሷን "ጣልቃ እንደማትገባ" አጋር በመግለጽ የልማት ሞዴሏን ለብዙ አገራት በተሳካ ሁኔታ ሸጣለች።
ቻይና በአፍሪካ የሚገኙ ስታዲየሞች ግንባታዎችን በማከናወን "የስታዲየም ዲፕሎማሲ" ከማራመድ ውጪ በላቲን አሜሪካ ትላልቅ የወደብ ግንባታዎች በማከናወን ቤይጂንግ ራሷን ለዋና ዋና የልማት ፕሮጀክቶች አጋር መሆኗን አሳይታለች።
ቻይና በምትሰጠው የልማት ድጋፍ አማካኝነት የምትጫወተው ወሳኝ ጉዳይ ታይዋን አንድ አካሏ መሆኗን የምታሳይበት "የአንድ ቻይና" መርኅ መኖሩ ነው።
በቅርቡ ይፋ በተደረገው መረጃ መሠረት 70 አገራት (በተለይም በግሎባል ደቡብ የሚገኙ) ሃሳቡን ደግፈውታል። ተንታኞች እንደሚጠቁሙት ይህ የፋይናንስ ዲፕሎማሲ ድጋፉ ከታይዋን ወደ ቻይና ምድር እንዲሸጋገር አስተዋጽኦ አድርጓል።
ፕሮፌሰር ብራውቲጋም "የቻይና መሪዎች ለረጅም ጊዜ ሲመኙት የነበረው የመልቲፖላር ዓለም (በርካታ ተሰሚለት ያላቸው ኃያላን አገራት መኖር) እየመጣ ነው። የትራምፕ አስተዳደርም ይህንኑ እያፋጠነው ነው" ብለዋል።
ቤይጂንግ ዩናይትድ ስቴትስን በመተካት ዓለም አቀፍ የእርዳታ አቅራቢነት ሚናን ለመተካት ዓመታትን ሊወስድባት ይችላል። እስከዚያው ድረስ ግን የቻይና ቋሚ እና የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ አንዳንድ ጥቅሞችን ለማግኘት ዝግጁ ያደርጋታል።












