የአሜሪካ እርዳታ መቋረጥ በኢትዮጵያ በሚካሄዱ የጤና እና የሰብዓዊ እርዳታ ሥራዎች ላይ ምን ያስከትላል?

የጤና ባለሙያ፣ የእርዳታ እህል የተሸከመ ግለሰብ እና የሚያነቡ ታዳጊዎች

የፎቶው ባለመብት, USAID

ዶናልድ ትራምፕ ያሳለፉትን ትዕዛዝ ተከትሎ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤድ) በዓለም ዙሪያ የሚሰጠውን እርዳታ እና ድጋፍ በአስቸኳይ በማቆሙ በበርካታ የአፍሪካ አገራት የጤና ድጋፎች እየተስተጓጎሉ ነው።

ይህ የሆነው ፕሬዚዳንት ትራምፕ የውጭ ፖሊሲያቸው ውጤታማነት እና ወጥነት እስኪገመገም ድረስ ለ90 ቀናት የውጭ የልማት ድጋፍ እንዲቆም ባሳለፉት የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዝን ምክንያት ነው።

ቀደም ሲል የነበረው የአሜሪካ አስተዳዳር ለጤና፣ ለግብርና፣ ለትምህርት፣ ለኢነርጂ እና ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ለዓመታት የሚውል በቢሊዮኖች የሚገመት ዶላር ድጋፍ አድርጎ ነበር።

ዩኤስኤድ የሚያደርገው የጤና ድጋፍ ለአፍሪካ ወሳኝ ሲሆን፣ኤችአይቪ/ኤድስ፣ ቲቢን እና ወባን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ድጋፍ ከሚያደርጉ ተቋማትም አንደኛው ነው።

ሆኖም የትራምፕን ትዕዛዝ ተከትሎ በድርጅቱ ድጋፍ ሥራቸውን የሚያከናውኑ ተቋማት ሥራቸው ላይ እንቅፋት የተፈጠረ ሲሆን፣ መጻኢ ዕድላቸውም ምን እንደሚሆን ግራ ተጋብተዋል።

በማላዊ በዩኤስኤድ የሚደገፉ ፕሮጀክቶች መቆማቸውን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።አምስት ትላልቅ የእርዳታ ድርጅቶችም ዩኤስኤድ በበርካታ አገራት ሥራ እንዲቆም በማዘዙ ምክንያት በጤና ተቋማት የሚሠሩ ሠራተኞቻቸው ሥራ እንዳይገቡ በደብዳቤ አሳውቀዋል።

የዓለም ጤና ድርጅትም ድጋፉ በአስቸኳይ መቆሙ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት በሚከናወኑ የኤችአይቪ ፕሮግራሞች ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ በጥልቅ እንዳሳሰበው ገልጿል።

የአሜሪካ ፕሬዚደንት የአስቸኳይ ጊዜ የኤድስ ድጋፍ የሆነውን (ፔፕፋር) ጨምሮ በአሜሪካ የሚደገፉ ፕሮጀክቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ30 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የኤችአይቪ ሕክምና እንዲያገኙ አድርጓል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በመሆኑም ድጋፉ መቋረጥ ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ሰዎችን ለህመም እና ለሞት የሚዳርግ እንዲሁም በሽታውን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅትም ባወጣው መግለጫ "ሕይወት አድን የኤችአይቪ ሕክምናዎች እና እንክብካቤዎች አቅርቦትን ለማረጋገጥ ከውሳኔው ነጻ እንዲሆኑ የአሜሪካን መንግሥትን እንጠይቃለን" ብሏል።

የትራምፕ አስተዳደር በበኩሉ ማክሰኞ ዕለት ሕይወት አድን የኤችአይቪ መድኃኒቶች እና የሕክምና አገልግሎቶች ውሳኔው እንደማይመለከታቸው አስታውቋል።

ሆኖም ውሳኔው በፔፕፋርም ሆነ በዩኤስኤድ የሚደገፉ ሌሎች ድርጅቶች የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ምን እንደሚያስከትል ግልፅ አይደለም።

በአፍሪካ፣ እስያ፣ አውሮፓ እና በአሜሪካ ያሉ የድርጅቱ ባለሥልጣናትም ይህ ውሳኔ ለሥራቸው ምን ማለት እንደሆነ እንዲሁም ሥራቸውን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ የተላለፈውን ትዕዛዝ የሚቀለብስ መሆን አለመሆኑ ግልጽ እንዳልሆነ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጸዋል።

