ፑቲን "ለፋሲካ የተኩስ አቁም" ቢያውጁም ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን ዜሌንስኪ ተናገሩ

በሩሲያ የአየር ጥቃት የወደመ መኖርያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወታደሮቻቸው ለፋሲካ በዓል "የተኩስ አቁም" እንዲደረግ እና "ማንኛውንም ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ" ማዘዛቸውን ተናግረዋል።

ቭላድሚር ፑቲን በትናንትናው ዕለት ለ30 ሰዓታት፣ እስከ እሁድ እኩለ ለሊት ድረስ የሚቆይ፣ የተኩስ አቁም ያወጁ ሲሆን የሩሲያ ወታደሮች "የሚፈጸሙ ጥሰቶች" ካሉ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ አገራቸው ይህንን የተኩስ አቁም እንደምታከብር ቢናገሩም ሞስኮ ቃሏን አጥፋለች ሲሉ ከስሰዋል።

"ሩሲያ እንዲህ በድንገት ሙሉ በሙሉ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የመሳሪያዎቿን ላንቃ ፀጥ ለማሰኘት ከወሰነች ዩክሬንም በሩሲያ ውሳኔ መሰረት እርምጃ ትወስዳለች" ብለዋል ።

"ተግባራችን ተመጣጣኝ እና አቻ ይሆናል። ሙሉ እና ቅድመ ሁኔታ የሌለው የ 30 ቀን የተኩስ አቁም ሀሳብ በጠረጴዛው ላይ እንደተቀመጠ ነው። ምላሹ ከሞስኮ መምጣት አለበት" ሲል በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

አክለውም ሩሲያ በኩርስክ እና ቤልጎሮድ አካባቢዎች ውግያ መቀጠሏን እና የሩስያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች አሁንም ጥቃት እየፈጸሙ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ በአንዳንድ አካባቢዎች ተኩስ መቆሙንም ተናግረዋል።

ዩክሬን የተኩስ አቁሙን ከፋሲካ ምሽት በላይ ለማራዘም ዝግጁ መሆኗን ዜሌንስኪ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል አሜሪካ የ30 ቀን የተኩስ አቁም ሀሳብ ያቀረበች ሲሆን ዩክሬን ተስማምታ ነበር።

ለፑቲን መግለጫ በኤክስ ገጻቸው ላይ ምላሽ የሰጡት የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሲቢሃ "ፑቲን ለተኩስ አቁም ዝግጁ መሆኑን መግለጫ ሰጥቷል። ከ30 ቀናት ይልቅ 30 ሰዓታት" ብለዋል።

"እንደ አለመታደል ሆኖ የሚሰጠው መግለጫ ከድርጊቶቹ ጋር የማይጣጣሙ መሆናቸውን የሚያሳይ ረዥም ታሪክ አለን። ቃላቶቹ ሊታመኑ እንደማይችሉ እናውቃለን። እናም ከቃላቱ ይልቅ ድርጊቶቹን እንመለከታለን" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፑቲን ጊዚያዊ የተኩስ አቁም መጀመሩን ከጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ቫለሪ ገራሲሞቭ ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ነው ይፋ ያደረጉት።

ፑቲን ለጌራሲሞቭ "በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ በመመስረት...ሩሲያ የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተኩስ አቁም ማድረጓን እገልጻለሁ። ስለዚህ ሁሉም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ አዝዣለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

"ዩክሬን የእኛን ምሳሌ ትከተላለች ብለን እናስባለን። ወታደሮቻችን የተኩስ አቁሙን የሚጥስ የጠላት እንቅስቀሴዎችን፣ ማንኛውንም የጥቃት እርምጃዎችን ለመመከት ዝግጁ መሆን አለባቸው።"

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የተኩስ አቁም ስምምነቱ በዩክሬን በኩል "ተፈጻሚ" እስከሆኑ ድረስ እነርሱም እንደሚያከብሩ ተናግረዋል።

በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት በድንገት የጦርነት ማቆም ጥሪ ሲተላለፍ ይህ የመጀመርያው አይደለም።

በጥር 2023 የኦርቶዶክስ እምነትተከታዮች በሚያከብሩት የገና በዓል ወቅት የተኩስ አቁም ታውጆ ሁለቱም ወገኖች በቀረበው ሀሳብ ላይ መስማማት ባለመቻላቸው ፈርሷል።

በዩኬ የሚገኘው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ የፑቲንን የተኩስ አቁም መግለጫ አስመልክቶ በሰጠው ምላሽ "ፑቲን ሙሉ በሙሉ የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ እና የዩክሬን መንግሥት እንደሚያቀርበው ጥሪ የፈጸመውን አሰቃቂ ወረራ በማቆም ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩበት ጊዜ አሁን ነው። ለፋሲካ በዓል የሚደረግ የአንድ ቀን እረፍት ብቻ አይደለም" ብሏል።

ቸ። በዚህ ጦርነት ከሁለቱም ወገኖች በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ አብዛኞቹ ወታደሮች የሆኑ፣ መሞታቸው ተገልጿል።

ጦርነቱን ለማቆም አሜሪካ ከሩሲያ ጋር በቀጥታ እየተነጋገረች ቢሆንም ምንም የታየ ተጨባጭ ለውጥ የለም ።

ባለፈው ወር ሞስኮ በአሜሪካ የቀረበውን ሙሉ በሙሉ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም ሃሳብ ውድቅ አድርጋለች።

ዩክሬን በተኩስ አቁሙ ሃሳብ መስማማቷን የገለፀችው ወድያው ነበር።

በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ተጨማሪ የሰላም ስምምነት ንግግር ለማድረግ ጥረት በሚደረግበት ወቅት ሁለቱ አገራት ውይይቱን 'ከባድ' የሚያደርጉት ከሆነ አሜሪካ በአሸማጋይነት እንደማትሳተፍ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አርብ ዕለት አስታውቀዋል።

ይህን ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አሜሪካ "ለሳምንታት ወይም ወራት አንታገሳቸውም። ሌሎች ትኩረታችንን የሚሹ ጉዳዮች አሉብን" ካሉ በኋላ ነው።

አክለውም "አሁን በፍጥነት መወሰን አለብን። ይህንን ስል ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ሆነም አልሆነም ስለ ጥቂት ቀናት ጉዳይ ነው የማወራው" ብለዋል።

"ይህ የማይሆን ከሆነ ወደ ሌሎች ጉዳዮቻችን እንሄዳለን"