የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌደራል ኃይሎች ጋር የተካሄደው ግጭት "ሊፈጠር የማይገባ ነበር" አለ

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰሞኑ በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተካሄደው ግጭት "ሊፈጠር የማይገባ ነበር" አለ። "በግጭቱ ምክንያት" የተቋረጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ዳግም እንዲጀመር ለፌደራል መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡንም አስታውቋል።

በሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይህንን ያለው ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ እሁድ ጥር 24/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው። የትግራይ ኃይሎች እና የአገር መከላከያ ሠራዊት ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ግጭት ውስጥ ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ያወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው ግጭቱ የተቀሰቀሰው በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በሚገኙ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ነው። የትግራይ እና አማራ ክልሎች በሚወዛገቡበት ጸለምት በሚገኙት ማይ-ዳጉሻ፣ ማንጫራ እና ሌሎች ስፍራዎች በከባድ መሳሪያ የታጀበ ውጊያ መታየቱን ሪፖርቶች አመልክተዋል።

አርብ ሌሊት እና ቅዳሜ ንጋት ላይ ደግሞ በማዕከላዊ ትግራይ ዞን በሚገኙ ሁለት ከተሞች እና አንድ ወረዳ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል፤ አንድ ሰው ደግሞ እንደቆሰለ የክልሉ መንግሥት አስታውቋል። እስካሁን ድረስ ግጭቱን በተመለከተ ከፌደራል መንግሥት በኩል በይፋ የተባለ ነገር የለም።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ እሁድ ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ አዲሱ ግጭት "የትግራይ ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ ባለማግኘቱ ምክንያት የተከሰተ" እንደሆነ ገልጿል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ "ዘላቂ መፍትሄ" በሚል የጠቀሰው የተፈናቃዮች እና የትግራይ ክልል ወሰን መከበር ጉዳይን ነው።

"በትግራይ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው ተፈናቃይ ወገኖች ዋስትናቸው ተጠብቆ ወደ ቀያቸው ሲመለሱ እና የትግራይ ሕገ-መንግሥታዊ ወሰን ሲከበር መሆኑን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ያምናል" ብሏል።

እነዚህ ጉዳዮች "መሠረታዊ እና ብቸኛ" ጥያቄዎች መሆናቸውን የገለጸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ "የድንገተኛ ግጭቶች መነሻ" ሊሆን እንደሚችሉም በመግለጫው አስፍሯል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ እነዚህ ጥያቄዎች "በሰላማዊ እና በፖለቲካዊ መንገድ መፈታት እንደሚችሉ እና [ሊፈቱ] እንደሚገባ በጽኑ" እንደሚያምንም አስታውቋል።

"ከዚህ ውጪ ያለው መንገድ ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ሊያረጋግጥ እንደማይችል" በመግለጫው የጠቀሰው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ ካለፈው ሳምንት አንስቶ የተቀሰቀሰው ግጭትም "መሠረታዊው የትግራይ ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ ባለማግኘቱ ምክንያት የተከሰተ እና ሊፈጠር የማይገባው ነበር" ብሏል።

ሰሞነኛው ግጭት በትክክል በምን ምክንያት እንደተነሳ እስካሁን ግልጽ አይደለም። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ቅዳሜ ምሽት በትግራይ ቴሌቪዥን በተላለፈ ቃለ መጠይቅ ላይ ግጭቱ የተነሳው የትግራይ ኃይሎች ወደ ጸለምት አካባቢ ለመግባት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት እንደሆነ ተናግረዋል።

"ወደ ላይኛው ጸለምቲ እና በትንሹም ወደ ታችኛው ፀለምቲ 'ማኑቨር' ለማድረግ የተወሰነ ኃይል እንዲሻገር ተወስኗል" ሲሉ የታጣቂዎቹ እንቅስቃሴ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውሳኔ የተከናወነ እንደሆነ ጠቁመዋል። እንደ ታደሰ ገለጻ እዚህ ውሳኔ የተደረሰበት አንድ ምክንያት ከተፈናቃዮች አለመመለስ ጋር የሚገናኝ እንደሆነም ገልጸዋል።

