ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ500 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ብር የተጠየቀባቸው ተማሪዎች ከታገቱ ከ10 ቀናት በላይ ሆናቸው
ባለፈው ሳምንት ሰኔ 25/2016 ዓ.ም. ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ የታገቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከአስር ቀናት በላይ እንደሆናቸው ቤተሰቦች ተናገሩ።
ከ100 በላይ የሚሆኑትን የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ከእገታ ለማስለቀቅ በታጣቂዎቹ ከ500 ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንደተጠየቁ ሦስት ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከቀናት በፊት የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ መለቀቃቸውን ለአገር ውስጥ መገናና ብዙኃን አስታውቀው ነበር።
ታጋቾቹ የሚማሩበት የደባርቅ ዩኒቨርስቲ የወንጌላዊያን ክርስቲያን ተማሪዎች ኅብረት ተማሪዎቹ አሁንም በእገታ ስር እንደሆኑ ለቢቢሲ አረጋግጦ፤ የታጋቾቹ ቁጥርም 150 እንደሚሆን ገልጿል።
ይሁን እንጂ ቤተሰቦች አብዛኞቹ ተማሪዎች አሁንም በአጋቾች እጅ እንደሆኑ ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፤ አጋቾች በቶሎ የጠየቁትን ገንዘብ እንዲከፍሉ ተማሪዎቹ ላይ ጫና እያደረሱባቸው ነው ብለዋል።
ልጃቸው እንደታገተችባቸው የተናገሩ እና ለደኅንነቷ ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የተጠየቁ አባት መንግሥት ተማሪዎቹን ሳያስለቀቅ “የውሸት ዜና አሠራጭቷል” ሲሉ ወቅሰዋል።
የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወሰዱት በተባለ እርምጃ ‘ተማሪዎቹ ተለቀቁ’ የሚለውን ዜና ሲሰሙ እውነት መስሏቸው እንደነበር እና ሁኔታውን ለማረጋገጥ ስልክ ሲደውሉ ግን ትክክል አለመሆኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ “167 ተማሪዎች 160ዎቹ መለቀቃቸውን” እና ቀሪዎቹን ለማስለቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው ነበር።
“‘ልጆቹ አንድ ላይ ነው ያለነው፤ ሌላ ቡድንም እንደኛ እንዲሁ አለ እያሉ ነው።’ መንግሥት ሰባት ሰው ብቻ ቀርቷል ማለቱ ትክልል አይደለም” በማለት የወቀሱት ግለሰቡ፤ “ምን ዓይነት ጭንቀት እና ችግር ውስጥ እንዳለን ማንም አልተረዳልንም” ብለዋል።
የሌላ ታጋች ተማሪ ወላጅ ደግሞ “20 የሚሆኑ ተማሪዎች ወደ መከላከያ ካምፕ ገብተው ያመለጡ መሆናቸውን እንዲሁም አጋቾቹ በመታወቂያቸው እየለዩ ለቀዋል።”
ጨምረውም “ማስለቀቂያ ተንዘብ ተከፍሎ የተለቀቁ እና ከአጋቾቹ ጠፍተው የወጡ አሉ። መንግሥት እነዚህን ቆጥሮ በራሱ ኃይል 160ዎቹን አስለቀቅኩ እያለ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“የሚወራው ወሬ እና ያለው እውነታ ግን ሰማይ እና ምድር ነው” ያሉ የሌላ ተማሪ አባት ልጃቸውን ዛሬ [አርብ ሐምሌ 5/2015 ዓ.ም.] በስልክ እንዳገኟት እና ከሌሎች ብርካታ ጓደኞቿ ጋር በአጋቾቹ ቁጥጥር ስር መሆናቸውን ገልጻለች።