ቢቢሲ በኢትዮጵያ ያሉ የድርጅቱን እንዲሁም በድርጅቱ የሚደገፉ ድርጅቶች ሠራተኞችን ለማነጋጋር ጥረት ያደረገ ቢሆንም "ለሦስተኛ ወገን ምንም ዓይነት መረጃ እንዳይሰጡ የሚከለክል ኢይሜል እንደተላከላቸው " በመግለጽ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ሆኖም ሮይተርስ የዜና ወኪል ያነጋገራቸው በትግራይ ክልል፣ የማኅበራዊ አገልግሎት፣ ጤና እና ልማት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ይርጋ ገብረ እግዚአብሔር እያካሄዱት ያሉትን ሥራ ጭምር እንዲያቆሙ እንደተነገራቸው፤ ነገር ግን ትዕዛዙ ግልጽ አለመሆኑን አስረድተዋል።

ድርጅቱ 30 ሺህ ለሚሆኑ ተጠቃሚዎች የምግብ፣ የኤችአይቪ መድኃኒቶችን እና የሕፃናት ትምህርት አገልግሎቶችን የሚያቀርበው ከዩኤስኤድ በሚያገኘው ድጋፍ እንደሆነም በዘገባው ተጠቅሷል።

አቶ ይርጋ ጨምረውም ለሠራተኞቻቸው የየካቲት ወር ደሞዝ መክፈል ይችሉ እንደሆነም ግልጽ አለመሆኑን ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በሌላ ዘገባው ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ የዩኤስኤድ ሠራተኞች ያለክፍያ ፈቃድ እንዲወጡ እንደተደረጉ እና የተወሰኑትም ውላቸው መቋረጡን አመልክቷል።

የእርዳታ እህል የያዙ የስንዴ ማዳበሪያዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ አደጋዎች በርካታ ሰብዓዊ ቀውሶች እያጋጠሟት ባለችው ኢትዮጵያ ዩኤስኤድ በቀጥታ እና በበርካታ አጋሮቹ አማካኝነት ድጋፍ ያደርጋል።

እንደ ዩኤስኤድ ሪፖርት ከሆነ በ2022/2023 የበጀት ዓመት ብቻ በሰሜን ኢትዮጵያ ላለው ውስብስብ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ የቀረበውን 1 ቢሊዮን ዶላር ጨምሮ ለኢትዮጵያ 2 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ሰጥቷል።

ከዚህም በተጨማሪም ለማገገሚያ፣ ለአደጋ ቅነሳ እና መቋቋሚያ ከ101 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።

ድርጅቱ በግብርና፣ በምግብ፣ በጤና፣ በምርታማነት፣ በሥነ ምግብ፣በመጠለያ እና ውሃን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ለሚከናወኑ ሥራዎች ድጋፍ ያደርጋል።

ከዚህም ባሻገር የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአማራ፣ በአፋር እና በትግራይ ክልሎች የገንዘብ እና የምግብ ድጋፍ እንዲያደርግ የቀጥታ ድጋፍ ሰጥቷል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ላለው ሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት አሜሪካ በዩኤስኤድ አማካኝነት ተጨማሪ 80 ሚሊዮን ዶላር የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቆ ነበር።

አሜሪካ በዓለም ከፍተኛ እርዳታ የምትሰጥ አገር ስትሆን በአውሮፓውያኑ 2023 በጀት ዓመት ብቻ ኢትዮጵያን ጨምሮ 72 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጋለች።በፔንሲልቫኒያ ስቴር ዩኒቨርሲቲ በሕብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት አበባየሁ ንጉሤ፣ ይህ ድጋፍ ለጊዜውም ቢሆን ያዝ መደረጉ በጤና ተጠቃሚዎች፣ የምግብ ዋስትና ችግር ላለባቸው፣ለሰብዓዊ ቀውስ ለተዳረጉ እንዲሁም ጤና፣ ትምህርት እና ግብርናን ጨምሮ በድርጅቱ ድጋፍ በተለያዩ ዘርፎች በሚሠሩ ምርምሮች ላይ መስተጓጎልን እንደሚፈጥር ይናገራሉ።

ድርጅቱ ባለፉት አስርት ዓመታት ወረርሽኞችን ከመለየት እና በሽታ የሚከሰትባቸው አገራት ላይ የአቅም ግንባታ በመስጠት ብዙ አስተዋፅኦ ማድረጉን ያነሱት ዶ/ር አበባየሁ፣ ድጋፉን ማቆሙ በተለይ በዓለም የጤና ጥበቃ ሥራ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖን ያስከትላል ይላሉ።

"በተለይ የኤችአይቪ መድኃኒት በቀጣይነት መወሰድ ስለሚኖርበት የሕይወት መጥፋት፣ እንዲሁም የመድኃኒት መላመድን (ድራግ ሬሲስታንስ) ሊያስከትል ይችላል" ብለዋል።

