ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባለፈው ሳምንት የታገቱ ተማሪዎች አብዛኞቹ ተለቀዋል ቢባልም ቤተሰቦች አሁንም የማስለቀቂያ ገንዘብ እየተጠየቅን ነው አሉ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ባለፈው ሳምንት በታጣቂዎች የታገቱ አብዛኞቹ ተማሪዎች መለቀቃቸውን ቢገልጹም የታጋች ቤተሰቦች ግን ተማሪዎቹ አሁንም ታግተው እንዳሉ ተናገሩ።
ከአማራ ክልል ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በሦስት በአውቶብሶች ሲጓዙ የነበሩ ከ100 የሚበልጡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሰኔ 25/2016 ዓ.ም. ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ውስጥ በታጣቂዎች መታገታቸው ይታወሳል።
ታጋቾቹ አብዛኞቹ የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መሆናቸው የታወቀ ሲሆን፤ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ አካባቢ “ሸኔ” በተባሉ ታጣቂዎች መታገታቸውን ከእገታው ያመለጡ ተማሪዎች እና የታጋች ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከቀናት እገታ በኋላ የፀጥታ ኃይሎች ወሰዱት በተባለ እርምጃ 138 ታጋቾች መለቀቃቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአካባቢው ባለሥልጣናት መስማቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።
18 ተማሪዎች ብቻ አሁንም በእገታ ላይ እንዳሉ የገለጸው ኮሚሽኑ፣ ታጋቾቹ መቼ እንደተለቀቁ ገና እያጣራ መሆኑን ተአመልክቷል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የታጋች ቤተሰቦች ግን ዜናው እንግዳ እንደሆነባቸው ገልጸው፤ የታገቱባቸውን ልጆቻቸውን ለማስለቀቅ ገንዘብ እያሰባሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።
አንድ የታጋች ቤተሰብ “ተማሪዎቹ ሁሉም ተይዞ ነው ያሉት፤ ማንም የተለቀቀ የለም” ሲሉ የአካባቢው ባለሥልጣናት የሰጡትን መረጃ የሚቃረን ሃሳብ ሰንዝረዋል።
በእገታው ስር ካሉ ተማሪዎች መካከል አንድ የቅርብ ቤተሰባቸው እንደሚገኙ የገለጹ አንድ ግለሰብ ዛሬ ረቡዕ ጠዋት (ሐምሌ 3/2016) በአጋቾች ስልክ ተደውሎላቸው ከታገቱት መካከል ማናገራቸውን ጠቅሰው፤ ከ100 በላይ ከሚሆኑ ተማሪዎች ጋር እንደሚገኙ መረዳታቸውን ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ ከእገታው ቀን ጀምሮ ታጋቾችን በቡድን ለይተው እንዲጓዙ ካደረጉ በኋላ ሰኞ ዕለት ወዳልታወቀ አካባቢ ስለመድረሳቸው ገልጸዋል።
“ሁሉም ተሰባስቦ፤ ከ100 በላይ ተማሪዎች አንድ ላይ ነው ያለነው፤ ሁላችንም አንድ ላይ ነን ተብሎ ተነግሮኛል” ያሉት የታጋች ቤተሰብ፤ “ምንም መፍትሄ እየመጣ አይደለም” ሲሉ በመንግሥት ላይ እምነት ማጣታቸውን ተናግረዋል።
“ከእነርሱ [ከታጣቂዎች] ጋር ሰላም ፈጥረን፤ ብር ከፍለን የሚሰጡን ከሆነ ማስወጣት ነው። መንግሥት ምንም ነገር እያደረገ ስላልሆነ የመንግሥትን ነገር ትተናል” ሲሉ ቅሬታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
