ሩሲያ እና ዩክሬን የሰላም ስምምነቱን 'ከባድ' ካደረጉ አሜሪካ እንደማታሸማግል ትራምፕ ተናገሩ

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ተጨማሪ የሰላም ስምምነት ንግግር ለማድረግ ጥረት በሚደረግበት ወቅት ሁለቱ አገራት ውይይቱን 'ከባድ' የሚያደርጉት ከሆነ አሜሪካ በአሸማጋይነት እንደማትሳተፍ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጹ።

የሰላም ስምነት ላይ "በአፋጣኝ" መደረስ አለበትም ብለዋል ትራምፕ።

በቀናት ውስጥ በሁለቱ አገራት መካከል ስምምነት ላይ የመድረስ ምልክት ካልታየ አሜሪካ ውይይቱን ጥላ እንደምትወጣ የውጭ ጉዳዩ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ ተናግረዋል።

"ለሳምንታት ወይም ወራት አንታገሳቸውም። ሌሎች ትኩረታችንን የሚሹ ጉዳዮች አሉብን" ብለዋል።

ሩሲያ ከሰሞኑ በፈጸመችው ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸው እና ከ100 በላይ ሰዎች መጎዳታቸው ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠዋል።

ትራምፕ "የሰዎችን ሞት እናስቆማለን። ግን ሁለቱም ወገኖች ሒደቱን ከባድ ካደረጉት 'እናንተ ሞኝ ናችሁ' ብለን ራሳችንን ከውይይቱ እናገልላለን" ብለዋል።

ትራምፕ በአፋጣኝ የሰላም ስምምነት ላይ ይደረሳል ብለው ቢያስቡም እስካሁን ውጤት አልተገኘም።

በፓሪስ ከአውሮፓ መሪዎች ጋር ውይይት ሲደረግ ነበር ማርኮ ሩቢዮ በአፋጣኝ የሰላም ስምምነት መደረግ አለበት ያሉት።

ትራምፕ ሥልጣን በያዙ በ24 ሰዓታት ጦርነቱን እንደሚያስቆሙ ሲናገሩ ነበር።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ "እየተደረገ ያለው ድርድር ከባድ ነው። ጥቅማችንን አስከብረን የሰላም ስምምነት ማድረግ ነው የምንፈልገው። ለሰላም ስምምነት ዝግጁ ነን" ብለዋል።

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጅያ ሜሎኒ እና ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከተገናኙ በኋላ ቫንስ "ደም አፋሳሹን ጦርነት ለማስቆም ተስፋ ይታየናል" ብለዋል።

የዩክሬን ማዕድናት እና የኃይል ዘርፍ መሠረተ ልማት እንዲሁም ነዳጅ በዚህ ድርድር ውስጥ ቀርበዋል። አሜሪካ ከዚህ ቀደም ላደረገችው ወታደራዊ ድጋፍ በምላሹ የዩክሬን ማዕድናት ቀርበው አሜሪካ ደግሞ ጦርነቱ እንዲቆም ጫና እንደምታደርግ ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በድርድሩ የሰላም ስምነት ከማድረግ በተጨማሪ የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጣቸውም ይፈልጋሉ።

አሜሪካ እስካሁን ለዩክሬን ግልጽ የደኅንነት ማስተማመኛ ከመስጠት ተቆጥባለች።

አሜሪካ በዩክሬን ኢንቨስት ስታደርግ ከሩሲያ የሚሰነዘር ጥቃት እንደማይኖር አሜሪካ ትናገራለች።

የዩክሬን የምጣኔ ሃብት ሚኒስትር ዩሊያ ሱድያድንኮ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰውን የምጣኔ ሃብት ስምምነት አስታውቀዋል።

የማዕድን ስምምነት በቀጣይ ሳምንታት እንደሚፈረም ትራምፕ ገልጸዋል።

በአውሮፓ ኅብረት የዩክሬን ፓርላማ ኮሚቴ መሪ ኢቫና ክላምፑሽ-ትስቲድዝ "ለሕዝባችንና ለአገራችን የሚጠቅም ስምምነት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሪ ሳቢሀ የትራምፕን ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የአሜሪካውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ካነጋገሩ በኋላ "ፍትሐዊና ዘላቂነት ያለው የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ተወያይተናል። የተኩስ አቁምና የጋራ ደኅንነት ማዕቀፍ የሚካተትበት ይሆናል" ብለዋል።