ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች ጦርነቱን ማቆም የማይፈልጉት ለምንድን ነው?
እሑድ ጥር 24/2018 ዓ. ም. ቢጫ፣ ሰማያዊ እና ነጭ ቀለም ያለው የሱዳን አየር መንገድ አውሮፕላን በካርቱም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ማኮብኮቢያ ላይ አረፈ።
160 ተሳፋሪዎች ከአውሮፕላኑ ሲወርዱ በደስታ እየተቃቀፉ ፎቶ ይነሱ ነበር። ይህ ከሦስት ዓመት ወዲህ ወደ ከተማው የገባ ሁለተኛው የንግድ በረራ ነበር።
ከሳምንታት ቀደም ብሎ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ይህ ዓመት "የሰላም ዓመት" እንደሚሆን አውጀው ነበር። ካሚል ኢድሪስ በጥር ወር በወታደሮች የሚመራው መንግሥት ሚኒስትሮች ወደ ፈራረሰችው የአገሪቱ ዋና ከተማ እንደሚመለሱ ተናግረው ነበር።
ከተማዋ ከሦስት ዓመታት ገደማ በፊት በሚያዝያ ወር የፈነዳው የእርስ በርስ ጦርነት ማዕከል ሆና ቆይታለች። ይህም ዋና ከተማዋን በእሳት አቃጥሎ መንግሥቱን በቀይ ባሕር ዳርቻ ወደምትገኘው ፖርት ሱዳን ለደኅንነቱ መሸሸጊያ እንዲያደርጋት አስገድዶታል።
ውድመቱ በእጅጉ የሚስደነግጥ ነው፤ የመንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ባንኮች እና ረዣዥም የቢሮ ሕንፃዎች በገጠማቸው ቃጠሎ ምክንያት ከስለው ቆመዋል።
በወቅቱ በሲቪሎች ላይ ከፍተኛ ውድመት፣ ሞት፣ ረሃብ እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ያስከተለው እና ሱዳንን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት "መውጫ ወደሌለው አዘቅት እየከተታት" ወዳለው ጦርነት ያስገባ ከባድ ነውጥ ነበር የተከሰተው።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በምዕራብ ዳርፉር ክልል የምትገኘውን ከተማ ኤል ፋሸርን መቆጣጠሩ ትልቅ ድል ነበር። ነገር ግን በታጣቂዎቹ የተፈጸሙ የተለያዩ ግፎች እና ጭካኔዎችን የሚያጋልጡ ማስረጃዎች መውጣት ዓለም አቀፍ ተቃውሞ እንዲነሳበት ምክንያት ሆኗል።
ይህንንም ተከትሎ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን፣ የዓለም ኃያላን በመጨረሻ ጣልቃ በመግባት ማለቂያ የሌለውን የሱዳናውያንን መከራ ለማስቆም የሚችሉ መስሎ ነበር።
ሆኖም ግን የወጡት ውግዘቶች እና ጠንካራ መግለጫዎች ምንም ለውጥን ሳያመጡ ጦርነቱ ከዋና ከተማው ርቆ ቀጠለ። የተቀረው ዓለምም ትኩረቱ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚፈጸሙ የአየር ጥቃቶች ላይ ሆነ።
የሱዳን አስፈሪ ጦርነት ሦስተኛ ዓመቱን ሊደፍን በተቃረበበት በአሁኑ ጊዜ የጦርነቱ ምክንያት የሆኑ መሠረታዊ ችግሮች መፍትሄ አላገኙም። ዓለም አቀፍ ቁጣ እና ተቃውሞ ተፋላሚዎቹን ለማስገደድ በቂ ካልሆነ፣ ሁለቱ ወገኖች ጦርነቱን እንዲያቆሙ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?
