ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አምነስቲ፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ሴቶችን "በወሲብ ባርነት" ይዘዋል እና "በቡድን ደፍረዋል" ሲል ከሰሰ
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት በሴቶች እና ሴት ልጆች ላይ "የወሲብ ባርነት" እንዲሁም "በቡድን መድፈርን" ጨምሮ የተለያዩ ወሲባዊ ጥቃቶችን ፈጽመዋል ሲል አዲስ ባወጣው ሪፖርት ከሰሰ።
የታጣቂ ቡድኑ አባላት በሴቶች ላይ የፈጸሟቸው ፆታዊ ጥቃቶች፣ ከፍርድ ውጪ የሆነ ግድያ እና የንጹኃንን ንብረት የማውደም ድርጊቶች "በጦር ወንጀልነት ሊፈረጁ የሚችሉ" እንደሆነ አስታውቋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ አርብ የካቲት27/2018 ዓ.ም. ይፋ የደረገው የምርመራ ሪፖርት፤ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱት የታጣቂ ቡድኑ አባላት ከአውሮፓውያኑ 2020 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት የፈጸሟቸውን ድርጊቶች የዳሰሰ ነው። ምርመራው የተደረገው በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ በሚገኙት ሳዮ እና አንፊሎ ወረዳዎች ውስጥ እንደሆነ ገልጿል።
የሰብአዊ መብቶች ተቋሙ ምርመራውን ሲያከናውን በቡድኑ አባላት ወሲባዊ ጥቃት ለተፈጸመባቸው 10 ሴቶች ቃለ መጠይቅ ማድረጉን እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን ማነጋገሩን እና የሕክምና መዝገቦችን መመርመሩን አስረድቷል። በምርመራው ከተካተቱ ሴቶች መካከል ሰባቱ ጥቃት በተፈጸመባቸው ወቅት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች እንደነበረም አክሏል።
በ2011 ዓ.ም. የተጀመረው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) እና የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች ግጭት "ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው በሲቪሉ ሕዝብ ላይ" እንደሆነ አምነስቲ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።
የድርጅቱ የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ፤ "ለሰባት ዓመታት ያህል ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያሉ ታጣቂዎች በኮሚዩኒኬሽን እና በመገናኛ ብዙኃን መገደብ ምክንያት በተፈጠረው የጨለማ ሽፋን [ስር ሆነው] ንጹኃንን ለከፍተኛ ስቃይ ዳርገዋል" ብለዋል።
የአምነስቲ ሪፖርት እንደሚያስረዳው፤ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው 10 ሴቶች መካከል አምስቱ "ለወሲብ ባርነት" ተዳርገው ነበር። ሪፖርቱ፤ "ዘጠኙ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፤ አንዷ ደግሞ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደርም እና በኦነሠ ታጣቂዎችም ጥቃት ደርሶባታል" ይላል።
በማሳያነት ተጠቀሰች አንዲት እናት እና በወቅቱ 12 ዓመቷ የነበረችው ልጇ ሦስት ሳምንት ለሚሆን ጊዜ ዋሻ ውስጥ እጃቸው ከዛፍ ጋር ታስሮ "በበርካታ የኦነሠ ወንዶች መደፈራቸውን" እንደተናገረች መግለጫው ላይ ሰፍሯል።
ወሲባዊ ጥቃት የተፈጸመባት እናት "ለሦስት ሳምንታት ያህል 15 ወንዶች እኔን እና ልጄን ይደፍሩን ነበር። ይፈራረቁብን ነበር" ማለቷን አምነስቲ በሪፖርቱ ገልጿል። በ2017 ዓ.ም. "በኦነሠ ተዋጊዎች በወሲብ ባርነት ተይዛ" የነበረች ሌላ ሴት የደረሰባት ሰቆቃም በሪፖርቱ ላይ በማሳያነት ተጠቅሷል።
እንደ አምነስቲ ገለጻ፤ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች "ባሎቻቸው፣ ወንድሞቻቸው ወይም አባቶቻቸው" የመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባል በመሆናቸው ምክንያት የታጣቂ ቡድኑ አባላት "በበቀል እንደደፈሯቸው" ተናግረዋል።
"ከፆታዊ ጥቃቱ በኋላ ቤታቸውን ለቅቀው እንዲሄዱ እንደተገደዱ" እንዲሁም ይህንን ያላደረጉት ቤታቸው እንደተቃጠለ ሪፖርቱ አመልክቷል። ሁለት ሴቶች ወንድ ዘመዶቻቸው በታጣቂዎቹ እንደተገደሉ ተናግረዋል ተብሏል።
