ትራምፕ፤ ከኢራን ቀጥሎ "አጀንዳችን ናት" ባሏት ኩባ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በመላው ኩባ ለ24 ሰዓታት መብራት ሲጠፋ የመጀመሪያው አይደለም። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ቀጥሎ "አጀንዳቸው" ኩባ መሆኗን ተናግረዋል።

ከሰሞኑ በድጋሚ በአገሪቱ መብራት መጥፋቱን ተከትሎም ትራምፕ "ቀጣይ አጀንዳችን ኩባ ናት። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በአገሪቱ ለውጥ ይኖራል" ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከሊዮኔል ሜሲ፣ ሉዊስ ስዋሬዝ እና ሌሎችም የኢንተር ማያሚ ተጫዋቾች እንዲሁም ከኩባዊው የክለቡ ባለቤት ጆርጌ ማስ አጠገብ ቆመው "በቅርቡ በኩባ በሚሆነው ነገር ትደሰታላችሁ" ብለዋቸዋል።

ትራምፕ አክለውም የኩባ መንግሥት "በጣም ነው መደራደር የሚፈልገው" ሲሉ ተናግረዋል። የኢንተር ማያሚ ባለቤት "ታላቅ ቀን ይሆናል" ሲል ለትራምፕ ምላሽ ሰጥቷል።

ፕሬዝዳንቱ ከሲኤንኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ደግሞ "ኩባ በቅርቡ ትወድቃለች" ሲሉ ተደምጠዋል።

የኩባ መንግሥት እየተደራደረ መሆን ጠቅሰው "ማርኮ ሩቢዮን እንልከውና ምን እንደሚፈጠር እናያለን" ሲሉ ለሲኤንኤን ተናግረዋል።

"ኩባ ዝግጁ ናት፤ ከ50 ዓመታት በኋላ" ያሉት ትራምፕ፤ አሁን ትኩረታቸው ኢራን ብትሆንም እጃቸው ላይ "ብዙ ጊዜ" እንዳላቸው ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ ቀጣናዊ ፍላጎታቸውን እስከሚያሳኩ ድረስ ኩባ ላይ ጫና ማሳደር እንደሚፈልጉ ከንግግራቸው መረዳት ይቻላል። መቼ እንደሚያደርጉት ግን ግልጽ አይደለም።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማርኮ ሩቢዮ "ኩባ ይላካሉ" ማለታቸው ድርድር ሊኖር እንደሚችል ይጠቁማል።

ከኩባ ጋር ድርድር ሊካሄድ ይችላል ብሎ ማሰብ እንግዳ ነገር ቢሆንም በትራምፕ አሜሪካ ብዙ ያልተጠበቁ ነገሮች እየተከናወኑ ነው። ኒኮላስ ማዱሮ በኃይል ከሥልጣን ወርደው፣ ከቬንዙዌላ ወደ አሜሪካ መወሰዳቸው የቅርብ ጊዜ ማሳያ ነው።

አሜሪካ በቬንዙዌላ በወሰደችው እርምጃ ኩባም ተጎድታለች። ቬንዙዌላ የኩባ የቅርብ አጋር ናት። ኩባ ድፍድር ነዳጅ ትገዛ የነበረውም ከቬንዙዌላ ነበር።

ኩባ ከቬንዙዌላ ታገኝ የነበረውን ነዳጅ በዋነኛነት በሜክሲኮ መተካት ብትሻም የትራምፕ ጫና አላላውስ ብሏታል።

የነዳጅ እጥረት በደሴቲቷ አገር ላይ በግልጽ እየተስተዋለ መጥቷል። የከተማ መስተዳደር ቆሻሻ ሰብሳቢ ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ ስላልቻሉ በየቦታው ቆሻሻ ተከምሯል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ምሽት ላይ ቆሻሻ ማቃጠል የተለመደ ሆኗል። በዚህም ምክንያት ከተሞች በጭስ እየታፈኑ ነው።

ዋና ከተማዋ ሐቫናን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ለምግብ ማብሰያነት የሚውለው እንጨት ከሆነ ሰነባብቷል።

መብራት በየጊዜው ይጠፋል። ነዳጅ ባለመኖሩ ጄነሬተር መጠቀም አልተቻለም። ሌላ አማራጭ ኃይል አመንጪዎችም ያለ ነዳጅ አይሠሩም።

ትራምፕ እና ሩቢዮ እንደሚሉት ኩባ ላይ በተቻለው መጠን ሁሉ ተጽዕኖ መፍጠር ይቀጥላሉ። ኩባ ተዳክማ ወደ ድርድር ጠረጴዛው እንድትሄድ የሚያስገድዱበት መንገድ ነው።

የአሜሪካን አካሄድ የሚተቹ ተንታኞች እንደሚሉት ከኩባ መንግሥት ይልቅ በዋነኛነት ዋጋ እየከፈሉ ያሉት ንጹኃን ዜጎች ናቸው። አሜሪካ የምትፈልገውም ኩባውያንን ለአመጽ ማነሳሳት ይመስላል።

የኩባ መንግሥት ከአሜሪካ ጋር ድርድር እየተደረገ ነው የሚለውን በተመለከተ ማረጋገጫ አልሰጠም።

በሐቫና በኩል ተደራዳሪው የኩባ አብዮት ዘመን መሪ ራውል ጉየርሞ ሮድሪገዝ ካስትሮ እንደሆኑ ተሰምቷል።

የግሉ ዘርፍ ከውጭ አገራት ነዳጅ ማስገባት እንዲጀምር ፈቃድ ለመስጠት ውስን እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ነዳጅ ከውጭ ቢገባም ግን ያለውን ፍላጎት ለመሸፈን አይበቃም። እናም ኩባውያን ችግሩ ይቀረፋል ብለው አያምኑም።

የኩባ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ቱሪዝም ነበር። ነገር ግን አውሮፕላኖች በሐቫና ነዳጅ ስለማያገኙ ጉዞዎች ተስተጓጉለዋል።

ኤር ፍራንስን ጨምሮ ሌሎችም አየር መንገዶች ወደ ኩባ የሚያደርጉትን በረራ ሰርዘዋል።

የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ አገሪቱ ከፍተኛ ሙቀት በሚገጥማት ወቅት የበለጠ ፈታኝ ይሆናል። ንፋስ የሚሰጥ እና በኤሌክትሪክ የሚሠራ መሣሪያ (air-conditioning ወይም fans) አገልግሎት ካልሰጠ ችግሩ ይባባሳል።