የኤችአይቪ የደም ናሙና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሌላ በኩልም አሜሪካ ድጋፍ ከምታደርግላቸው አገራት ጋር ባላት ግንኙነት ላይ ክፍተትን እንደሚፈጥር ይገልጻሉ።

"እርዳታ 'በነጻ የሚደረግ' ባለመሆኑ ተቀናቃኝ ኃያል አገራት ይህንን ክፍተት ለመሙላት ዕድሉን ሊጠቀሙበት ይችላሉ" ሲሉም ውሳኔው በአሜሪካም ላይ የራሱ ጉዳቶች እንዳሉት አስተያየተቻውን ሰጥተዋል።

ሆኖም በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ቀውሶችን ባሉባቸው አገራት ላይ ዳፋው የበዛ ነው ይላሉ።

ዶ/ር አበባየሁ ይህንን በሦስት ከፍለው ይመለከቱታል። አንደኛው የምግብ፣ የመጠለያ፣ የውሃ እና የጤና ተጠቃሚዎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ሲሆን፣ የእነዚህ አገልግሎቶች መቋረጥም ወረርሽኞች እንዲከሰቱ ምክንያት ይሆናል።

ሌላኛው የዩኤስኤይዲ ፕሮግራም ተቀጣሪዎች ሥራ እንዲያጡ ማድረጉ እና በቤተሰብ እና በማኅበረሰቡ ላይ ሥራ አጥነት ማስከተሉ ነው።በዚህም በተለያዩ አገራት ያሉ የድርጅቱን ፕሮግራሞችን የሚቆጣጠሩ እና በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ያሉ እንዲሁም ጆንስ ሆፕኪንስን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲ ፕሮግራሞች ላይ የሚሠሩ አሜሪካውያን ላይም ተጽእኖ አለው።

አሜሪካ የዩኤስኤድን ብራንድ (መለያ) ለመፍጠር ለበርካታ ዓመታት ሠርታለች የሚሉት ዶ/ር አበባየሁ ይህ መለያ እንዲደበዝዝ ማድረጉ ሌላኛው ተፅዕኖ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።

ኢትዮጵያ ያለዩኤስኤድ ድጋፍ ምን መልክ ይኖራት ይሆን?

የተባበሩት መንግሥታት እንደ አውሮፓውያኑ 2024 ባወጣው ሪፖርት በኢትዮጵያ ባለው ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የፀጥታ ችግር ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ከ21 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ብሏል።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ተቋም ባወጣው አንድ ሪፖርት እንዳመለከተው በአገሪቱ ውስጥ በአውሮፓውያኑ 2023 ከ603 ሺህ በላይ ሰዎች ኤችአይቪ በደማቸው የሚገኝ ሲሆን፣ ከመካከላቸው አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው።

በኤችአይቪ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከአውሮፓውያኑ 2022 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም፣ በቅርብ ጊዜ የግጭት ቀጠና በሆኑ ክልሎች እና በሌሎችም አካባቢዎች ሥርጭቱ እየተስፋፋ መሆኑን የሚያሳዩ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።

ዩኤስኤይድ በብዛት ትኩረቱን የሚያደርገው ተላላፊ በሽታዎችን በመቆጣጠር ላይ መሆኑን የሚገልጹት ዶ/ር አበባየሁም፣ ይህ ፕሮግራሙ ቢቆም የእነዚህ ተላላፊ በሽታዎች ሥርጭት መጨመሩ አይቀሬ ነው ይላሉ።

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ዝግጁ ያልሆኑ አገራት ይህ በሚሆንበት ጊዜ እነዚህ በሽታዎች የመስፋፋት ዕድላቸው የሰፋ እንደሚሆን ይናገራሉ።

በተለይ ግጭት በሚካሄድባቸው እና በርካታ ሕዝብ በሚኖርባቸው ክልሎች የሰብዓዊ ቀውሱን የባሰ ሊያደርገው እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ይህ ሁኔታ "ትምህርት የሚሰጥ ነው" የሚሉት ባለሙያው፣መንግሥት በእርዳታ ድርጅቶች ላይ ሃሳቡን ከመጣል ይልቅ በአገር ውስጥ ያለውን አቅም ማጠናከር እና ቅድሚያ በመስጠት መሥራት እንደሚገባው ይመክራሉ።

አዲሱ የትራምፕ አስተዳዳር የአሜሪካ ሕይወት አድን የሆኑ ድጋፎች እንደማይቋረጡ ቢገልጽም፣ አገራት ለድጋፉ መቋረጥ ዝግጁ ባለመሆናቸው የአሜሪካ መንግሥትን ማግባባት ሊያስፈልጋቸው እንደሚችልም ይጠቁማሉ።

ክትባት የያዙ ቦርሳዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images