ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኤርትራ መንግሥት በርካታ የወንጌላውያን እምነት ተከታዮችን ከእስር ለቀቀ
የኤርትራ ባለሥልጣናት በእምነታቸው ምክንያት ለእስር ተዳርገው የቆዩ በርካታ የወንጌላውያንን እምነት ተከታዮችን መልቀቃቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ትግርኛ ገለጹ።
ቁጥራቸው ከ40 የሚበልጡት ሰዎች ከዋና ከተማዋ አሥመራ አቅራቢያ ከሚገኘው ማይ-ሰርዋ ወታደራዊ እስር ቤት የተለቀቁት ባለፉት ቀናት ውስጥ ነው።
የኤርትራ መንግሥት ክልከላ የጣለባቸው የክርስትና ቤተ እምነቶች ተከታዮች የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገሪቱ ዜጎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከእስር እየተለቀቁ ነው።
በጥር ወር መጀመሪያ አካባቢ ጋሽ ባርካ በሚባለው የአገሪቱ ክፍል ውስጥ በእስር ላይ የነበሩ 13 የወንጌላውያን እምነት ተከታዮች ከእስር ወጥተዋል።
በተመሳሳይ በኅዳር ወር ላይ ክስ ሳይቀርብባቸው እና ካለ ፍርድ ቤት ውሳኔ ለዓመታት በእስር ላይ የቆዩ 100 የሚደርሱ የተለያዩ የክርስትና እምነት ቅርንጫፎች አብያተ ክርስቲያናት አባላት ከእስር መለቀቃቸው ይታወሳል።
ባለፉት ወራት የኤርትራ መንግሥት ከሃይማኖት ተከታዮች በተጨማሪ ለ18 ዓመታት በእስር ላይ የቆዩ ነጋዴዎችን፣ የፀጥታ ኃይል አባላትን እና ሌሎችንም ከማይ-ስርዋ እስር ቤት ለቅቋል።
በቅርቡ ከእስር ከተለቀቁት ሰዎች መካከል ሴቶች እንዲሁም ባል እና ሚስቶች ጭምር እንደሚገኙ ምንጮች ተናግረዋል።
ከ20 ዓመታት በፊት የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት በርካታ የእምነት ተቋማትን በይፋ በማገድ መሪዎቻቸውን እና ተከታዮቻቸውን አስረዋል።
ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በእስር ላይ ከሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች መካከል ዶ/ር ክፍሉ ገብረመስቀል፣ ቀሲስ ዶ/ር ፍጹም ገብረንጉሥ፣ ቀሲስ ዶ/ር ተክለአብ መንግሥተአብ፣ ቀሲስ ገብረሚካኤል ገብረጊዮርጊስ፣ ፓስተር ኪዳኔ ወልዱ እና ፓስተር ኃይሌ ናይዝጊ ይገኙበታል።
የተባበሩት መንግሥታት እና የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪዎች እስረኞቹ በይፋ ክስ እንዳልተመሠረተባቸው እና ፍርድ ቤትም አለመቅረባቸውን ይገልጻሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ተቋም ባለፈው ዓመት ባወጣው መግለጫ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ መምህራን እና የሃይማኖት መሪዎችን ጨምሮ አስር ሺህ የሚደርሱ እስረኞች እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርቧል።
የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት ከፍርድ ውጪ የሚፈጽሙት እስር ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይናገራሉ።
ኤርትራ ውስጥ በመንግሥት ዕውቅና ያላቸው አራት የእምነት ተቋማት ብቻ ናቸው። እነርሱም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ኢቫንጄሊካል ሉተራን ቤተርክስቲያን እና የሱኒ እስልምና ናቸው።
የኤርትራ መንግሥት ዕውቅና ከሰጣቸው የሃይማኖት ተቋማት ውጪ ያሉት ቡድኖችን የውጭ መንግሥታት መጠቀሚያ መሣሪያዎች ናቸው ሲል ይወነጅላቸዋል።
በዚህም የተነሳ ከአራቱ የእምነት ቡድኖች ውጪ ያሉ የሃይማኖት ተቋማት በአገሪቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ይፋዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ አይፈቀድላቸውም።
መንግሥት ዕውቅና የሰጣቸው የእምነት ቡድኖችም ቢሆኑ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ሲሆን ንብረቶቻቸውም በመንግሥት ይወረሳሉ።