የማያቋርጥ ውጊያ
ሱዳን በአውሮፓውያኑ 1956 ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ካሉት 70 ዓመታት አብዛኛውን ማለትም 58 ዓመቱን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።
ነገር ግን ቀደም ሲል የተከሰቱት ጦርነቶች የተካሄዱት ከዋና ከተማዋ ካርቱም ርቀው በሚገኙ የድንበር አካባቢዎች ነው።
የአሁኑ ጦነርት ግን ከአገሪቱ እምብርት ተነስቶ ታይቶ የማይታወቅ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ከመኖሪያቸው አፈናቅሏል፣ ክፍፍልን አባብሶ እና አገሪቱን ለሁለት እንድትሰነጠቅ የሚያደርግ አደጋ ደቅኗል።
ጦርነቱ የተጀመረው በሱዳን ጦር ኃይሎች እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል በተፈጠረ የሥልጣን ሽኩቻ ነው።
ፈጥኖ ደራሽ ላይሉ በአውሮፓውያኑ 2019 ሕዝባዊ ተቃውሞን ከሥልጣን የተባረሩት የአገሪቱ የረዥም ጊዜ የቀድሞ ወታደራዊ ገዢ በኦማር አልበሽር የተሾሙ እና ታማኛቸው የነበረ ነው።
አል ባሽር ሄሜቲ በመባል የሚታወቁትን ጄነራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ፣ በአገሪቱ ጦር ሠራዊቱ ውስጥ ሊገጥሟቸው ከሚችሉ ተግዳሮቶች እንዲከላከሏቸው እንደግል ዘባቸው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን እንዲመሩ ሥልጣን ሰጥተዋቸው ነበር።
ነገር ግን አል ባሽር ከሥልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ በሄሜቲ እና በሱዳን ጦር አዛዡ ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን መካከል የነበረው ውጥረት ወደ ሰፊ ግጭት ተለወጠ።
መጀመሪያ ላይ "ይህ የሱዳን ጦርነት ሳይሆን፣ በአገሪቱ የደኅንነት ኃይሎች መካከል የተፈጠረ ግጭት ነው የሚል ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር" ሲሉ የኮንፍሉዌንሲ የተባለው የጥናት ቡድን መሥራች የሆኑት የሱዳን ፖለቲካ ተንታኝ ኹሉድ ካይር ተናግረዋል።
ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች አብረዋቸው የሚሰለፉ አጋሮችን በማስፋት ጥያቄ እና ፍላጎታቸውን ወደ ኋላ በመለጠጥ ከሱዳን የአገርነት ምሥረታ ጊዜ አንስቶ የነበረ አድርጎ እስከማቅረብ ደረሱ።
የሱዳን ወታደራዊ ኃይል በአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ መጠን ያለውን ሀብት በመቆጣጠር በዘመድ አዝማድ እና በመጠቃቀም ባህል ላይ የተመሠረተ ነው። ከግመል ንግድ ተነስተው ስኬታማ ነጋዴ የሆኑት ሄሜቲ ከፈጥኖ ደራሽ ኃያል መሪነት ከፍተኛ ሀብት ማካበት ችለዋል።
በተጨማሪም ከምዕራብ ዳርፉር ክልል እንደመጣ ሰው ከዋና ከተማው ባሻገር ያለው ማኅበረሰብን ቅሬታ እና መገለልን በማንሳት የመሪነት ዕድልን አግኝተዋል።
ሄሜቲ አሁን ግጭቱን የኅልውና ጥያቄ አድርገውታል። በዚህም ቡድናቸው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የወታደራዊ ኃይሉ የሚያቀነቅነው ከቅኝ ግዛት በኋላ የተመሠረተውን በወታደሮች ቁጥጥር ሥር ያለውን መንግሥት የማፍረስ ፍላጎት አለው። በምላሹም መቀመጫውን ዳርፉር ደያረገ መንግሥት ለማወጅ ያለመ አብዮታዊ ኃይል መሆኑን አስታውቋል።
የሱዳን የጦር ኃይሎች ደግሞ ጦርነቱን ከ"አሸባሪ ሚሊሻ" ጋር የሚካሄድ አመፅ በማለት የኅልውና ትግል እንደሆነ እየገለጸው ይገኛል።
"ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለያዛቸው ግዛቶች ዕውቅና በመስጠት የተኩስ አቁም ስምምነትን መቀበልን ጨምሮ፣ በማንኛውም መንገድ የኃይሉን ሕጋዊነት ለመቀበል ጠንካራ ተቃውሞ በሠራዊቱ ውስጥ አለ" ይላሉ በብሪታኒያ ቻተም ሐውስ የምርምር ማዕከል ውስጥ የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ የሆኑት አሕመድ ሶሊማን።
ሁለቱም ወገኖች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ዋነኛ የድጋፍ ማዕከል በሆነው በደቡብ እና በምዕራብ በሚገኙ አርብቶ አደር አረቦችን እና አገሪቱን የሚገዙት በከተሞች እና በግብርና አካባቢዎች የሚኖሩት በአባይ ሸለቆ አረቦች መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀውን የጎሳ ልዩነት እንደ መሣሪያ ተጠቅመዋል።
በዳርፉር የተፈጸመው ጎሳን መሠረት ያደረገ ጥቃት በክልሉ የነበረውን ተመሳሳይ ታሪክ መልሶ ቀስቅሶታል። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አረብ ሚሊሻዎች አረብ ያልሆኑ ሕዝቦችን በጭካኔ በመግደላቸው የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች ክስተቱን የዘር ማጥፋት "አመልካች" መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በጦርነቱ በውጤቱ ላይ ቀጥተኛ ድርሻ ያላቸው ወይም ጦርነቱን ተጽዕኗቸውን ለማስፋት በሚፈልጉ የውጭ ኃይሎች እየተቀጣጠለ ነው።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የጦር መሣሪያ እንደምታቀርብ በሰፊው የተረጋገጡ ማስረጃዎች ያሉ ቢሆንም ኤምሬትስ ግን ይህንን በይፋ ታስተባብላለች።
ተፋላሚው የሱዳን ጦር ኃይልም የቱርክ እና የኢራንን ድሮኖች ታጠቀ ሲሆን፣ ከግብፅ፣ ከኳታር እና ከሳዑዲ አረቢያ የፖለቲካ እና ሌሎች ድጋፎችንም ያገኛል።
የሰላም ፍኖተ ካርታ
ኳድ በመባል በሚጠሩት በዩናይትድ ስቴትስ፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና በግብፅ አማካይነት የሚደርጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ላይ ብዙዎች ተስፋ አላቸው።
ይህ መንገድ "ከተፋላሚ ወገኖች ይልቅ በቀጣናው ተዋናዮች መካከል ድርድር ማድረግ ነው" ይላሉ የቻታም ሐውስ ሶሊማን። ነገር ግን ስምምነት ላይ ለመድረስ በርካታ እንቅፋቶች አሉ።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በኳድ ቡድን የቀረበውን የሰላም ፍኖተ ካርታ ሰብአዊነት እርዳታ ለማቅረብ በሚደረስ ስምምነት ለመጀመር በቃል መቀበሉን ገልጿል፤ ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች በይፋ ምላሽ አልሰጡም። ውጊያው ግን ጋብ ከማለት ይልቅ ተባብሷል።
የጦር ኃይሉ አዛዥ አል ቡርሃን፣ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እጅ ከመስጠት ጋር የሚስተካከሉ ቅድመ ሁኔታዎችን እስካልተቀበለ ድረስ በዕቅዱ እንደማይስማሙ ተናግረዋል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በመደገፍ በምትከስሰው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውይይት ውስጥ መሳተፍን ጦሩ ይቃወማል።
በተጨማሪም የሰላም ፍኖተ ካርታው በሱዳን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ውስጥ ማንኛውም ዓይነት እስላማዊ ተጽዕኖን በግልጽ ውድቅ አድርጓል።