እኚሁ ወላጅ ለመንግሥት ስለታገቱት ተማሪዎች መረጃ ማድረሳቸውን የገለጹም ሲሆን፤ የተጠየቀውን ማስለቀቂያ ገንዘብ ከፍሎ ከማስለቀቅ ውጪ ተስፋ የሚሰጥ ነገር የለም ብለዋል።
“ብዙ መረጃ ተሰብስቧል፤ ብዙ ነገር ተጠይቀን አናግረናል፤ አልቅሰናል፤ ጮኸናል። ለልጆቹ መብት የደረሰ ማንም የለም። ስለዚህ እኛ ብር ከየትም ከየትም ብለን የምናገኝ ከሆነ፤ ከእነሱ ጋር አልቅሰንም ይሁን ለምነናቸው ልጆቻችንን ማስመለስ ነው የምንፈልገው። ምንም መፍትሄ ስለሌለ ተስፋ ቆርጠናል” ብለዋል።
“ቤተሰቦቻችሁ ላይ ደውሉና [ብር] ያስገቡ እያሉ እያስፈራሯቸው ነው፤ እስካሁን ድረስ እዚያ ነው ያሉት” ያሉት ሌላ ወላጅ፤ የልጃቸው ሕይወት አደጋ ላይ እንዳለ ተናግረዋል።
“[ታጣቂዎች] ‘ዛሬ የመጨረሻ ቀን ነው፤ ብዙ ደክማችሁ በኋላ ትሞታላችሁ’ [እያሏቸው ነው]። በፊት ደረቅ ዳቦ ይሰጡ [ነበር]፤ አሁን እሱን ራሱ አንሰጣችሁም እያሉ [ነው]። አንድ ነገር ያደርጉናል ብለው እኛ ራሱ በስጋት ላይ ስላስቀመጡን፤ ገበያ ውስጥ ጨርቅ ዘርግተን እየለመንን ነው” ሲሉ ቢቢሲ ሲያናጋግራቸው ወላጅ ገንዘብ ለማሰባሰብ ገበያ መውጣታቸውን ተናግረዋል።
ከልጃቸው ትናንት ማክሰኞ (ሐምሌ 2) ተደውሎ እንዳናገሩ የገለጹ ሲሆን፤ ከሌሎች 35 ታጋቾች ጋር በአንድ ላይ እንደሚገኙ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
“ከዚህ ሰዓት በኋላ አጋቾቹ ምን እንደሚያደርጉ አላወቅንም” የሚሉት የታጋች አባት፤ የልጃቸውን ስልክ በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ ተናግረዋል።
የታጋች ቤተሰቦች ይህን ቢሉም የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ግን “የፀጥታ ኃይሎች” በወሰዱት እርምጃ 160 ተማሪዎች ተለቀዋል ብሏል።
የክልሉ የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ከታገቱት 167 ተማሪዎች ውስጥ ሰባት ተማሪዎች ብቻ አለመለቀቃቸውን ለአሻም ለተባለው የአገር ውስጥ ቴሌቪዢን ዛሬ ሐምሌ 3/2016 ዓ.ም. መናገራቸው ተዘግቧል።
ከአዲስ አበባ በስተ ሰሜን 155 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከተፈጸመው እገታ የተወሰኑ ተማሪዎች ሲያመልጡ ሌሎች ደግሞ “የመጡበት አካባቢ ተለይቶ” መለቀቃቸውን ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።
አብዛኞቹ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎቹች የሆኑት በሦስት የሕዝብ ትራንስፖርት አውቶብሶች ሲጓዙ የነበሩ ታጋቾች መነሻቸው ከአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ እና ከባሕር ዳር ነበረ።
ሰዎችን በማገት ገንዘብ መቀበል እየተደጋገመ ያለ ክስተት ሲሆን፣ ከዚሁ ወንጀል ጋር በተያያዘ ስሙ እየተነሳ ያለው መንግሥት በሽብርተኝነት ፈርጆ 'ሸኔ' የሚለው ታጣቂው ቡድን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ግን አስካሁን ስለእገታው ያለው ነገር የለም።
* በዚህ ዜና ውስጥ ቢቢሲ ያናገራችው የታጋች ቤተሰቦች ለታጋቾቹ እና ለራሳቸው ደኅንነት ሲሉ ስማቸው እንዳይገለጽ ጠይቀዋል። ቢቢሲም ታጋቾችን እና ቤተሰባቸውን የሚያመለክቱ አገላለጾችን እንዲቀሩ አድርጓል።