“በየቀኑ አገኛታለሁ” ሲሉ የስልክ ግንኙነታቸውን የተናገሩ ግለሰቡ፤ ታጋቾቹ በቡድን በቡድን ተከፋፍለው “ጫካ ውስጥ” እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ተማሪዋ ትናንት [ሐሙስ] በአጋቾች ስልክ ደውላ እንዳነጋገሯት የገለጹት የቤተሰብ አባሉ፤ ከሌሎች 44 ተማሪዎች ጋር አብራ መሆኗን ተረድተዋል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር የማስለቀቂያ ገንዘብ እንደተጠየቁም የተናገሩት ግለሰቡ፤ ቤተሰባቸው ገንዘቡን ለማሰባሰብ ጥረት ቢያደርግም ‘ተለቀዋል’ የመባሉ ዜና እንደ አጭበርባሪ እንድንታይ አደረገን ይላሉ።
“ሁሉም ተማሪዎች ተለቀዋል ተብሏል በማለት ለመርዳት የፈቀዱ ሰዎች ገንዘብ ከለከሉን። እኔ ራሴ በግሌ ከሰው እየለመንኩ እየወሰድኩ ነበር። ሰው ሁሉ ወጥተዋል ብሎ ዝም አለ” ሲሉ የማስለቀቂያ ገንዘብ ለማሰባሰብ እንቅፋት እንደገጠማቸው ተናግረዋል።
“ልጄን እናቷ ቅጠል ሸጣ ነው ያስተማረቻት” ሲሉ የተጠየቁትን 500 ሺ ብር የማስለቀቂያ ገንዘብ ለመክፈል አቅም እንደሌላቸው የተናገሩት አንድ የታጋች ቤተሰብ፤ “ድንኳን ጥለን የአካባቢውን ሰው እርዱን ብለን እያሰባሰብን ነው ያለነው” ብለዋል።
ሆኖም ግን እስካሁን ያሰባሰቡት ገንዘብ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
“አንድ ሚሊዮን [ብር] ክፈሉ፤ ካልከፈላችሁ ልጆቻችሁን አታገኙም [ብለውናልል]” ሲሉ ረቡዕ ዕለት የሦስተኛ ዓመት ተማሪ የሆነውን ታጋች ልጃቸውን በስልክ እንዳገኙ ሌላ የቤተሰብ አባል ተናግረዋል።
“ከ37 ተማሪ ጋር አብረን ነው ያለነው” ማለቱን የተናገሩት ግለሰቡ፤ ገንዘቡን ለመክፈል አቅም እንደሌላቸው ተናግረዋል።
“የልጃቸውን ሕይወት ለማዳን” ብለው የተጠየቀውን ገንዘብ ለማሰባሰብ ቢቢሲ ባናገራቸው ወቅት ፖስተሩን አሠርተው ቤተ ክርስቲያ እና ገበያ ላይ “ለመለመን” እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የታጋች ቤተሰቦች “እጃችን ላይ ያለችውን ገንዘብ እንኳ ልከን እባካችሁ ልጆቻንን ስጡን እያሉ ነው” ያሉት አንድ የወንጌላዊ ክርስቲያን ተማሪዎች ኅብረት አገልጋይ፤ ለማስለቀቂያ ይጠየቅ የነበረው ገንዘብ ጨምሯል ብለዋል።
እስካሁንም ሁለት ተማሪዎች ለማስለቀቂያ የተጠየቀውን ገንዘብ ለአጋቾች ከፍለው ስለመለቀቃቸው ከቤተሰብ መስማታቸውንም አገልጋዩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያናገራቸው የታጋች ቤተሰቦች እስካሁን የማስለቀቂያ ገንዘቡ ባለመከፈሉ ተማሪዎቹን እያስፈራሯቸው እና ጫና እያደረሱባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
እስከ አርብ [ዛሬ] ገንዘቡን እንድናስገባ ቀነ ገደብ ተሰጥቶናል ያሉ ሌላ ቤተሰብ፤ ተማሪዎቹን እያስፈራሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
“’[ምግብ] በቀን አንድ ጊዜ ይሰጣል፤ በሦስት ቀን [አንዴ] ባዶ እንጀራ በሚጥሚጣ ይሰጡናል’ [ብላለች]። . . . መናገር እንኳ አልቻለችም። ምክንያቱም ጉዳት አለ። ምግብ በሥርዓት አያገኙም፤ ውሃ አያገኙም። ወደ ሌላ ቦታ እየወሰዱ በጣም እያንከራተቷቸው ነው” ብለዋል።
“’ብር ያልከፈላችሁ ከባድ ስቃይ ውስጥ ነው የምናስገባችሁ፤ ከእንግዲህ መውጣት የሚባል ነገር የለም፤ አሁን ክረምት ነው ሂዱ ብንል እንኳ ለመውጣት አቅጣጫ የማታውቁበት ቦታ ነው የምንወስዳችሁ፤ ከእንግዲህ ምግብም አንሰጣችሁም’ ብለው፤ አሁን ራሱ ምግብ ተከልክለው፤ ልጆቹ ስቃይ ውስጥ ነው ያሉት” ሲሉ ሌላ ቤተሰብ ተናግረዋል።
ማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍለው የተለቀቁ ተማሪዎች እንዳሉ መስማታቸውን የተናገሩ አንድ የታጋች ወላጅ፤ ማክሰኞ ዕለት ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም. አንዲት የአዲስ አበባ ልጅ 400 ሺህ ከፍላ ወጣች ብለዋል።
“ከጭንቀት እና ለቅሶ ውጪ ምን እናደርጋለን። [ቤተሰብ] ባሉበት ቁጭ ብለው ያለቅሳሉ” ሲሉ የቤተሰባቸውን ሁኔታ ተናግረዋል።
ሌላ ቤተሰብ በበኩላቸው “. . . ወይም ሞታለች ብለን እርም አላወጣንም። በመሀል ትመጣለች እያልን፤ እናቷም እየተሰቃየች ተቸገርን። እናቷ በጣም ከባድ ሁኔታ ላይ ናት፤ እያጽናናት ነው። ድብርት ውስጥ ገብታለች። ምን እንደምናደርግ አናውቅም” ብለዋል።
ቤተሰቦች ገንዘቡ ቢገኝ እንኳ እንዴት እና በምን ሁኔታ ገዘንዘቡን እናደርሳለን የሚለውም እንዳስጨነቃቸው ተናግረዋል።
“አካውንት ይላካል እናንተ ሰብስቡ ነው የሚሉት” በማለት የተናገሩት ወላጅ ነገር ግን አጋቾች የባንክ ሂሳብ ቁጥር እንዳልሰጧቸው ገልጸዋል።
“ብሩንም ለመስጠት ደግሞ አካውንት የላቸውም። እኛ እንነግራችኋለን ተዘጋጁ ነው የሚሉት። በምን አካውንት ነው የምናስገባው ስንል አንድ ጊዜ...በአካል ትሰጣላችሁ” መባላቸውን ቢቢሲ ያናጋራቸው ወላጅ ተናግረዋል።
ስለ እገታው ይመለከታቸው ለተባሉ የክልል እና የፌደራል ተቋማት ማመልከታቸውን የተናገሩት ቤተሰቦች፤ ከመንግሥት በኩል ጠብ ያለ መፍትሄ አለመኖሩን እና ተስፋ መቁረጣቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ ለመገናኛ ብዙኃን ተማሪዎቹን መለቀቃቸውን ያሳወቀውን የኦሮሚያ ክልል መንግሥትን የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎትን፣ እገታው ተፈጽሞበታል የተባለውን አካባቢ ባለሥልጣናትን፣ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤትን እንዲሁም ትምህርት ሚኒስቴርን ለማናገር ያደረገው ጥረት ስልክ ባለማንሳታቸው አልተሳካም።
እገታውን በመንግሥት ‘ሸኔ’ የሚባለው እና በአሸባሪነት የተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንደፈጸመው የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ ታጋቾች መለቀቃቸውን ባሳወቁበት ጊዜ ገልጸው ነበር።
ይሁን እንጂ ከእገታው ከቀናት በኋላ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ባወጣው መግለጫ በእገታው ውስጥ እጁ እንደሌለበት በመግለጽ መንግሥትን ተጠያቂ አድርጓል።
ቡድኑ የመንግሥት የፀጥታ መዋቅር መዳከሙን በመጠቀም ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ሰዎችን ያግታሉ በማለት “የመንግሥት ኃይሎች፣ የአካባቢ ካድሬዎች እና ሥራ አጥ ወጣቶች” እገታውን ፈጽመው ሊሆን ይችላል” በማለት እራሱን ከድርጊቱ አርቋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚንቀሳቀስባቸው የክልሉ አካባቢዎች ውስጥ ባለፉት ዓመታት ተደጋጋሚ እገታዎች ሲፈጸሙ የቆየ ሲሆን፣ አሁን በርካታ ተማሪዎች በታገቱበት የሰሜን ሸዋም እገታው ሲደጋገም መቆየቱ ይታወቃል።