እንደ ሶሊማን ያሉ ተንታኞች እንደሚሉት ኤምሬቶች በእስላማዊ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ለሚሆን መንግሥት ያላቸውን ጥላቻ ግልጽ ስላደረጉ ሚናቸው ጎልቶ ይታያል። ይህንን ደግሞ በርካታ የሱዳን ፀረ-ጦርነት ሲቪሎች የሚጋሩት ስሜት ነው።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ለመደገፍ ምክንያት ከሆኗት ነገሮች መካከልም አንዱ ይኸው ጉዳይ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል።
የጦር ኃይሉ እያካሄደ ባለው ፍልሚያ ውስጥ እስላማዊ ሚሊሻዎች ወሳኝ ሚና አላቸው። ምንም እንኳን የእስልምና ተቋማት በአውሮፓውያኑ 2019 አብዮት ቢዳከሙም አሁንም ድረስ ግን ተጽዕኗቸው ፈጽሞ አልጠፋም።
ስለዚህም ይህ እስላማዊ ቡድኖችን ገለል የማድረጉ የስምምነቱ ውልን አል ቡርሐን ለመቀበል እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል።
የአሜሪካ አምባሳደር ማሳድ ቡሎስ የተሻሻለ ዕቅድ እንዳላቸው እና በቅርቡ በሰብአዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ላይ ለመድረስ "ጥንቃቄ የተሞላው ተስፋ" እንዳላቸው ተናግረዋል።
ጦር መሣሪያዎችን ማቆም
የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲጸና የቀጣናው ደጋፊዎች ተፋላሚ ወገኖቹን ማስታጠቅ እንዲያቆሙ ስምምነት መደረስ አለበት። ነገር ግን ይህንን ለማሳካት ቀላል አይሆንም።
"በግልጽ እንደሚታየው፣ ሁሉም ወደ አገሪቱ መሣሪያ በብዛት እያጋዘ ባለበት ሁኔታ የተኩስ አቁም ለማድረግ መሞከር ውጤት አያመጣም" ይላሉ የዓለም አቀፉ የክራይሲስ ግሩፕ የአፍሪካ ቀንድ ተንታኝ አለን ቦስዌል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ሚና በተመለከተ በይፋ የሚታየውን አሻሚነት መፍታት በሂደቱ ውስጥ አስቸጋሪው ፈተና ሆነወል።
የበረራ መረጃዎችን እና የሳተላይት ምሥሎችን የሚጠቅሱ በርካታ የምርመራ ሪፖርቶች ኤምሬቶች የጦር መሣሪያዎችን እና ቅጥረኛ ተዋጊዎችን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወደሚቆጣጠራቸው ቦታዎች በመላክ ተሳትፎ እንዳላት ዘግበዋል። የተባበሩት መንግሥታትም ማስረጃዎቹን ታማኝ ብሏቸዋል።
ነገር ግን አቡ ዳቢ ይህንን አጥብቃ ተቃውማለች። ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽም በየትኛውም መልኩ ድጋፍ እንደማያደርጉ እና ክሱ ፍጹም ሐሰት መሆኑን በመግለጽ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሱዳን ላይ ሙሉ በሙሉ የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እንዲጣል ጥሪ አቅርባለች። ነገር ግን የጦር ኃይሉ ደጋፊዎች ይህ ውሳኔ በአንድ ሚሊሻ እና በመንግሥት መካከል አቻነትን ይፈጥራል ብለው ይቃወሙታል ሲሉ ቦስዌል ተናግረዋል።
የኤምሬቶች ሚና ለከፍተኛ ትችት የተጋለጠው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ኤል-ፋሸርን ከ18 ወራት ከበባ በኋላ በተቆጣጠረበት ወቅት ተዋጊዎቹ ባልታጠቁ ሰዎች ላይ የፈጸሙትን የጅምላ ግድያ እየቀረጹ ካሳዩ በኋላ ሲሆን ወሲባዊ ጥቃት እና እስር መፈጸሙም በሰፊው ተዘግቧል።
"ኤምሬቶች ዓለም አቀፍ ዝናዋን እንዴት እንደምታስከብር በጣም ትጨነቃለች" ሲሉ የሬፊዩጂ ኢንተርናሽናል ፕሬዝዳንት ጄረሚ ኮኒንዲክ ተናግረዋል። "ስለዚህም አሜሪካ ይህንን ገጽታ ይፋ ልታወጣው ይገባል። እናም አሜሪካ ይህንን መቃወም አለባት።"
