ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የህወሓት አመራር "ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት" እያደረገ ነው አሉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ የህወሓት አመራር "ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት"፣ "የጦር መሣሪያ ግዥ" እና "ወታደራዊ ቅስቀሳዎችን እያደረገ ነው" ሲሉ በትግርኛ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ከሰሱ።
በፌደራል መንግሥት በኩል "በጭራሽ ትግራይ ላይ የሚጀመር ጦርነት እንደሌለ" አረጋግጣለሁ ሲሉም ተናግረዋል።
ትናንት ማክሰኞ የካቲት 24/2018 ዓ. ም. ምሽት ላይ የተላለፈው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቃለ መጠይቅ በአብዛኛው ያተኮረው ከትግራይ ክልል እና ከኤርትራ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ነው።
ዐቢይ፤ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ከነበራቸው የ40 ደቂቃ ገደማ ቆይታ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ጊዜ የወሰደው ስለ ትግራይ ጦርነት እና ስለ ፕሪቶሪያ ስምምነት ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጠው ምላሽ ነው።
የፌደራል መንግሥት በፕሪቶሪያው ስምምነት የተጣሉበትን ግዴታዎች "እንደፈጸመ" የገለጹት ዐቢይ፤ "አሁን ችግር ሆኖ ያለው ከወልቃይት አካባቢ የተፈናቀሉትን [ነዋሪዎች] የሚመለከት ነው" ብለዋል።
"ይህ ደግሞ ግትር አቋም ባለው ቆሞ ቀሩ ኃይል ምክንያት አልተሳካም" ሲሉ በህወሓት ውስጥ ይገኛል ያሉትን ቡድን ተጠያቂ አድርገዋል። "ብዙ ጊዜ ተነጋግረናል አሁንም እምነታችን ምን እንደሆነ ሕዝባችን ያውቀዋል። ነገር ግን በቆሞ ቀሩ ግትር አቋም ምክንያት ያሰብነው ሊሳካ አልቻለም" ሲሉም ተናግረዋል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት ውስጥ "ትልቁ የቤት ሥራ" ብለው የሚወስዱት "ከወልቃይት የተፈናቀሉ" ነዋሪዎችን ጉዳይ እንደሆነ ያነሱት ዐቢይ፤ "ተፈናቃዮች የግድ ወደ ቦታቸው መመለስ አለባቸው" ሲሉ ተደምጠዋል።
የሁለት ዓመቱን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት "በሙሉነት እንዳይፈጸም" ምክንያት ከሆኑ አንዱ "ህወሓት ሕገ መንግሥቱንና ተቋማትን ባለማክበር ወደ ጎን" መተዉ እንደሆነም በማንሳት ወቅሰዋል። "የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ሕግ አልተቀበለም" ሲሉም ላቀረቡት ክስ ማሳያ ጠቅሰዋል።
"ሁሉም ወገኖች" ተግባራቸውን ካከናወኑ "አብዛኛው ችግር ይፈታል" የሚል ዕምነት እንዳላቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን የህወሓት አመራሮች "ለጦርነት እየተዘጋጁ ነው" ሲሉ ከስሰዋል። "ቆሞ ቀሩ ቡድን በሰፊው ወታደራዊ ዝግጅት ላይ ይገኛል። በጣም የሚገርመው ደግሞ በግልጽ ፀረ ኢትዮጵያ ከሆኑ ኃይሎች ጋር መሰለፉ ነው" ብለዋል።
እንደ ዐቢይ ገለጻ፤ ቡድኑ "ተስፋውን ወደ ውጭ ኃይሎች" ያደረገው "በአባላቱ ላይና በሕዝቡ ላይ የነበረው ተስፋ እየተዳከመ" በመምጣቱ ነው። "የትግራይ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ፣ ታጣቂዎችንም ጨምሮ እምቢ ለጦርነት ሲል እያየን ነው" በማለት ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ቡድኑ፤ "ባለችው አቅም ወታደራዊ ቅስቀሳዎችን እያደረገ ነው" ያሉት ዐቢይ፤ "የትግራይ ወርቅ እና ሌሎች ማዕድናትን እየበዘበዘ ለጦር መሣሪያ ግዥ እያዋለው ነው" ሲሉ ወንጅለዋል።
