የዩኤስኤይድ ድጋፍ በመቆሙ የተነሳ በ50 አገራት የኤችአይቪ ሕክምና ተስተጓጉሏል- የዓለም ጤና ድርጅት

ዩኤስአይዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ በመቋረጡ የተነሳ ኤችአይቪ፣ ፖሊዮ፣ ኤምፖክስ እና የበርድ ፍሉን ለመከላከል የሚከናወኑ ስራዎች መስተጓጎላቸውን ተናገሩ።

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ወጪ "በፍፁም አሳማኝ ምከንያት ሊቀርብበት የማይችል" በማለት ለመዝጋት እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል።

ሆኖም የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፤ የትራምፕ አስተዳደር ሌሎች መፍትሄዎች እስኪገኙ ድረስ ድጋፍ ማድረጉን እንዲቀጥል ተማጽነዋል።

በ50 አገራት የኤችአይቪ ሕክምና እና ሌሎች አገልግሎቶች መቋረጣቸውንም ረቡዕ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

ለመጀመርያ ጊዜ በይፋ የዩኤስ ኤይድ ድጋፍ ስለመቋረጡ በጄኔቫ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩት ዶ/ር ቴድሮስ፤ "የአሜሪካ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች አሉ... እኛን ስጋት ውስጥ መክተት ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው" ብለዋል።

በተለይም የፕሬዚዳንቱ የአደጋ ጊዜ የኤድስ እርዳታ ዕቅድ (ፒኢፒኤፍኤአር) በ50 አገራት የሚሰጣቸውን የኤችአይቪ ሕክምና፣ ምርመራ እና መከላከል አገልግሎቶች አቋርጧል ብለዋል።

ለነፍስ አድን አገልግሎት የሚደረገው ድጋፍ እንዳይቋረጥ የተደረገው ተማጽኖ ፍሬ አለማፍራቱን ተናግረዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ፤ "ክሊኒኮች ተዘግተዋል፤ የጤና ባለሙያዎች እረፍት እንዲወስዱ ተደርገዋል" ብለዋል።

የዓለም ጤና ባለሙያዎች የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ በመቋረጡ ምከንያት በሽታዎች ሊስፋፉ እንደሚችሉ፣ ክትባቶች ለማጎልበት የሚከናወኑ እና በአዳዲስ ሕክምናዎች ላይ የሚደረጉ ምርምሮች እንደሚስተጓጎሉ አስጠንቅቀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ ዩኤስ ኤይድ "ብቃት የሌለው እና ሙሰኛ ነው" ሲሉ ይከራከራሉ።

አክለውም 10,000 የሚጠጉ የተቋሙ ሠራተኞችን ለመቀነስ እና ዩኤስ ኤይድ ሲሰጣቸው የነበሩ በርካታ እርዳታዎችን እንደሚያቆም ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ኤጀንሲው የተለያዩ የጤና አገልግሎቶችን ለመደገፍ እና ለሰብዓዊ እርዳታ ወደ 40 ቢሊዮን ዶላር፣ ከጠቅላላው የአሜሪካ መንግሥት ዓመታዊ ወጪ 0.6% ያህል ያወጣል።

አብዛኛው የዩኤስ ኤይድ ገንዘብ በእስያ፣ ከሰሃራ በታች ባሉ አፍሪካ እና በአውሮፓ የሚሰጥ ቢሆንም በዋነኛነት በዩክሬን ውስጥ ለሰብአዊ ዕርዳታ ይውላል።

ዋይት ሀውስ የፌደራል መንግሥትን ወጪ ለመቀነስ በሚያደርገው ጥረት ላይ እየሰራ ያለው ቢሊየነሩ ኢሎን መስክ፤ ቀደም ሲል የረድኤት ድርጅቱ "ወንጀለኛ ድርጅት ነው" ሲል ተናግሮ ነበር።

ትራምፕም ሆነ መስክ ይህንን ውንጀላቸውን የሚደግፍ ምንም ዓይነት ማስረጃ አላቀረቡም።

ትራምፕ ዩኤስ ኤይድ የሚሰጠውን ድጋፍ ከማቆም ባሻገር አገራቸው ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት እንድትወጣ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል።

በባይደን አስተዳደር ዘመን አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጤና ኤጀንሲ ትልቁ ገንዘብ ለጋሽ ነበረች። እ.ኤ.አ. በ2023ም ከኤጀንሲው በጀት አንድ አምስተኛ የሚሆነውን አበርክታለች።

ዶ/ር ቴድሮስ፤ የትራምፕ ውሳኔ በአገሮች መካከል በዓለም አቀፍ የጤና ስጋት ላይ ያለውን ትብብር እየጎዳ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ዩናይትድ ስቴትስ በሰው ልጆች ላይ የወፍ ጉንፋን እያደረሰ ያለውን ሪፖርት ማድረግ መቀነሷን ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ጥቅም ላይ ከዋሉት ጋር ተመሳሳይ የሆኑ የአደጋ ጊዜ እርምጃዎችን በመጠቀም እጥረት ያለባቸው አገልግሎቶች ለማዳረስ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት የኤችአይቪ፣ ሄፓታይተስ እና በግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ ኢንፌክሽኖች (STI) ፕሮግራሞች ዳይሬክተር ሜግ ዶኸርቲ፣ በአገሮች መካከል ወሳኝ የሆኑ የመድኃኒት አቅርቦቶችን በጋራ ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ይኹን እንጂ የተሻለና የረዥም ጊዜ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። "በአገራት መካከል የሚደረግን ትብብር እና ድጋፍ ስንፈልግ ቆይተናል፤ ይህ ግን የአጭር ጊዜ አካሄድ ነው" ሲሉም ሀሳባቸውን ገልጸዋል።