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮም ይህን ለማድረግ የተቃረቡ ይመስላሉ።
"በጦር መሣሪያ አቅርቦት ውስጥ የተሳተፉ ወገኖች እነማን እንደሆኑ እናውቃለን" ሲሉ በኅዳር ወር ላይ ተናግረዋል።
"ለዚህም ነው ከሌሎች አገሮች ጋር የኳድ አባል የሆኑት። በሚመለከታቸው ወገኖች ላይ ጫና እየተደረገ ነው" ብለዋል።
ነገር ግን ሩቢዮ ስም አልጠቀሱም። ተንታኞች እና የመብት ተሟጋች ቡድኖች የትራምፕ አስተዳደር ይህንን ያደርጋል ብለው አይጠብቁም።
"ለእነሱ መቆም በጣም ከባድ ነው" ይላሉ የሱዳኑ የፖለቲካ ተንታኝ ካይር። "አሜሪካ በዚህ ጦርነት ውስጥ በንቃት የሚሳተፉትን የውጭ ጓደኞቿን ስጋቶች እንዴት ማስወገድ እና ማስደሰት እንደምትችል ማወቅ አለባት፣ በተለይም ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን። እናም ይህን እንዴት ማድረግ እንዳለባት እስካሁን አላወቀችም።"
ሶሊማን እንደሚሉት፤ የአሜሪካ መንግሥት "ከሳውዲ አረቢያ እና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል መምረጥ ስለማይፈልግ ውርርዱን እየተከላከለ ነው። ይህ ደግሞ ከተሳታፊ አገራት ጋር ያለውን ሰፊ ግንኙነት ያበላሻል።"
የኃያላኑ የፉከክር መድረክ
የመፍትሄ ፍለጋው በአቅራቢያው ባሉ ኃይሎች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች የበለጠ አስቸጋሪ ሆኗል።
አንዳንድ ተንታኞች የሱዳንን ጦርነት ከአፍሪካ ዘመናዊ ትግል ጋር ያወዳድራሉ።
እና በቅርብ ወራት ውስጥ ሌሎች የኳድ አባላት በጦርነቱ ውስጥ የበለጠ በንቃት እየተሳተፉ በመሆናቸው፣ መሬት ላይ ያለው ገጽታ የበለጠ አስቸጋሪ ሆኗል።
ግብፅ ከሱዳን ጋር በደቡብ ምዕራብ ድንበር አቅራቢያ ካለ ሩቅ አየር ማረፊያ ኃይለኛ የቱርክ የጦር አውሮፕላን ሞዴል በመጠቀም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን የአቅርቦት ኮንቮዮች እና ሌሎች ዒላማዎች ላይ ቦምብ መጣሏን የኒውዮርክ ታይምስ እና የሮይተርስ የዜና ወኪል ምርመራ ይጠቁማል። ካይሮ ግን ምንም አስተያየት አልሰጠችም።
ጦርነቱ ወደ ግብፅ ድንበር ከተቃረበ በኋላ እየተባባሰ መጥቷል።
ሪያድ በአካባቢው ያለውን የኤሚሬቶች ተጽዕኖ ለማደናቀፍ ስትፈልግ፣ ከሳዑዲ አረቢያ ለሠራዊቱ የሚሰጠው ተጨማሪ ድጋፍ ተጽዕኖ አሳድሮበት ሊሆን ይችላል።
በሳውዲ አረቢያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ውጥረት የተፈጠረ ሲሆን፤ በታኅሣሥ ወር በየመን ግጭት ምክንያት በሁለቱ የባሕረ ሰላጤ ኃያላን መካከል ያለው ግንኙነት ተቋርጧል። ይህም በሱዳን ውስጥ የመፍትሄ ዕድል ላይ ስጋት ያስከትላል።
እንዴት ሰላም ማምጣት ይቻላል?
ሰላም ማምጣት የሚቻለው የግጭቱ ዋነኛ መንስኤ ላይ ሲደረስ ነው። ሁለቱም ወገኖች ለመዋጋት ሰበብ ያላቸው መሆኑ ለጦርነቱ መቀጠል ምክንያት ሆኗል።
የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ቢደረስ ለንጹኃን ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ ይረዳል። የሱዳን ጦርነት የዓለም የከፋው ሰብአዊ ቀውስ ተብሏል።
25 ሚሊዮን ሰዎች በአስቸኳይ የምግብ እጥረት የገጠማቸው ሲሆን፤ 12 ሚሊዮን ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
የተኩስ አቁም ዘላቂ ሰላም ወደማስፈን ሊያመራ እንደማይችል ተንታኞች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ቦስዌል "ሰብአዊ ተኩስ አቁም ውጤታማ ሲሆን አይታየኝም። ሁለቱም ወገኖች የኅልውና ስጋት ስላላቸው ውጊያ ለማቆም አይፈቅዱም። ለተኩስ አቁም ፈቃደኛ የሚሆኑት በቀጣይ ምን ይመጣል? የሚለው ጥያቄ ከተመለሰ ነው። ሁለቱም ወገኖች አይተማመኑም" ይላሉ።
ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጎን የቆሙ ጎሳዎች እንደ ኅልውና ዋስትና ይወስዱታል። በምጣኔ ሃብት ተጠቃሚ ለመሆን ወይም ለጥቅማ ጥቅሞች ተደራሽነት በቡድኑ ይተማመናሉ።
እስላማዊው ኃይልም በጦርነቱ ውስጥ የሚታየው ዕድል አለ።
ካሂር እንደሚያስረዱት ይህ ኃይል ወደ ሥልጣን መመለሱን ካላረጋገጠ የጦርነቱን ማክተም አይፈልግም።
ሌላው ጉዳይ ተጠያቂነት ነው። ሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊዎች እና ደጋፊዎቻቸው በጦር ወንጀሎች፣ በጎሳ ተኮር ግድያ እና በጅምላ ጭፍጨፋ ተከስሰዋል። ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ወታደራዊ አመራሮች ሊከሰሱም ይችላሉ።
ስለዚህም የፖለቲካ ድርድር ሲደረግ ተዋጊዎች ከጦርነቱ መገባደድ በኋላ ምን ይጠብቃቸዋል? የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ እና ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ መሆን አለበት።
ኳድ በሲቪሎች የሚመራ አስተዳደር ቢመሠርት የፀጥታ ኃይሎች የሚያገኙትን ገቢ ያጣሉ።
"ግጭቱ በዘላቂነት እንዲቆም ሱዳን ከወታደሮች ነጻ መሆን አለባት። ተደራሽነትን የሚያረጋግጥ አዲስ ሕገ መንግሥትም መርቀቅ አለበት። ይሄንን ደግሞ የሱዳን ተዋጊዎች አይፈልጉም" ሲሉ ካሂር ያስረዳሉ።
ድርድር ማካሄድ ቀጣይነት ያለው ትኩረት የሚሻ ነው። የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሙከራዎች ቢያደርግም፤ አሁን ላይ ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች አሉት።
ሶሊማን እንደሚሉት አሜሪካ በዘላቂነት ሰላም በማስፈን ሂደት ውስጥ አትሳተፍም። ሌላ አማራጭ የሚያቀርቡም አካላት የሉም።
ትልቁ ፍርሃት
ቢቢሲ በአውሮፓውያኑ 2024 ያነጋገራቸው የሱዳን መከላከያ ባለሥልጣን ጦርነቱ ምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ተጠይቀው፤ ጦርነቱን 20 ዓመታት ከዘለቀው እና አሜሪካ በአፍጋኒስታን ከታሊባን ጋር ካደረገችው ፍልሚያ ጋር አነጻጽረው ነበር።
ሱዳን ከዚህ ቀደም 20 ዓመታት የቆየ ጦርነት ገጥሟታል። የአሁኑ የተራዘመ ጦርነት አገሪቱን የመከፋፈል አደጋ ውስጥ ከቷታል።
ካሂር "ጦርነቱ ሦስተኛ ዓመቱ ነው። ለተጨማሪ 10፣ 15 ወይም 20 ዓመታት ሊቆይ እንደሚችል ታሪክ ምስክር ነው። ይህም የተከፋፈለች ሱዳንን ይፈጥራል" ሲሉ ያስረዳሉ።
የሱዳን ጦርነት ለቀጣናውም ስጋት ነው። ሰባቱ የሱዳን አጎራባች አገራት ተፈናቃዮችን እያስተናገዱ ይገኛሉ።
አንዳንዶቹ አጎራባች አገራት ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የጦር መሣሪያ በማድረስ ተከስሰዋል። ግጭቱ ድንበር ሊሻገር እንደሚችል እና ዓለም አቀፍ ቀውስ እንደሚያስከትልም ምልክቶች ታይተዋል።
ሱሌይማን እንደሚሉት፤ ሁለቱ ተዋጊዎች አደገኛ ፍጥጫ ውስጥ ሲገቡ ደጋፊዎቻቸው አቋማቸውን መልሰው ያጤኑ ይሆናል።
"የተከፋፈለች፣ ደኅንነቷ ያልተጠበቀ እና ያልተጋጋች ሱዳን አትጠቅማቸውም። በቀጣናው ያሉ የጦርነቱ ደጋፊዎች አንድ ላይ ሆነው በስምምነት የወደፊቱን መንገድ ይቀይሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሌላ አማራጭ አይታየኝም" ይላሉ።