በትግራይ፣ አማራ እና አፋር አዋሳኝ አካባቢዎች ግጭቶች መካሄዳቸውን ኢሰመኮ አረጋገጠ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ካለፈው ሳምንት እሁድ ዕለት ጀምሮ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች መካከል በሚገኙ "አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች" ግጭቶች መቀስቀሳቸውን ገለጸ። በተለይም በጸለምት፣ መጋሌ እና አብአላ አካባቢዎች የተነሱት ግጭቶች "የሰዎችን የሕይወት እና የአካል ደኅንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ" እንደሆኑ አስታውቋል።

መንግሥታዊው የሰብአዊ መብቶች ተቋም ኢሰመኮ፤ እስካሁን ከፌደራልም ይሁን ከትግራይ ክልል አካላት ይፋዊ ማረጋገጫ ሳይሰጥበት የቆየውን ሰሞነኛ ግጭት የተመለከተ መግለጫ ያወጣው ትናንት አርብ ጥር 22/2018 ዓ.ም. ምሽት ነው።

የኢሰመኮ መግለጫ እንደሚያስረዳው ሦስቱን ክልሎች በሚያዋስኑት ሥፍራዎች ግጭት የተነሳው ከእሑድ ጥር 17 ቀን ጀምሮ ነው። መግለጫው ግጭት ተካሂዶበታል በሚል የጠቀሰው አንዱ ሥፍራ የትግራይ እና አማራ ክልሎች የሚወዛገቡበት ጸለምት ነው።

የዜና ወኪሎቹ ሮይተርስ እና ኤጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) የደኅንነት እና የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ዋቢ አድርገው ባወጧቸው ዘገባዎች፤ በዚህ ሥፍራ ላይ የትግራይ ኃይሎች "ከኢትዮጵያ ሠራዊት እና ከአማራ ሚሊሻዎች" ጋር ውጊያ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

በኢሰመኮ መግለጫ ላይ ትግራይ እና አፋር ክልሎችን በሚያዋስኑ ሥፍራዎች የሚገኙት መጋሌ እና አብአላ አካባቢዎችም ተጠቅሰዋል። በዚህን ሳምንትም ግጭት እንደተካሄደበት የተገለጸው አፋር ክልሉ መጋሌ ወረዳ ባለፈው ጥቅምት መጨረሻ ላይም ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ ነበር።

የክልሉ መንግሥት በወቅቱ ባወጣው መግለጫ "የህወሓት ቡድን" በወረዳው በምትገኘው ቶንሳ ቀበሌ ላይ "የከባድ መሣሪያ ተኩስ መክፈቱን" በመግለጽ ከስሶ ነበር።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪም "ጥቃት የከፈቱት" የትግራይ ኃይሎች "ወደ 15 ኪሎ ሜትር ዘልቀው" መግባታቸውን እና "ስድስት መንደሮችን" መቆጣጠራቸውን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። በዚህም ምክንያት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የቀበሌዋ ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉ ተገልጿል።

በእነዚህ "አዋሳኝ አካባቢዎች ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን እየተከታተለ" እንደሆነ የገለጸው ኢሰመኮ፤ "በተለይም በጸለምት/ጠለምት፣ በመጋሌ እና አብአላ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች" ስጋት መፍጠራቸውን አስታውቋል።

በሦስቱ "አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶችን ተከትሎ የሰዎችን የሕይወት፣ የአካል ደኅንነት፣ ነጻነት እና ንብረት መብቶች ስጋት ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን መረዳት ችሏል" ሲል የደረሰበትን በመግለጫው አስረድቷል።

በእነዚህ ሥፍራዎች "የተቀሰቀሰው ግጭት እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ" አማራ እና ትግራይ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው የራያ አካባቢዎች ነዋሪዎች ዘንድ "ወደ ጦርነት ሊሸጋገር ይችላል" የሚል ስጋት መፍጠሩን ገልጿል።

አላማጣ ከተማ እና ሌሎች የራያ አካባቢዎች "በኮማንድ ፖስት" ሥር እንደነበሩ ኢሰመኮ ገልጿል። ከትግራይ ጦርነት በኋላ በአማራ ክልል ሥር ሲተዳደሩ የቆዩት እነዚህ አካባቢዎች ከሚያዝያ 2016 ዓ.ም. አንስቶ መዋቀራቸው ፈርሷል።

በተለይም አላማጣ ከተማ ውስጥ ከሰፈሩት የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ውጪ መደበኛ የመንግሥት አገልግሎቶችን የሚሰጥ መዋቅር ሳይኖር ወደ ሁለተኛ ዓመት እየተጠጋ ነው። የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላትም ከረቡዕ ጥር 20 ሌሊት አንስቶ አላማጣ እና ኮረም ከተሞችን ለቅቀው መውጣታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ ሁኔታ ስጋት ፈጠረባቸው ነዋሪዎች በቅርብ ርቀት ወደምትገኘው የአማራ ክልሏ ቆቦ ከተማ መሸሻቸውንም አስረድተዋል።

ኢሰመኮ ትናንት ባወጣው መግለጫም " 'በኮማንድ ፖስት' ሲተዳደሩ ከቆዩት አላማጣ ከተማ እና ሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉ መሆኑን" እንደተገነዘበ አስታውቋል። በተጨማሪም በእነዚህ አካባቢዎች "በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ገደቦች መጣላቸውን" እንደተረዳ ገልጿል።

ትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎችን በሚያዋስኑት ሥፍራዎች የተነሳው ግጭት "የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ በአካባቢዎቹ ሰፍኖ የነበረውን አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት ወደ ኋላ የሚመልስ" እንደሆነ ኢሰመኮ ጠቅሷል።

"የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች ለተጨማሪ ጉዳት፣ መፈናቀል እና ሌሎች ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የሚያጋልጥ" እንደሆነ በመጥቀስም ስጋቱን አሰምቷል።

የሰብአዊ መብቶች ተቋሙ "በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ችግሩን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ" እንዲሁም "በሲቪል ሰዎች እና መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃቶችን ከማድረስ እንዲታቀቡ" ጠይቋል። "ለግጭት መነሻ የሆኑ ልዩነቶችን በሕግ መሠረት በምክክር እና በመግባባት ለመፍታት በቁርጠኝነት እንዲሠሩ" ሲልም አሳስቧል።

ከዚህ ግጭት ጋር በተያያዘ የሚወሰዱ "ማናቸውም እርምጃዎች የሰብአዊ መብቶች መርሆችን ያከበሩ" እንዲሆኑ ኢሰመኮ በመግለጫው ጠይቋል።

"በተለይም በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች" ዓለም አቀፋዊ እና አገራዊ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎችን ያከበሩ መሆን እንዳለበባቸውም አጽንኦት ሰጥቷል። እርምጃዎቹ "የሕጋዊነት፣ የጥብቅ አስፈላጊነት እና የተመጣጣኝነት መርሖችን ያከበሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል" ብሏል።

በተጨማሪም ተቋሙ ከሚያከናውነው መደበኛ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ "ጎን ለጎን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር የተፈጠረው ግጭት በውይይት የሚፈታበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እንደሚያደርግ" አስታውቋል።