ዐቢይ፤ ህወሓት "የጦርነት ቅስቀሳውን" እያከናወነ ያለው "ከምርጫ ቦርድ ተሰረዝኩ፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አልተመለሱም" የሚል ምክንያቶች በመጥቀስ እንደሆነ ተናግረዋል። እነዚህ ችግሮችንም "ራሱ የፈጠራቸው" ሲሉ ጠርተዋል።
"የእኔ አቋም ከቃላት አልፎ ወደ ወታደራዊ ትንኮሳ ከገባ ግን 'እንደ ቀድሞ መስሎሽ ጎርፉ ይወስድሻል' ብቻ ነው ማለት የምችለው" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
አክለውም፤ "በበኩላችን በፍጹም በጭራሽ ትግራይ ላይ የሚጀመር ጦርነት እንደሌለ ለማረጋገጥ እና ለመግለጽ እወዳለሁ። በትግራይ ዳግም ውጊያ የመጀመር ፍላጎት እና ሐሳብ እንደሌለን ሕዝባችን ማወቅ አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን የህወሓት ቡድን "ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት" እያደረገ ነው የሚል ክስ ያቀረቡት በፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ውጥረት ወደ ለየለት ግጭት ይገባል የሚል ስጋት ባየለበት ወቅት ነው። ሁለቱ ኃይሎች ባለፈው ጥር ላይ ትግራይ ክልልን ከአማራ እና አፋር ክልሎች ጋር በሚያዋስኑ ሥፍራዎች ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር።
ከትግራይ ጦርነት በኋላ በአማራ ክልል ሥር እየተዳደሩ ያሉት አወዛጋቢ ሥፍራዎች ከትግራይ ክልል ውጪ ሆነው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድ ባለፈው ሳምንት የተላለፈው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ደግሞ ውጥረቱ ይበልጥ እንዲካረር ምክንያት ሆኗል።
ህወሓት ይህንን ወሳኔ በመቃወም ባወጣው መግለጫ፤ በክልሉ ላይ "ከባድ ወታደራዊ ከበባ" እንዲሁም "መሠረታዊ ፍላጎቶች እና አገልግሎቶች ክልከላ" እንደተፈጸመ ገልጾ ነበር።
ዐቢይ፤ በትናንቱ ቃለ ምልልሳቸው የፌደራል መንግሥት ወደ ትግራይ "በጀት እየላከ" መሆኑን ቢጠቅሱም፤ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከጥቅምት አንስቶ የድጎማ በጀት እንዲሁም የነዳጅ አቅርቦት መቋረጡን እየገለጸ ይገኛል።
ጥር ላይ በፌደራል እና ትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት በተፈጠረበት ወቅት ወደ ትግራይ ክልል የሚደረገው የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ለአምስት ቀናት ተቋርጦ ቆይቷል። በክልሉ የሚገኙ ባንኮችም ደንበኞቻቸው በአንድ ቀን ውስጥ ማውጣት የሚችሉትን የገንዘብ መጠን ወደ ሁለት ሺህ ብር እንዳወረዱ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች ዳግም ሊነሳ የሚችል ጦርነትን ሽሽት ወደ አዲስ አበባ እየተጓዙ እንደሆነም ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የህወሓት አመራርን የጦርነት ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ በመግለጽ የከሰሱት ዐቢይ በበኩላቸው፤ ቡድኑ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚያመለክት ገለጻ በትናንቱ ቃለ መጠይቅ ሰጥተዋል።
ከኤርትራ መንግሥት "ጥሩ ነገር ማግኘት የማይታሰብ ነው። ስለሆነም አቅም ካገኘ አገርን ከመበጥበጥ ወደ ኋላ አይልም" ሲሉ ከስሰዋል።
ይሁን እንጂ አሳምረን ስለምናውቀው ዳግም ሕዝባችንን እንዲበድል ዕድል አንሰጠውም። ምናልባት ከሞከረ ደግሞ የመጨረሻ ሙከራ ነው የሚሆነው ብዬ ነው የማምነው" ሲሉ ማስጠንቀቂያ አዘል ምላሽ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በአስመራ ላይ ይህንን ዓይነቱን ክስ በተደጋጋሚ ቢያቀርብም ኤርትራ ውንጀላውን ውድቅ አድርጋለች። በምላሹም የኢትዮጵያ መንግሥት "በሉዓላዊ ባሕር በር" ስም "የጦርነት ትንኮሳ" እየፈጸመ መሆኑን በማንሳትም ክስ ታቀርባለች።