"ተፈናቃዮችን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ጊዜያዊ አስተዳደሩን የማግለል ሁኔታ" እንዳለ በማንሳት የወቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ "የመመለስ ዕቅዱ አፈጻጸም ሙሉ በሙሉ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ወደ ጎን በመተው እየተንቀሳቀሰ ነው፤ ይህ እንዲስተካከል ስንጠይቅ ቆይተናል" ብለዋል።

ጸለምት አካባቢ "ሊፈርስ የሚገባው ሕገ-ወጥ አስተዳደር እየተጠናከረ" በመሄዱ ምክንያት ተደቅፏል ያሉትን "የማንነት አደጋም" በምክንያትነት ጠቅሰዋል። በአካባቢው ያለው "የትምህርት ሥርዓት ተቀይሮ" ተማሪዎች "በአማርኛ ቋንቋ እንዲማሩ ተገድደዋል" ሲሉም አክለዋል።

የትግራይ ኃይሎች በጸለምት አካባቢ እንዲቀሳቀሱ የተደረገው ይህ ጉዳይ "ዳግም አጀንዳ ሆኖ እንዲነሳ ለማድረግ እንጂ የውጊያ እንቅስቃሴ አልነበረም" ሲሉም እርምጃውን ተከላክለዋል።

ይህ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ጊዜ ግን "ያልታሰበ ግጭት አጋጥሟል" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ "ወደ ሙሉ ጦርነት [የገባ] የሚመስል የድሮን ጥቃት መፈጸሙን" በማንሳትም የፌደራል መንግሥትን ወቅሰዋል።

"ከሰሞኑ እየተፈጸመ ያለው የድሮን ጥቃት እና ወደ ሙሉ ጦርነት ለመሸጋገር የሚደረጉ ዝግጅቶች ተገቢ አይደሉም" ሲሉም ተችተዋል።

በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ግጭት መነሳቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ክልሉ የሚያደርጋቸው በረራዎች ከሐሙስ ዕለት አንስቶ ተቋርጠዋል። አምስት ቀናትን ያስቆጠረው የበረራ መቋረጥ ዛሬ ሰኞም መቀጠሉን ቢቢሲ አረጋግጧል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰም ይህ የበረራ መቋረጥ ወደ አዲስ አበባ ሊያደርጉት የነበረን ጉዞ ማስተጓጎሉን በቃለ መጠይቁ ገልጸዋል።

ሰሞነኛውን ግጭት እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ "ከፌደራል መንግሥት ጋር ለመወያየት" ቀጠሮ እንደነበራቸው የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በረራው በመቋረጡ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ መጓዝ እንዳልቻሉ አስረድተዋል። በረራው የሚመለስ ከሆነ "ውይይቱን ለማድረግ እንደሚጓዙም" ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንት ታደሰ "ልዩነቶቻችንን እያጠበብን ያለውን ችግር መፍታት አለብን። ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት የለንም። ጥያቄዎቻችንን በፕሪቶሪያ ስምምነት በኩል እንፈታቸዋለን" ሲሉም በቃለ መጠይቁ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደርም ባወጣው መግለጫ፤ "አሁንም በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ እና ዘላቂ መፍትሄን እውን ለማድረግ ቁርጠኛ" መሆኑን አረጋግጧል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ "ተፈናቃዮችን የመመለስና የትግራይን ሕገ መንግሥታዊ ወሰን የማስከበር ጉዳይ፣ እንዲሁም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በሰላማዊ እና በፖለቲካዊ መንገድ ለመታገል ያለበትን ግዴታ እንደሚወጣ" ገልጿል።

ከተቋረጠ ዛሬ አምስተኛ ቀኑን የያዘው ወደ ክልሉ የሚደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ በድጋሚ እንዲጀመር ለፌደራል መንግሥት ጥያቄ መቅረቡን አስታውቋል።

"ሕዝቡ በፋይናንስ ሥርዓቱ አምኖ ያስቀመጠውን ገንዘብ በባንኮች ካለው የጥሬ ገንዘብ እጥረት የተነሳ የተፈጠረው ችግር እንዲፈታም" መጠየቁን ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው ጠቅሷል።

"እንዲሁም ወር ከወር ለመሻገር የሚቸገረው የመንግሥት ሠራተኛ መደበኛ ደሞዙን በወቅቱ የሚያገኝበት ሁኔታ እንዲመቻች የፌዴራል መንግሥቱን ጠይቆ አዎንታዊ ምላሽ እየጠበቀ ይገኛል" ብሏል።