ወሲባዊ ጥቃት እና ከባድ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል የተባሉት ሴቶች አሁንም ቢሆን "በኦነሠ ተዋጊዎች እና በባለሥልጣናት የበቀል እርምጃ እንደሚወሰድባቸው በመስጋት እና ከወሲባዊ ጥቃት ጋር ተያይዞ በሚመጣው መገለል የተነሳ" የሕክምና አገልግሎት እንዳላገኙ ተገልጿል።
የተቋሙ የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ፤ "እነዚህ ተደጋጋሚ በደሎች አሰቃቂ ብቻ አይደሉም፤ የጦር ወንጀል ሊሆኑ ይችላሉ" ብለዋል።
አምነስቲ የሰነዳቸው እነዚህ ግፎች የተፈጸሙት "ተጠያቂነት በሌለበት ከባቢ" ውስጥ እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ መንግሥት በአካባቢው የግንኙነት መስመሮችን ማቋረጡም ድርጊቶቹ እንዲፈጸሙ አስተዋጾ ማድረጉን ተናግረዋል።
"የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቀውስ ጊዜያት ሳንሱርን ተግባራዊ ወደ ማድረግ ሲመለሱ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ሙሉው ምሥል ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።
"በሲቪሎች፣ በተለይም በሴቶች እና በልጃገረዶች ላይ የሚፈጸመው የበደል አዙሪት ማብቃት አለበት" ያሉት ቻጉታህ፤ "ዓለም አቀፍ እና የአፍሪካ የመብት ተከታታዮች" ድምጻቸው እንዲያሰሙ ጠይቀዋል።
"የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ወንጀለኞች ተጠያቂ ማድረግ እንዲሁም ለተጎጂዎች እና የጥቃት ሰለባዎች ፍትሕ እንዲሁም መፍትሔ ማቅረብን ዓላማው ያደረገ አስቸኳይ፣ ገለልተኛ እና ጥልቅ ምርመራ እንዲያጀምሩ መጠየቅ አለባቸው" ብለዋል።
በምርመራው የተካተቱ ሴቶችም በሚፈጸሙት "ጥቃቶቹ እንዲቆሙ እንዲሁም ፍትሕ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን" እንደጠየቁ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
የሰብአዊ መብቶች ተቋሙ ሪጅናል ዳይሬክተር፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትም እንደ "ወሲባዊ ጥቃትን፣ ሌሎች የስቅይት ድርጊቶችን፣ ግድያን፣ የግዳጅ መፈናቀል" ያሉ ድርጊቶችን የፈጸሙ አባላቱ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል።
የታጣቂ ቡድኑ አመራሮች፤ እነዚህን እና "ሌሎች በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ወንጀል የሆኑ ተግባራትን የፈጸሙ ታጣቂዎችን እና/ወይም አሃዶችን ትጥቅ ማስፈታት እና ማሰናበት አለባቸው" ብለዋል።
ታጣቂዎቻቸው "ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግን እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግን እንዲያከብሩ በአስቸኳይ ትዕዛዝ እንዲሰጡም" አሳስበዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን የተመለከተው ይህ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ይፋ የሆነው፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ታጣቂ ቡድኑ በኦሮሚያ ክልል አርሶ ዞን "ቁጥራቸው በውል ያልተለዩ" ሰዎችን መግደሉን የሚገልጽ መግለጫ ባወጣ በቀናት ልዩነት ነው።
ኢሰመኮ ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ታጣቂ ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በፈጸመው ጥቃት "የሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ እገታ እንዲሁም መፈናቀል" መድረሱን እንዳረጋገጠ አስታውቆ ነበር።
ኢሰመኮ ይህንን ከማለቱ አስቀድሞ በአካባቢው የተፈጸመው ግድያ በተመለከተ መግለጫ ያወጣው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ግን "በአርሲ ዞን የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ለደረሰው እልቂት" ተጠያቂ ያደረገው በመንግሥት ተሰማርተዋል ያላቸውን "ተላላኪዎች" ነው።
ታጣቂ ቡድኑ በአምነስቲ ሪፖርት ስለቀረቡበት ውንጀላዎች እስካሁን ምላሽ አልሰጠም። ይሁን እንጂ የዜና ወኪሉ አሶሺዬትድ ፕሬስ ከአንድ ወር በፊት ባወጣው ዘገባ ላይ የቡድኑ መሪ የሆኑት ድሪባ ኩምሳ (ጃል መሮ)፤ የቡድኑ ተዋጊዎቸ ንጹኃንን ዒላማ ያደርጋሉ መባሉን ውድቅ አድርገው ነበር።
"ንጹኃንን የሚጎዳ ማንኛውንም ድርጊት በጽኑ እንቃወማለን፣ እናወግዛለንም" ያሉት የታጣቂ ቡድን መሪው፤ "ገለልተኛ በሆነ ዓለም አቀፍ አካል የሚደረግ ነፃ ምርመራን" እንደሚቀበሉም ተናግረው ነበር።